የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥትና ክልሎች የሚሰበስቡት ግብር በሚያዝያ “ከትሪሊዮን ብር ይሻገራል”
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 29 2017
የኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ዘጠኝ ወራት 646.7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 653.2 ቢሊዮን ብር እንደተሳካለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ሰነድ ያሳያል። ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሰበሰቡት የገንዘብ መጠን ከታቀደው 101% ነው።
ከባለፈው ዓመት በ279 ቢሊዮን ብር ወይም 74.56 በመቶ ይልቃል። በገቢዎች ሚኒስቴር ሰነድ መሠረት 345.93 ቢሊዮን ብር ከሀገር ውስጥ ታክስ 307.3 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከውጪ ንግድ ቀረጥ እና ታክስ የተሰበሰበ ነው።
የገቢዎች ሚኒስትሯ ዓይናለም ንጉሴ የመሥሪያ ቤታቸውን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ሚያዝያ 28 ቀን 2017 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ግን ፌድራል መንግሥት እና የክልል መስተዳድሮች የሰበሰቡት የታክስ ገቢ በሰነዱ ከተጠቀሰው የላቀ እንደሆነ ሪፖርት አድርገዋል።
ወይዘሮ ዓይናለም “አሁን ባለኝ ሪፖርት በሚያዝያ ወር የእኛም የክልሎችም ተደምሮ ከትሪሊዮን [ብር] ይሻገራል። የፌድራል መንግሥት ዛሬ ላይ ሆነን እስከ 720 [ቢሊዮን ብር] ደርሰናል” ሲሉ ተደምጠዋል። በ2017 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት 1.5 ትሪሊዮን ብር በግብር መልክ የመሰብሰብ ዕቅድ አለው። ከዚህ ውስጥ የፌድራል መንግሥት 900 ቢሊዮን ብር፤ የክልል መንግሥታት በአንጻሩ 600 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ይጠበቅባቸዋል።
መንግሥት የሰበሰበው የገቢ መጠን ካለፈው ዓመት አኳያ በከፍተኛ መጠን የጨመረው የኤክሳይዝ ታክስን በመከለስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እና የወጪ ንግድ የቀረጥ ማበረታቻ ሥርዓት አዋጆችን በማሻሻል እንዲሁም የታክስ መሠረቱን በማስፋት ነው።
የገቢዎች ሚኒስትሯ ዓይናለም ንጉሴ እንዳሉት “ከተጨማሪ እሴት ታክስ አሰባሰብ አኳያ” በተለይ በሐምሌ 2016 የተደረገው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ “የማይናቅ ለውጥ አምጥቷል።” የንግድ ትርፍ ግብር እና ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶች መንግሥት በየዓመቱ በሚሰበስበው የሀገር ውስጥ ገቢ ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙ ናቸው።
ይሁንና “የሀገራችን የታክስ ሕግ ተገዢነት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠነኛ መሻሻል እያሳየ ቢሆንም በተለይ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶችን ለመሰብሰብ የታክስ አስተዳደሩ የሚያደርገው ጥረት በተለያዩ ችግሮች ውስጥ እየተፈተነ ያለ ነው” ሲሉ ወይዘሮ ዓይናለም ተናግረዋል።
የገቢዎች ሚኒስትሯ “ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ለምሳሌ እንደ ተጨማሪ እሴት ታክስ የመሳሰሉትን ስናይ በሻጭም ሆነ በገዢ በኩል ያለው አመለካከት፤ ለታክስ ያለው የግንዛቤ ደረጃ ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ነው” በማለት አስረድተዋል።
መንግሥት ባለፉት ወራት ገቢውን ለማሳደግ ቆርጦ ሲነሳ በባንክ አገልግሎት ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፈል አድርጓል። ለቴሌኮምዩንኬሽን አገልግሎት የኤክሳይዝ ታክስ ይከፈላል። ኢትዮጵያውያን በቤት እና በመሬት ግብር የሚከፍሉበት የንብረት ታክስ ሥራ ላይ የዋለው በተያዘው ዓመት ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በንግድ ግብይቱ ውስጥ ወይዘሮ ዓይናለም በሚመሩት የገቢዎች ሚኒስቴር መሣሪያዎች ብቻ የሚነበብ ባለ ልዩ መለያ ኮድ (QR Cod) ደረሰኝ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የታክስ አሰባሰብ ሒደቱን ለማቀላጠፍ እና ቁጥጥሩን ለማጥበቅ ወስኗል።
መንግሥት ገቢውን ለማሳደግ በተከተለው አካሔድ የሰበሰበው የገንዘብ መጠን ብቻ ሳይሆን በግብር ከፋዮች ላይ ያሳደረው ጫና ጭምር ሊታይ እንደሚገባ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ይሞግታሉ። “የታክስ ባለሥልጣን በጣም ትልቅ ጉልበት ያለው ተቋም ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን መሥሪያ ቤቱ ባለው ኃይል የፈለገውን ቅጣት በመጣል እና ታክስ በመተመን ሊሰበስብ እንደሚችል ተናግረዋል።
እንዲያም ሆኖ ግን የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም “የመንግሥት ገቢ አድጓል ምንም ጥያቄ የለውም። ነገር ግን የተሰበሰበው ገቢ ከሀገር የልማት ፍላጎት አኳያ” በቂ አይደለም የሚል ዕምነታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። መንግሥታቸው ከታክስ የሚሰበስበው ገቢ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ ያለውን ምጣኔ ለማሳደግ “በጣም ብዙ መሠራት ይጠበቅበታል” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በመጪዎቹ አራት ዓመታት ከታክስ የሚሰበስበውን ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ በአራት በመቶ የማሳደግ ዕቅድ አለው። ወይዘሮ ዓይናለም ለሕግ አውጪው ምክር ቤት መንግሥታቸው በያዘው ዕቅድ መሠረት በ2017 ከታክስ የሚሰበስበው ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አኳያ በአንድ በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
“የዛሬ ዓመት የሚሰበሰበው ታክስ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ያለው ድርሻ 6.8% ቢሆን ይኸን ዓመት ስናጠቃልል 7.8% እናደርሳለን። በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ደግሞ ሠርተን ከ10% ለማድረስ ነው ዕቅድ ይዘን እየሠራን ያለንው” ሲሉ ተደምጠዋል። ይህን ለማሳካት በሒደት “በታክስ ፖሊሲ እና በአስተዳደር ረገድ ያሉ ችግሮችን መፍታት” ይጠይቃል። ከዚህ በተጨማሪ “ኢ-መደበኛ” የሚባለውን ክፍለ-ኢኮኖሚ ወደ ታክስ ሥርዓት ማስገባት እና “በዲጂታል ሲስተም የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር” መንግሥት ሊከተል ያቀዳቸው አካሔዶች ናቸው።
ኢትዮጵያ ከታክስ የምትሰበስበው ገቢ ኬንያን ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት ያነሰ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚተቹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን ባለፈው ጥቅምት 2017 መንግሥታቸው የሚሰበስበው ታክስ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ በተያዘው ዓመት ወደ 8.5 በመቶ ከፍ እንዲል መታቀዱን ተናግረው ነበር።
“አሁን በጀመርንው ሪፎርም ዘንድሮ 2% እንኳ ማሻሻል ብንችል የምንደርሰው ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርታችን 8.5% ነው” ያሉት ዐቢይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ “ልናስገባ ከሚገባን በጣም ሩቅ ነን። ከ10% በታች ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ ዕቅድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት 3.4 ቢሊዮን ዶላር ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በሚበደርበት ሥምምነት የተካተተ ግዴታ ነው። መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው አበዳሪ ተቋም የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) 117 ቢሊዮን ዶላር ይገምተዋል።
በድርጅቱ ሰነድ መሠረት መንግሥት ከታክስ የሚሰበስበው ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) ያለው ምጣኔ ባለፈው ዓመት 7.3 በመቶ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ወደ 8.5 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል። የታክስ ገቢ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት አኳያ ያለው ምጣኔ እያደገ ሔዶ በጎርጎሮሳዊው 2028/29 ወደ 11.4 በመቶ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአይኤምኤፍ መረጃ ያሳያል።
ዶክተር አብዱልመናን ግን የኢትዮጵያ “የአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) መረጃ (data) በጣም የተጋነነ ቢሆንስ?” የሚል ጥያቄ አላቸው። “በጣም የተጋነነ ከሆነ” ከታክስ የሚሰበሰበው የገቢ መጠን ለራሱ ለመንግሥት “ያነሰ” ሊመስል እንደሚችል ያስረዳሉ። በዚህ ምክንያት ከታክስ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ መንግሥት “በጣም ጨከን፤ መረር ያሉ እርምጃዎች” ወደ መውሰድ ሊያመራ ይችላል።
“ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ ማተም አቁሙ ብሏቸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት እንደፈለገው ብር የሚያትምበት ዘመን አብቅቷል” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ የቀረው አማራጭ ገቢን ማሳደግ ወይም ወጪን መቀነስ እንደሆነ ይናገራሉ። “የኢትዮጵያ መንግሥት ገቢ መጨመርን መርጧል” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “ይኸ ግን አደጋም ሊኖረው ይችላል። ብዙ ቢዝነሶችን ከገበያ ሊያስወጣ ይችላል፤ ብዙ ብሶትም ሊቀሰቅስ ይችላል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።
የዐቢይ መንግሥት ከታክስ የሚሰበሰበውን ገቢ በሦስት ዓመታት ውስጥ በአራት በመቶ ለማሳደግ ዕቅድ የያዘው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በግጭት፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና የጸጥታ መጓደል በኃይል በሚፈተንበት ወቅት ነው። የዋጋ ንረት እና የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ለውጥ ሲደረግ የተከተለው የብር የመግዛት አቅም መዳከም በዜጎች ላይ የፈጠሩት ጫናም ቀላል አይደለም።
“የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ በግልጽ የሚታይ ጉዳይ ነው። ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ እየተከተለ ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን መቋጫ ካልተበጀላቸው ግጭቶች ጋር ተደማምሮ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሐብት ፈተና መሆናቸውን አስታውሰዋል። “ሕብረተሰቡ ውስጥ የፍርሐት ስሜት አለ። ወጣም ብለህ እንደፈለክ እንደ ድሮው የምትሠራበት ወቅት አይደለም” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው “በዚህ ሁኔታ ላይ የምትሰበስበው ገቢ ዜጎችን አንቀህ እንደሆነ የታወቀ ነው” ሲሉ ይናገራሉ።
አርታዒ ማንተጋፍቶት ስለሺ