1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ኤርትራ ዉዝግብ

ሰኞ፣ የካቲት 28 2008

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ኤርትራን ደጋግሞ ማዉገዝ-ማስጠንቀቁም ምናልባት የማይመቸዉን የአስመራና የሐያላኑን መቀራረብ የትኩረት አቅጣጫን ከኦሮሚያዉ ዓይነት ግጭትና ሁከት ለማስቀየስ አልሞ ሊሆን ይችላል።ባይሆን እንኳ ጋዜጠኛ ሮንግ እንዳለችዉ የዉግዘት፤ ዛቻዉ መደጋገም ኢትዮጵያ ምናልባት ወታደራዊ ጡንቻዋን ልትሞክር ትችላለች ማሰኘቱ አልቀረም

ምስል Reuters/T. Mukoya

[No title]

This browser does not support the audio element.

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠንካራ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ «ደደብ»-(stupid) ያሉት የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከቆመ እነሆ ዘንድሮ አስራ-ስድተኛ ዓመቱን አገባደደ።ይሁንና እንደ ጥብቅ ወዳጅ የጋራ ጠላታቸዉን በአንድነት ወግተዉ አስመራ እና አዲስ አበባ ላይ አዳዲስ መንግሥታት ባቆሙ በሰባተኛ ዓመታቸዉ ዉጊያ የገጠሙት ሐይላት ሙሉ ጦርነት አቆሙ እንጂ ሠላም አስፍነዉ አያዉቁም።ጦርነት የለም።ቁርቁስ፤ ሽኩቻ፤ዛቻ፤ ፉከራ-መካከሱ ግን አልተቋረጠም።እና ሠላምም የለም።ሰሞኑን ደግሞ መወጋገዝ፤ መካሰሱ ይደጋገም ይዟል።ሰበብ ምክንያት አስተጋብኦቱ የዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።።

የሶማሊያ የርስ በርስ ጦርነት ሲግም የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጥታ፤ የኤርትራ በተዘዋዋሪ ጦርነቱን ዘዋሪዎች ናቸዉ።ሠሜንና ደቡብ ሱዳን ሲጋጩ-ሁለቱ ሐገራት በተቃራኒ ጎራ ለመቆም አላመነቱም።ደቡብ ሱዳኖች እርስ በርስ ሲዋጉ፤ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት የሁለቱ መንግሥታት እጅ በቀጥታም፤ በተዘዋዋሪም አለበት።አንዳቸዉ የሌላቸዉን አማፂ ቡድን ማስታጠቅ፤ ማስጠጋት ማደራጀታቸዉም ሚስጥር ሆኖ አያዉቅም።

ሥለ ሁለቱ ሐገራት ግጭትና ግንኙነት ሁለት መፅሐፍት ያሳተመችዉ ጋዜጠኛ ሚካኤላ ሮንግ እንደምትለዉ አንዳቸዉ የሌላዉን ሥርዓት ለማዳከም የማያደርጉት የለም።«ያሁኑን ወቀሳ ዝርዝር ጉዳይ ትተን ሁለቱ ወገኖች ላለፉት አስራ-ስድስት ዓመታት አንዳቸዉ የሌላቸዉን አማፂ ቡድናትን እና ንቅናቄዎችን ለመርዳት አላመነቱም።አማፂያኑ የሚንቀሳቀሱበት አስተማማኝ የጦር ሠፈር፤ ዋና ፅሕፈት ቤት፤ ገንዘብ ይሰጣሉ።ይሕን የሚያደርጉት አንዳቸዉ ከድንበር ማዶ ያለዉን የሌላቸዉን ሥርዓት ለማዳከም ነዉ።»

ምስል AP

ኤርትራዉያን ወጣቶች በብዛት ለመሰደዳቸዉ አስመራ ሲአይ ኤን አስቀድማ አዲስ አበባን አስከትላ ትወቅሳለች።ኤርትራ በ2009 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ዓለም አቀፍ ማዕቀብ ሲጣልባት-ባንደኛ ደረጃ ተወቃሽዋ ኢትዮጵያ ነበረች።በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ አምባሳደር ግርማ አስምሮም በቀደም ደገሙትም።

የኢትዮ-ኤርትራ እስካሁን ያልተፈታዉ «ችግር» ገለልተኛ የተባለዉ ዓለም አቀፍ ኮሚሽን በወሰነዉ መሠረት ኢትዮጵያ ለኤርትራ የሚገባትን መሬት አለማስረከቧ ነዉ።ይሁንና ሁለቱ መንግሥታት ለመጣላት ሌላም ምክንያት አላጡም።

ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር በሚያዋስነዉ ድንበር ሐገር ጎብኚዎች ወይም ያገሬዉ ነዋሪዎች ከታገቱ ፤ከተገደሉ ወይም ከተጉላሉ አዲስ አበባ-አስመራን ለማዉገዝ፤ ለመዛት ማስፈራራት አትዘገየም።ኢትዮጵያ ዉስጥ የቦምብ አደጋ ከደረሰ ወይም ሊደርስ ነበር ከተባለ የኢትዮጵያ መንግሥት ማንን እንደሚወቅስ ወይም እንደሚያወግዝ ለማወቅ የመንግስት መግለጫ እስከሚወጣ መጠበቅ አያስፈልግም።

በቅርቡ በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳዉ ተቃዉሞም የሁለቱን መንግሥታት የአስራ-ስድስት ዓመታት እንኪያ ሠላንቲያ ለማጦዝ ተጨማሪ ምክንያት ነዉ-የሆነዉ።

የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር አቶ ጌታቸዉ ረዳ።የኤርትራ መንግሥትም ከኢትዮጵያ የተሰነዘረበትን ዉግዘት እንደተለመደዉ አዉግዟል።የሐገሪቱ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰዉ ተቃዉሞ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የሚከተለዉ የ«ከፋፍለሕ ግዛ» ሥልት ዉጤት ነዉ።

«ዉሸት ቢደጋገም እዉነት አይሆንም» በሚል ርዕሥ የተሠራጨዉ መግለጫ እንደሚለዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን የሚያወግዘዉ በሐገሩ ዉስጥ ያለዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ ዉጪያዊ መልክና ባሕሪ ለመስጠት ነዉ።ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ-ግብረዓብም ወቀሳዉን መሠረተ ቢስ ይሉታል።

ምስል AP

«ሥለ ጉዳዩ ይፋ መግለጫ ሰጥተናል።ይሕ ወቀሳ በመረጃ ያልተደረገፈና መሠረተ-ቢስ ነዉ።እንደሚመስለኝ ሥርዓቱ የሐገር ዉስጥ ችግሩን ዉጪያዊu ለማድረግ እየሞከረ ነዉ።»የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሥ ዜናዊ በ2005 ማብቂያ ቦንን በጎበኙበት ወቅት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸዉ ጥያቄ-ሲመልሱ ሁለት ዓመት ያዋጋዉን ጦርነት አላስፈላጊ እና ደደብ በማለት ኮንነዉት ነበር።

ጦርነቱ ራሱ ወይም የጦርነቱ አዋጊዎች «ደደብ» ከነበሩ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች ሕይወታቸዉን የገበሩበት ምክንያት የሁለቱም ሐገራት ሕዝብ በግልፅ ሊያዉቀዉ፤ አላስፈላጊ ጦርነት አቀጣጣዮችም ሊጠየቁ በተገባ ነበር።

ሁለቱ መንግሥታት ለጦርነቱ መጫር አንዳቸዉ ሌላቸዉን ከመወንጀል ባለፍ የየሕዝባቸዉን ይቅርታ ለማግኘትም ሆነ ሐላፊነቱን ለመዉሰድ እስካሁን አልደፈሩም።በጦርነቱ የተገደለና የቆሠለዉ ሰዉ ትክክለኛ ቁጥር፤ የተፈናቀለዉ ሕዝብ ብዛት፤ የጠፋዉ ሐብት ንብረት ትክክለኛ መጠን ጦርነቱ ቆመ በተባለ ባስራ-ስድስተኛ ዓመቱ ዘንድሮም ለሁለቱም ሐገራት ሕዝብ ሚስጥር ነዉ።

ጦርነቱ ከድንበር ዉዝግብ ይልቅ ምጣኔ ሐብታዊ፤ ከምጣኔ ሐብታዊነቱ በላይ አካባቢዉን በበላይነት የመቆጣጠር ፉክክር፤ ከዚም ይበልጥ የሁለቱ ገዢ ፓርቲዎች ወይም መሪዎች ጠብ የወለደዉ እንደሆነ በሠፊዉ ይታመናል።በተለይ ምዕራባዉያን የፖለቲካ ተንታኞች፤ ጦርነቱ በይፋ መቆሙ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ የቀጠለዉ ግጭት፤ ቁርቁስ፤ ዛቻ የሚቆመዉ ከሁለቱ ገዢዎች አንዳቸዉ ወይም ሁለቱ ከሥልጣን ሲለዩ ወይም ሲወገዱ ነዉ የሚል እምነት ነበራቸዉ።2012 አቶ መለስ ሞቱ።የተለወጠ ነገር የለም።

«ጠቅላይ ሚንስትር መለሥ ዜናዊ ከሞቱ በኋላ ትልቅ ተስፋ ነበር።ከሁለቱ ዋና ዋና ተዋኞች አንዱ ከትዕይንቱ ሲለዩ የሁለቱን ሐገራት ግንኙነት እንደገና ይጤናል የሚል ግምት ነበር።ምክንያቱም የጠንካራዉ ፖለቲከኛ ሞት ብዙ ቢያሳዝንም በሁለቱ መሪዎች በመለስና በኢሳያስ መካከል ከነሱም በላይ በሁለቱ (የቀድሞ) አማፂ ቡድናት፤ በTPLF እና በEPLF መካከል ቅራኔ ሥለነበር፤ ቢያንስ አንዱ ተዋኝ ከመድረኩ ሲለቅ አዲስ ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ግምት ነበር።ይሕ ግን አልሆነም።እንዲያዉም አዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት አስመራ ላይ ይበልጥ ጠንካራ ነዉ-የሆነዉ።»

ቁርቁስ፤ ግጭት መወጋገዙ ከቀድሞዉ ጠቅላይ ሚንስትር ሞት በኋላም መቀጠሉ የሑለቱን ሐገራት ሕዝቦች በየጊዜዉ እንዳሸማቀቀ ነዉ። ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ኤርትራ በተለይ የሶማሊያዉን አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አል-ሸባብን ትረዳለች፤ ጅቡቲን ወርራለች የሚል ወቀሳ ከተሰነዘረባት በኋላ ከአብዛኛዉ ዓለም ተገልላ ነበር።በማዕቀብ ተቀጥታለችም።

ምስል Reuters/T. Negeri

የኤርትራ ወጣቶች በብዛት ወደ አዉሮጳ መግባታቸዉ እና ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ አካባቢ የአረብ ሐገራት ጦር በየመኑ የርስ በርስ ጦርነት መነከሩ፤ ኤርትራን አርቋት የነበረዉ ዓለም ዳግም እንዲቀርባት አስገድዶታል።የኤርትራ መንግስት ለሚሰደዱ ወጣቶቹ «የሥራ ዕድል» እንዲፈጥር በሚል ሰበብ የአዉሮጳ ሕብረት «ጨቋኝ» ለሚለዉ የኤርትራ መንግስት የ200 ሚሊዮን ዩሮ ርዳታ ለመስጠት ተፈራርሟል።

የየመንን አማፂ ቡድን የሚወጉት ሳዑዲ አረቢያና ተከታዮችዋ ደግሞ ኤርትራን የስንቅና ትጥቅ ማደራጃና ማቀበያ ለማድረግ አቅደዋል።ኤርትራ ከየመን አርባ ኪሎ ሜትር ብትርቅ ነዉ።ኤርትራም አጋጣሚዉን መጠቀም የፈለገች ይመስላል።ከእስር ቤቶቿ ቢያንስ አንዱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰራተኞች እንዲጎበኙ ፈቅዳለች።የተጣለባት ማዕቀብ እንዲነሳ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ምክር ቤትን ጠይቃለችም።

የኤርትራ መንግስት በልማዱ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ ከሚባለዉ ሐያል-ሐብታም ሐይል ጋር መቀራረቡ፤ ምዕራባዉያን ተንታኞች እንደሚገምቱት ለአዲስ አበባ መሪዎች፤ በአዲስ አበቦች ቋንቋ «የሚመች» አይደለም።

ምስል Reuters/T. Negeri

የኢትዮጵያ መንግሥት ሰሞኑን ኤርትራን ደጋግሞ ማዉገዝ-ማስጠንቀቁም ምናልባት የማይመቸዉን የአስመራና የሐያላኑን መቀራረብ ለማደናቀፍ ወይም የትኩረት አቅጣጫን ከኦሮሚያዉ ዓይነት ግጭትና ሁከት ለማስቀየስ አልሞ ሊሆን ይችላል።ባይሆን እንኳ ጋዜጠኛ ሮንግ እንዳለችዉ የዉግዘት፤ ዛቻዉ መደጋገም ኢትዮጵያ ምናልባት ወታደራዊ ጡንቻዋን ልትሞክር ትችላለች ማሰኘቱ አልቀረም።ለግማሽ ምዕተ-ዓመት ያክል ከጦርነት-ግጭት እልቂት-ስደት ላልተላቀቀዉ ለሁለቱ ሐገራት ሕዝብ ሌላ ስጋት።እስከመቼ አይታወቅም።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW