1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ኤርትራ ስምምነት አንድምታና ተግዳሮት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 3 2010

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ እና የኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈንና ግንኙነቶችን ለማደስ በሚል በአምስት ጉዳዮች ላይ ስምምነቶችን መፈራረማቸው ተገልጧል። የሁለቱ ሀገራት ስምምነት አንድምታውና ተግዳሮቱ ምን ይመስላል?

President Isaias Afwerki &  Prime Minister Abiy Ahmed in Asmera
ምስል Yemane G. Meskel

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ እና የኤርትራ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማስፈንና ግንኙነቶችን ለማደስ በሚል በአምስት ጉዳዮች ላይ ስምምነቶችን መፈራረማቸው ተገልጧል። ባለ አምስት ነጥብ ስምምነቶቹ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር በድረ ገጹ፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ደግሞ በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድርገዋል። የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ቻላቸው ታደሰ ስምምነት የተደረገባቸው አምስቱ ነጥቦች አንድምታቸው ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።

«የሁለቱ ሀገራት የተስማሙባቸው አምስቱ ነጥቦች በጣም ከፍተኛ አንድምታ ያላቸው አድርጎ ነው መውሰድ የሚቻለው። በሁለቱ ሀገራት የንግድ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ ግንኙነትም ኾነ በቃጣናው በአፍሪቃ ቀንድ ላላቸው ለሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊ እና ማንኛውም ፖለቲካዊ  እንቅስቃሴ የአጠቃላይ  የቃጣናው ንግድ እንቅስቃሴ ትስስርን ከፍተኛ አንድምታ ነው ያላቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል።»

ምስል Imago/photothek

ለአብነት ያህልም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በዲፕሎማሲው መስክ በተለይ ሶማሊያ ላይ ያንጸባርቁ የነበረው ፖለቲካ እጅግ ተጻራሪ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ቻላቸው አሁን ኢትጵያ በሶማሊያ ምክንያት ኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ መጠየቋ ትስስሩን ያጠናክራል ብለዋል። ኾኖም የድንበር ስምምነቱን ኤርትራ በምን መልኩ ልትተገብረው እንደምትችል ግልጽ ባልኾነበት ማዕቀቡ ይነሳ የሚለው ጥያቄ የተቻኮለ እንደኾነ የፖለቲካ ተንታኙ ስጋታቸውን ገልጠዋል።

ሁለቱ ሀገራት አካባቢያዊ ሰላም፣ ልማት እና ትብብር እንዲጠናከር በጋራ ጥረት እንደሚያደርጉ በስምምነታቸው ተገልጿል። በሌላ መልኩ ኤርትራ ወደ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመጣች ቁጥር በሀገሯ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ ሊያጭርም ይችላል ሲሉ አክለዋል አቶ ቻላቸው። የወደብ አጠቃቀምን በተመለከተም ባለ አምስት ነጥቡ ስምምነት ስለሚኖረው ተግዳሮት አቶ ቻላቸው ቀጣዩን ብለዋል።  

«የአሰብ ወደብ በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የማስተናገድ አቅሙ ምን ላይ እንዳለ ዐናውቅም። ላለፉት ኻያ ዓመታት ያው ዝግ ኾኖ የኖረ ነው። ያም ኹኖ ግን ኢትዮጵያ በየትኛውም መለኪያ የአሰብን ያኽል የሚጠቅማት እንደሌለ በርካታ ባለሞያዎች የታወቀ ነው።  ስለዚህ አኹን በቃጣናውም ስናየው፤ ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ወደብ በርበራን እየተጠቀመች ነው። ጅቡቲንም እየተጠቀመች ነው። አኹን ፊቷን ወደ አሰብ የምታዞር ከኾነ፤ በእርግጥም ታዞራለች ተብሎ ነው የሚጠበቀው፤ የኤርትራ መንግሥትም ይኽን ይፈልጋል።  በጅቡቲ እና በሶማሊላንድ ወደቦች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ አንድምታ ነው የሚኖረው። ጅቡቲና ኤርትራ ደግሞ  እንደምናውቀው ጥል ናቸው።»

በፌስቡክ ገጻችን ባደረግነው ውይይት ሁሴን ሐሰን የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦« በስሙነቱ መሰረት ኤርትራ የባህር ወደቧን ክፍት ማድረግ አለባት» ብለዋል። ተማም ያሲን በበኩላቸው፦ «የወደብ የድንበር ጥየቄን ሊፈታ የሚችለው ሁለንተናዊ integration ሲኖረን ነው። ይህን ለማምጣት ቀጣይ አዎንታዊ ዉይይት ይጋብዛል። ከመደማመጥ ብዙ ነገሮች ይመጣሉ» የሚል አስተያየት አስፍረዋል።  «እኛ በመጀመሪያ የወደብ ጉዳይ አያስጨንቀንም ህዝቦቻችን እንጂ» የሚለው አስተያየት የተሻገር ሽጉጤ ነው።

ምስል Reuters/T. Mukoya

በባለ አምስት ነጥቡ ስምምነት መሰረት በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የነበረው የጦርነት ስጋት ማብቃቱ የተገለጠ ሲኾን፤ የሰላምና የወዳጅነት አዲስ ምዕራፍ መከፈቱም ይፋ ተደርጓል። ሁለቱ መንግሥታት የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሐብት፣ የማኅበራዊ፣ የባህል እና የደኅንነት ትብብር ለማድረግ እንደሚጥሩ፤ ይኽም የሕዝቦቻቸውን ጥቅም ለማስከበር ወሳኝ መኾኑ ተገልጧል። በሁለቱ ሃገራት መካከል የመጓጓዣ አገልግሎት፣ ንግድ እና ኮሙኒኬሽን ያንሰራራልም ተብሏል። ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እና እንቅስቃሴዎች ዳግም ተጀምረው የሁለቱን ሃገራት ድንበር የተመለከተው ውሳኔ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተጠቅሷል። አቶ ቻላቸው የድንበሩን ኹኔታ በተመለከተ ተጨማሪ ተግዳሮት ሊኖር እንደሚችል ተናግረዋል።

«በድንበር በኩል ስናየው የትግራይ እና የአፋር ክልል አንድ ተግዳሮት ነው። ጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ  ትግራይ ክልልን የሚመራው ሕወሓት ብዙ ነጥቦችን እያነሱ ለውጡን የመቃወም አዝማሚያ ይታያል። ኤርትራ ላይ የተደረገው ስምምነትም፤ ጦርነቱን በማቆሙ ረገድም የልሉ ገዢ ፓርቲ ሕወሓት ግልጽ የኾነ አቋም ማንጸባረቅ አልቻለም። ድፍንፍን ያለ ኹኔታ ነው። እንግዲህ ምናልባት የኤርትራ ልዑካን ቡድን ወደ ትግራይ ወደ መቀሌ  ይኼዳል ተብሏል፤ ምናልባት ያኔ ኹኔታዎች ከፈትፈት ሊሉ ይችላሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ ይቻላል።»

ስለ መግለጫው ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍጹም አረጋ ጋር በተደጋጋሚ ብንደውልም ስብሰባ ላይ እንደኾኑ ተነግሮናል። የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ስልክ በተደጋጋሚ ቢጠራም አይነሳም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW