የኢትዮ ሱዳን የድንበር አካባቢ ባለሥልጣናት ውይይት
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 24 2015
ሱዳንና ኢትዮጵያ በድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ በሚፈጠሩ የተለያዩ ምክንያቶች ወደ አለመግባባት እየደረሱ በታጣቂዎች መካከል ግጭቶች እየተከሰቱ በየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ላይ ማኅበራዊ ችግሮች ይፈጠራሉ። በተለይ ከእንስሳት ስርቆት ጋር በተያያዘ በሁለቱ አጎራባች ወረዳዎች መካከል ግጭቶች ሲነሱ ቆይተዋል። እነኝህን ችግሮች ለማስወገድና ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን አሳልፎ መስጠት የሚያስችልና ከሁለቱም ወገን የተሰረቁ እንስሳት ወደየአካባቢዎቹ እንዲመለሱ የሚያደርጉ ውይይቶች በአካባቢ አስተዳደሮች መካከል ሲካሄድ እንደነበርና ሰሞኑንም የዚያው ተከታይ የሆነ ውይይት በቋራ ወረዳ ነፍስ ገበያ ቁጥር 4 መካሄዱን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የቋራ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ አመልክቷል።
የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሞገስ ለዶቼ ቬሌ በስልክ እንደተናገሩት፣ በተከታታይ የተደረጉ ውይይቶች ውጤት አስመዝግበዋል፣ ከእኛ የተዘረፉ እንስሳት ተመልሰዋል ከእነርሱም የተወሰዱ እንስሳት ተመልሰዋል ብለዋል። ከአንድ ወር በኋላ ውይይቱን ወደ ዞን ደረጃ ለማሳደግ እቅድ መያዙን የሚናገሩት አቶ ደሳለኝ፣ በተገኙ ውጤቶች ኅብረተሰቡ እፎይታ ማግኘቱን አመልክተዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ቢሆነኝ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሱዳን የረጅም ጊዜ ወዳጆች መሆናቸውን አስታውሰው በየጊዜው የሚደረጉ ውይይቶች የሁለቱን ሃገራት ህዝቦች የቆየ ታሪካዊ ትስስር ለማጠናከር እና ሰላማዊ ግንኙነቱም የጎላ እንዲሆን ያለመ መሆኑን ለዶይቼ ቬሌ አብራርተዋል።
አገራዊ የሆኑና ከፍ ያሉ ጉዳዮች በፌደራል ደረጃ የሚታዩ እንደሆኑ ያመለከቱት አቶ ፋንታሁን «በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚፈቱ ችግሮችን እየፈታን ነው»ም ብለዋል። በጥቅምት 24/2013 ዓ ም የተከሰተውን የሰሜን ጦርነት ተከትሎ የሱዳን ጦር በተለያዩ የምዕራብ ጎንደር አካባቢዎች በግብርና ዘርፍ በተሰማሩ ባለሀብቶች ላይ ጥቃት ከፍቶ ነበር፤ በሰኔ 2014 ዓ ም ደግሞ የሱዳን መንግሥት «ሰባት ወታደሮቼ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ተገድለውብኛል» በሚል፣ ሁለቱ አገሮች የይገባኛል ጥያቄ በሚያቀርቡበት የአልፋሽጋ አካባቢ የሱዳን ጦር ጥቃት ፈፅሞ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወታደሮቹን እንዳልገደለ መግለጹ ይታወሳል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ