1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የድንበር ግጭቶችን በዲፕሎማሲ የመፍታት እንቅስቃሴ

ረቡዕ፣ ግንቦት 26 2012

ባለፈው ግንቦት 20 ገበሬዎች በድንበር አካባቢ በሚያካሂዱት የእርሻ እንቅስቃሴ ምክንያት የተከሰተው ግጭትም የተለመደና ተመሳሳይ ይዘት ያለው ቢሆንም እንቅፋት የሆኑ ገዳዮችን በመለየት ችግሩን በሰላማዊና በዲፕሎማሲ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት በሁለቱም ሀገራት መካከል አዲስ አበባና ካርቱም ላይ ውይይት መጀመሩንም ይፋ አድርገዋል::

Äthiopien E. Gedu Andargachew, Außenminister
ምስል፦ Prime Minister Office of Ethiopia

የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ግጭት እና የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ምላሽ

This browser does not support the audio element.


ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በድንበር አካባቢ የሚከሰተውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ውዝግቡ በውይይትና  በዲፕሎማሲ እንዲፈታ እንቅስቃሴ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተለይ ለዶይቼ ቨለ "DW" እንደገለፁት የኢትዮጵያ ገበሬዎች በያዙትና ሱዳኖች በቅኝ ግዛት ተከልሏል የኛ ነው በሚሉት የመሬት ይዞታ ከምዕተ ዓመት የዘለቀ ውዝግብ አልፎ አልፎ ሲያጋጥም የቆየ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል::ባለፈው ግንቦት 20 ገበሬዎች በድንበር አካባቢ በሚያካሂዱት የእርሻ እንቅስቃሴ ምክንያት የተከሰተው ግጭትም የተለመደና ተመሳሳይ ይዘት ያለው ቢሆንም እንቅፋት የሆኑ ገዳዮችን በመለየት ችግሩን በሰላማዊና በዲፕሎማሲ መንገድ በዘላቂነት ለመፍታት በሁለቱም ሀገራት መካከል አዲስ አበባና ካርቱም ላይ ውይይት መጀመሩንም ይፋ አድርገዋል:: ሚያዝያ 4,2012 ዓ.ም አሻራቅ አል-አዋሳት የተሰኘ አንድ የመካከለኛው ምስራቅ የዜና አውታር የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ በሱዳን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ባወጣው ዘገባ ሱዳንና ኢትዮጵያን የሚያወዛግበውን የ "አል ፋሻቅ" ለም የእርሻ መሬት ለሱዳን የመመለስ ፍላጎት መኖሩን በመግለፅ ያወጣውንም መረጃ "በሀገራቱ መካከል የድንበር አካባቢ ግጭቶችን ለመፍታት በሚቻልበት ስልት ዙሪያ ከተደረገ ውይይት ውጪ በዘፈቀደ የተሰጠም ሆነ የሚሰጥ መሬት የለም ዘገባው ሃሰት ነው" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል:: ባለፈው ግንቦት 20,2020 ዓ.ም የሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች የሚደገፉ ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው በመግባት ጥቃት አድርሰውብኛል ሲል ክስ አቅርቧል። አልቃዳሪፍ በተባለው ቦታ ተፈፅሟል በተባለው በዚህ ጥቃት የሞትና የመቁሰል ጉዳት መድረሱንም ገልጿል። ሮይተርስ የሱዳኑን የጦር ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል አሚር መሐመድ አል ሐሰንን ጠቅሶ እንደዘገበው በተደጋጋሚ ግጭት በሚከሰትበት አልቃዳሪፍ በተባለው የድንበር አካባቢ የእርሻ ቦታ የውኃ ጉድጓድን ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት በታጣቂዎቹና በሱዳን ወታደሮች መካከል በተካሄደው ግጭት አንድ የሱዳን የጦር መኮንን ሕይወቱን ሲያጣ 7 ያህል ወታደሮችና ሰላማዊ ዜጎችም ቆስለዋል ተብሏል:: ግጭቱ ሌላ ፖለቲካዊ ይዘት ይኖረው ወይም አይኖረው እንደሆነ ከዚህ ውጪ ተከሰተ የተባለው ግጭት በህዳሴው ግድብ የውኃ አሞላልና አስተዳደር ጉዳይ በሚያደርጉት ቀጣይ ውይይት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ስለመኖሩና ተጨማሪ የብቀላ ጥቃት ሊኖር ይችላል በሚለው ስጋት ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጠይቀናቸው ነበር:: "በሱዳንና በኢትዮጵያ ድንበር አልፎ አልፎ በተለይም በግንቦትና ሰኔ ወራቶች ገበሬዎች የእርሻ መሬት ለማረስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግጭት ያጋጥማል::ይሄም የተለመደ ግጭት ነው:: ከ 100 ዓመታት በላይ በአካባቢው የመሬት ይገባኛል ውዝግቡ በተለያዩ ጊዜያት ሲከሰት የቆየ ጉዳይ መሆኑ አይዘነጋም:: በመሰረቱ መሬቱ በኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ይዞታ ስር ነው የሚገኘው :: በሌላ በኩል ደግሞ በቅኝ ግዛት ዘመን ተከልሏል የሚባልና ሱዳኖች የእኛ ነው የሚሉት የመሬት ይዞታ አለ:: ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቶቹ ግጭቶት በየጊዜያቱ ያጋጥሙ እንጂ የሁለቱም ሀገራት መንግሥታት ችግሮቹን እያጓጓኑ ወደባሰ ጥፋትና ችግር እንዲሸጋገር አድርገው አያውቁም:: አሁንም ይህ ችግር ሊፈታ የሚችለው በውይይትና በዲፕሎማሲ መሆኑ በሁለቱም ወገኖች ስለሚታመን ያለንን መልካም ጉርብትናና ታሪካዊ ግንኙነት ተጠቅመን እንደ ሌላው ጊዜ ሁሉ ይሄንንም ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ እንፈታዋለን የሚል ፅኑ ዕምነት አለኝ" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልፅዋል::የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚን ጠርቶ ባለፈው ማክሰኞ በአልቀዳሪፍ ከተማ አቅራቢያ ተፈጸመ በተባለ ጥቃት ላይ ያለውን ተቃውሞ መግለፁ ታውቋል። የኢትዮጵያ መንግስትም በቅርብ የተከሰተውን ብቻ ሳይሆን ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሁለቱ ሀገራትን ሲያወዛግብ የኖረው የመሬት ይገባኛልና የድንበር አካባቢ የፀጥታ ችግሩ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ አንዲጣራና ችግሩ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ በግልፅ ለሱዳን መንግስት ጠይቋል።የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያም ሆነ በሱዳን በኩል ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ ሀዘኑን የገለፀ ሲሆን እንዲህ ዓይነቶቹ ክስተቶች በሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች መካከል ያለውን ጥብቅ ወዳጅነት አይወክልም ነው ያለው። ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበትና ከፍተኛ የእርሻና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በሚከናወንበት  በምዕራብ ጎንደር መተማ ቋራ እና ታች አርማጭሆ ባሉ አካባቢዎች የሱዳን ጦር የኢትዮጵያ ድንበር ጥሶ በመግባት ተደጋጋሚ ጥቃት ፈፅሟል የሚል ቅሬታ በአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሰቀርብ ቆይቷል:: ባለፈው ሚያዝያ 4,2012 ዓ.ም አሻራቅ አል-አዋሳት የተሰኘ አንድ የመካከለኛው ምስራቅ የዜና አውታርም የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ በሱዳን ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ባወጣው ዘገባ " ሱዳን ከኢትዮጵያና ግብፅ ጋር በሚያዋስናት የሃላየብ ትሪያንግልና በአልፋሻቅ ለም የእርሻ መሬት ለዓመታት የዘለቀ የድንበር ውዝግብ እንዳላት በማውሳት በተለይምለረጅም ዘመናት ሁለቱን ሀገራት ሲያወዛግብ የቆየው 600 ስክዌር ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን "የአል ፋሻቅ" መሬት ከኢትዮጵያ ጋር በተደረሰ ስምምነት በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለሱዳን ለመለስ ከስምምነት ላይ ተደርሷል" የሚል አወዛጋቢ ዘገባ አውጥቶ ነበር:: ይህ ዘገባ ምን ያህል ተአማኒነት አለው ስንልም አቶ ገዱን ጠይቀናቸው "ፍፁም ሃሰት ነው" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል:: "ሱዳንም ሆነች ኢትዮጵያ በይገባኛል የሚያነሷቸው የመሬት ይዞታዎች አሉ:: በሀገራቱ መካከል የድንበር አካባቢ ግጭቶችን ለመፍታት በሚቻልበት ስልት ዙሪያ ከተደረገ ውይይት ውጪ በዘፈቀደ የተሰጠም ሆነ የሚሰጥ አንዳችም መሬት የለም ዘገባው ሃሰት ነው" በማለት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል:: በሁለቱ አገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በየጊዜው የሚያጋጥሙ የፀጥታና የደህንነት ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉናየሁለቱን አገሮች የድንበር ጉዳይ በተመለከተ” አዲስ አበባ ላይ ከግንቦት 8-10 ውይይት የተደረገ ሲሆን በሀገራቱ አዋሳኝ ድንበሮች የሚፈፀም ህገ-ወጥ የሰዎችና የጦር መሳሪያዎች ዝውውር፣ አፈናና የመሳሰሉ የወንጀል ድርጊቶችን በጋራ ለመከላከልና መፍትሄ ለመሻት የሚያስችል አቅጣጫም ማስቀመጡ ተነግሯል።ቀጣዩም ውይይት በቅርቡ ካርቱም ላይ እንደሚካሄድም ነው የተገለፀው:።እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር ሐምሌ 3, 2007 ዓ.ም ሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ እንደ ጎርጎሮዋዊው አቆጣጠር በ1971 ዓ.ም  ሁለቱ አገራት ዳግም ድንበራቸውን ለማካለል በደረሱት ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያና ሱዳን ከ 100 ዓመታት በላይ ሲወዛገቡባቸው የቆዩ በምስራቃዊ አትባራ ወንዝ ዳርቻ ሁለቱን ሀገራት የሚያዋስኑ 17 ቀበሌዎች ለሱዳን በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ የቴክኒክ ዝግጅት መጠናቀቁን የሚገልፅ አንድ ዘገባ ካወጣ በኋላ ድርጊቱን የተቃወሙ ኢትዮጵያውያን "የኢትዮጵያ ድንበር አስመላሽ ኮሚቴ" የሚል እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይታወሳል :: መንግስት ሱዳንን በሚያዋስነው መተማ አቅራቢያ ደለሎ አካባቢ የሚገኘውን ይህንኑ 12ሺህ ሄክታር ያህል ለም የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን ሰጥቷል መባሉን ሲያስተባብል ቢቆይም የአማራ ክልል ገዥ ፓርቲ አዴፓ ከሁለት ዓመታት በፊት ከለውጡ በኋላ በዚሁ አወዛጋቢ የመሬት ጉዳይ ላይ ልዩ  ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ውይይት እንደሚጀምር አስታውቆ ነበር:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ አሜሪካና የዓለም ባንክ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የነበራቸው የሽምግልና ሚና ጥቅሜን የሚጎዳ ነው በማለት ውይይቱን ማቋረጧ ይታወሳል:: የውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ከአሁን ቀደም በተያዘለት ዕቅድ መሰረት በሐምሌ ወር መከናወን እንደሚጀምር ቢገልፅም አሜሪካ በበኩሏ በጉዳዩ ላይ ስምምነት ላይ ሳይደረስ የግድቡ የውሀ ሙሌት እንዳይጀመርና ባለድርሻዎቹ ሀገራት በአስቸኳይ ወደተቋረጠው ድርድር እንዲመለሱ ለጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ጥያቄ አቅርባለች። በሶስቱ ሀገራት መካከል ተቋርጦ የቆየው ውይይት የኢትዮጵያን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ዳግም ለመቀጠል መስማማታቸውንም
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለዶይቼ ቨለ "DW" ጨምረው ገልፀዋል::

እንዳልካቸው ፈቃደ
ታምራት ዲንሳ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW