1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጥሪ አቀረቡ

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሰኞ፣ መስከረም 19 2018

የትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ የፌደራል መንግስቱ ለትግራይ ጥያቄዎች በሕገመንግስቱ መሰረት ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል። በሌላ በኩል በትግራይ ውስጥ 'ሁሉ አካታች የመግባባት ጉባኤ' ለማድረግ መታቀዱን ጨምረው ገልፀዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመስቀል በዓል አከባበር ላይ
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ የመስቀል በዓል ባሰሙት ንግግር ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 በተካሔደው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬአቸው ሊመለሱ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። ምስል፦ Million Haileselassie/DW

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት ለትግራይ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጥሪ አቀረቡ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ በኩል ለሚቀርቡ ጥያቄዎች የፌደራል መንግስቱ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አስታወቀ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ የፌደራል መንግስቱ የትግራይ ጥያቄዎች በሕገመንግስቱ መሰረት ምላሽ ማግኘት አለባቸው ብለዋል። በሌላ በኩል በትግራይ ውስጥ 'ሁሉ አካታች የመግባባት ጉባኤ' ለማድረግ መታቀዱን ጨምረው ገልፀዋል።

የመስቀል በዓል በተከበረበት ይፋዊ ስነስርዓት ንግግር ያደረጉት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙርያ አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን ለጦርነት ምክንያት የሆኑ አጀንዳዎች ከሰላም ስምምነቱ በኃላ በውይይት እና ሕግ አግባብ ሊፈቱ ሲገባቸው እስካሁን ድረስ መቋጫ አለማግኘታቸው የትግራይ ህዝብ ለከፋ ሁኔታ ዳርጎ እንዳለ አመልክተዋል።

ፕሬዝደንቱ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በትግራይ በኩል እየቀረቡ ላሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ያሉ ሲሆን፥ በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀዬአቸው ሊመለሱ፣ በሕገመንግስቱ መሰረትም የትግራይ ግዛት ወደቦታው ሊመለስ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። 

የሰላም ስምምነቱ አደጋ ላይ

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በኢትዮጵያ መንግስት እና የትግራይ ሐይሎች መካከል የነበረው ጦርነት ያስቆመ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት አደጋ ላይ እንዳለም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ ግጭት የማቆም ሥምምነት ከተፈራረሙ ሦስት ዓመታት ሊሞላቸው የቀራቸው ጥቂት ወራት ነው።ምስል፦ SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

ጀነራል ታደሰ "የጦርነት ምክንያቶች እና ጉዳቶች በሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መንገድ እንዲፈቱ ዕድል የፈጠረ የፕሪቶርያ ስምምነት በሞት እና ሕይወት መካከል ሆኖ፥ ጦርነት ሳይመለስ ይሁን እንጂ በየግዜው በሚታዩ ተስፋ ሰጪ እና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ሆነን፥ ያለው ሰላም እየተንከባከብን እንደ መንግስት እና ህዝብ እየቀጠልን ነው። ይህ ሆኖ እያለ አሁን ያለንበት ተነፃፃሪ ሰላም የሚፈታተኑ፣ የሚቃረኑ፣ ወደ አደጋ የሚያስገቡ የውስጥና ውጭ ምክንያቶች መኖራቸው ግልፅ ነው" ብለዋል።

ሰላም ዘላቂ ማድረግ 

ከዚህ በተጨማሪ ጀነራል ታደሰ የአመራር ብቃት ሰላም ዘላቂ በማድረግ እንዲሁም ጦርነት በማስቀረት መለካት አለበት ያሉ ሲሆን ያሉ የሰላም ዕድሎች ለመጠቀም ግዚያዊ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ትግራይን ሊያጠቃበት የሚያስችል ተጨባጭ ምክንያት የለም ሲሉም ተናግረዋል።

ጀነራል ታደሰ "የፌደራል መንግስት ትግራይን ወቅታዊ እና ትክክለኛ ስጋት አድርጎ በመውሰድ የሚያጠቃበት፣ የሚያዳክምበት፣የሚዘጋበት ምንም ተጨባጭ ምክንያት አለ የሚል እምነት የለንም። እንደውም አሁን ያለው ሰላም እንደወርቃዊ ዕድል በመጠቀም፥ በረባ እና ያልረባ ምክንያት ከእጃችን ወጥቶ እንዳይባክን ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል" ሲሉ ገልፀዋል።

ያልተፈፀሙ የስምምነት ይዘቶች 

በትግራይ ስላለው ሁኔታ የተናገሩት የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ያሉ ልዩነቶች ለመፍታት እንዲሁም የተጋሩ አንድነት ለመመለስ ያለመ የመግባባት ጉባኤ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል። የፕሪቶርያ የሰላም የእስካሁን አፈፃፀም በማንሳት ህወሓት እና የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ቅሬታዎች የሚያነሱ ሲሆን የውሉ ትልልቅ ይዘቶች አልተፈፀሙም፣ ለዚህም ተጠያቂው የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ነው ሲሉ በተደጋጋሚ ይከሳሉ። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት በበኩሉ ላለተፈፀሙ ጉዳዮች ተጠያቂው ህወሓት አድርጎ ያቀርባል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW