1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትና የወደብ ጥያቄ

ሰኞ፣ ጥቅምት 19 2016

ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ ኖቤል ያሸለመ፣ ቀለበት ያሳሰረዉ የአዲስ አበባና የአስመራ መሪዎች ፍቅር ድምፃዊዉ እንዳለዉ «ትናንት ዛሬ» አይደለም ያሰኝ ይዟል።በፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ ዩሱፍ ያሲን አገላለፅ የሁለቱ መሪዎች «እፍእፍ» ያለ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሁለቱ ሐገራት ህዝብ ተስፋም መክኗል።

የሁለቱ መሪዎች ወዳጅነት በጠበቀበት ወቅት
ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ-አስመራምስል Yemane G. Meskel/Minister of Information

ማሕደረ ዜና፣ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት

This browser does not support the audio element.

የሰሜን ኢትዮጵያዉን ጦርነት ያስቆመዉ የፕሪቶሪያዉ «ግጭት የማቆም» ስምምነት የተፈረመበት አንድኛ ዓመት የፊታችን ሐሙስ ይዘከራል።ስምምነቱ የተፈለገዉን ያክል-ሆነም አልሆነ ሠላም ማስፈኑ እስካሁን አላጠያየቀም።በጦርነቱ ወቅት «በዜጎች ደም-አጥንት የተለሰነ» የሚባል ዓይነት ወዳጅነት መሥርተዉ የነበሩት የአዲስ አበባና የአስመራ መሪዎች ፍቅር ባንፃሩ ተራዉን ለጠብ የለቀቀ መስሏል።የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሰሞኑን ስለ ወደብ አስፈላጊነት የሰጡት ማብራሪያ ደግሞ የአስመራ መሪዎችን ይበልጥ አስከፍቷል።ሰሞኑን ከቀይ ባሕር ጥግ አሰብ እስከ ዛላንበሳ ጠርዝ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ያዩ እንደሚሉት የአስመራ-አዲስ አበባ መሪዎች ሕዝባቸዉን ዳግም ስለጦርነት «ሳያዘምሩት» አይቀርም የሚል ስጋት አጭሯል።ሥጋቱ መነሻ፣ ጥቂት ምክንያቶቹ ማጣቃሻችን ነዉ።

ከ2010 አጋማሽ ጀምሮ ኖቤል ያሸለመ፣ ቀለበት ያሳሰረዉየአዲስ አበባና የአስመራ መሪዎች ፍቅር  ድምፃዊዉ እንዳለዉ «ትናንት ዛሬ» አይደለም ያሰኝ ይዟል።በፖለቲካ ተንታኝና ደራሲ ዩሱፍ ያሲን አገላለፅ የሁለቱ መሪዎች «እፍእፍ» ያለ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሁለቱ ሐገራት ህዝብ ተስፋም መክኗል።

«መጀመሪያ ላይ የነበረዉ «እፍእፍ» የሚያሰኝ ፍቅርና «ተዘወሪ መኪና» ተብሎ አስመራና አዲስ አበባ  የመመላለሱ ጉዳይ ያለቀ ይመስላል። በሁለቱ ፕሬዝደንቶች መሐል የነበረዉ ብቻ ሳይሆን ያኔ ህዝቡ ተስፋ አድርጎ የነበረዉ ብዙ ነገሮች፣ የሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚባለዉም ነገር ያለ አይመስልም»      

ሌላዉ የአፍሪቃ ቀንድና የመካከለኛዉ ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝና ፀሐፊ አብዱረሕማን ሰዒድ እንደሚሉት አምና አጋማሽ ካይሮ ላይ የሱዳን አጎራባች ሐገራት መሪዎች ባደረጉት ጉባኤና ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ በተደረገዉ የብሪክስ ጉባኤ ላይ ሁለቱ መሪዎች መገናኘታቸዉ እያሽቆለቆለ የመጣዉን ግንኙነት ለመጠጋገን ይረዳል ተብሎ ነበር።ሁለቱም አልሆነም።

«ግንኙነታቸዉ የሻከረ ነዉ የሚመስለዉ።የሱዳን ጎረቤት ሐገራት መሪዎች ካይሮ ዉስጥ ባደረጉት ጉባኤ ላይ ሁለቱ መሪዎች ከተገናኙ በኋላ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አዲስ አበባን ይጎበኛሉ የሚል ቃል ከጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አማካሪ ከሪድዋን ሁሴይን ተሰምቶ ነበር-----»

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድና ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስምምነት ሲፈራራሙምስል Yemane G. Meskel

ተነገረ፣ ተስፋ ተደረገ፣ ምናልባት ታቀደ፣ ብቻ ቀረ።ሰሞኑን ደግሞ የቀዘቀዘዉ  ግንኙነትን የማደስ ተስፋዉ ርቆ ሁለቱም ወገኖች በየድንበር ግዛቶቻቸዉ አዳዲስ ጦር ኃይል እያሰፈሩ መሆናቸዉ እየተነገረ ነዉ።ገለልተኛ ወገኖች አላረጋገጡም።ይሁንና ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተለዉ የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚ ፓርቲ የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ (EANC-በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና ቃል አቀባይ ዓሊ መሐመድ ዑመርም በድንበር አካባቢ አዲስ ጦር መስፈሩንና ወታደራዊ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚጠቁም መረጃ ደርሷቸዋል።

«አሰብ አካባቢ ኃይለኛ የጦር ክምችት አለ።ከባድ መሳሪዎችም እየተጠጉ ነዉ።አሰብ አዉሮፕላን ማረፊያ  የዓየር ኃይል  እንቅስቃሴዎች በጣም ይታያሉ።በኢትዮጵያ በኩል በተለይ በአፋር አካባቢ  ያየነዉ ነገር የለም።በትግራይ ክልል ግን በተለይ በዛላንበሳ ግንባር ሁለቱም ሐገራት ወታደሮቻቸዉንና ከባድ መሳሪዎችን እያስጠጉ ነዉ የሚል መረጃ ደርሶናል።»

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ባለፈዉ ጥቅምት መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ማንሳት አለባት የሚል ይዘት ያለዉ ንግግር ማድረጋቸዉ አንዳዶች በሐገር ዉስጥ ላለዉ ቀዉስ የትኩረት አቅጣጫ ማስቀየሪያ፣ሌሎች የሕዝብን ስሜት መኮርኮሪያ፣ የመንግስት ደጋፊዎች ተገቢ ጥያቄ፣ ሌሎች ግን  የአስመራ-አዲስ አበባ መሪዎች ቅራኔ የመካረሩ አብነት እያሉ መከራከራቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።

የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድን መግለጫ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲም አጥብቀዉ ተቃዉመዉታል።ሐሳቡን ከተቃወሙት አንዱ የኤርትራ አፋር ብሔራዊ ጉባኤ አንዱ ነዉ።ቃል አቀባይ ዓሊ መሐመድ ዑመር እንዳሉት ግን ተቃዉሟቸዉ የወደብ ባለቤትነትን እንጂ ወደብን መጠቀምን ዓይደለም።ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይም ባለፈዉ ሐሙስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን ሲከበር ባደረጉት ንግግር ተቃዉሞዉን ለማለዘብ ያለመ መልዕክት አስተላልፈዋል።

  «ኢትዮጵያ ባንዳድ ጉዳዮች ዉይይት ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ስታነሳ፣ ወረራ ሊካሔድ ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለ ይደመጣል------ኢትዮጵያ  በኃይልና በወረራ ለማሳካት የምትፈልገዉ አንዳች ነገር የለም።»                                  

የኤርትራን ቁጣ ያረገበ ግን አይመስልም።የአስመራ መንግስትን የሚደግፉ የሚመስሉ አንዳድ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ኢትዮጵያን በተለይም ጠቅላይ ሚንስትሩን የሚያጣጥል አስተያየት እያሰራጩ ነዉ።የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚያምኑት የወደቡ ጥያቄ ጠቡን አካሮት ይሆናል እንጂ የአስመራ አዲስ አበቦች ልዩነት መነሻ እንዳልሆነ ሁሉ የጠቅላይ ሚንስትሩ የአደባባይ ማስተባበያም ልዩነት ማጥበቢያ ሊሆን አይችልም።አልቻለምም።

አቶ አብዱረሕማን ሰዒድ እንደሚሉት ልዩነት የታየዉ ከፕሪቶሪያዉ ስምምነት ጀምሮ ነዉ።ፕሬዝደንት ኢሳያስ እንደተመኙና እንደተናገሩት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ከአካባቢዉ ፖለቲካ ሙሉ በሙሉ አለመዉጣቱና በድርድሩ ኤርትራ መገለሏ የአስመራዉን ገዢ አስቆጥቷል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቀን አዲስ አበባ ዉስጥ ሲከበርምስል Solomon Muche/DW

የጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ መንግስት የአማራ ኃይላትን ትጥቅ ማስፈታት መጀመሩና የተከተለዉ ግጭት አቶ አብዱረሕማን እንደሚሉት ለፕሬዝደንት ኢሳያስ «አደገኛ ነዉ»

«ከጥቂት ጊዜ ወዲሕ ደግሞ የአማራ {ታጣቂዎችን} ትጥቅ ማስፈታትና ማጥቃትም ጀመሩ።ይኽ ደግሞ ለፕሬዝደንት ኢሳያስ እንደ አደገኛ ነገር ሆኖ ነዉ የሚታየዉ።ምክንያቱም  አማሮቹ ታማኝ ተባባሪ ተብለዉ ጦርነቱ ላይ የተሳተፉ ነበሩ።ከዚያም በላይ የወልቃይት----»

የፕሪቶሪያዉ ስምምነት ከመፈረሙ በፊት ጀምሮ የኤርትራ መንግስት የአማራ ታጣቂዎችን ይረዳል የሚል ጥርጣሬና መላምት ሲነገር ነበር።የፕሪቶሪያዉ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ደግሞ የኤርትራ መንግስት የአዲስ አበባ አስተዳደርን የሚቃወሙ የአማራ ታጣቂዎችን በሰፊዉ መርዳቱ ይነገራል።ሥለ ርዳታዉ ዓይነትና መጠን ግን እስካሁን በተጨባጭ መረጃ የተረጋገጠ ዘገባ አላየንም።

አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የአዲስ አበባና የአስመራ ገዢዎች ፍቅር በጠብ ከተቀየረ የኃይል አሰላለፉም መቀየሩ ሊያስደንቅ አይገባም።የጠቡም ሆነ የአዲሱ የኃይል አሰላለፍ ወይም ሥጋት መሰረታዊ ምክንያት ግን አቶ ዩሱፍ እንደሚሉት ወዳጅነቱ የሁለቱ መሪዎች ሚስጥራዊ ስምምነት እንጂ የሁለቱ ህዝቦች አለመሆኑ ነዉ።

በፕሪቶሪያዉ ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዉጪ ያሉ የኤርትራ ጦርና የአማራ ክልል ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል መዉጣት አለባቸዉ።ይሁንና የኤርትራ ጦር  ዛላንበሳና አካባቢዉን፣ ኢሮብ አካባቢ፣ የሺራሮ አዋሳኝ አካባቢዎችን አሁንም እንደተቆጣጠረ ነዉ።

የትግራይና የአማራ ፖለቲከኞች በወልቃይት ጠገዴ (ፀገዴ) ግዛት የይገባኛል ጥያቄ እንደተወዛገቡ ነዉ።ምዕራብ ኦሮሚያ ዉስጥ በሸመቁ ታጣቂዎችና በመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች መካከል የሚደረገዉ ግጭት፣ በዘር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት፣ ለስድስተኛ ዓመት እንደቀጠለ ነዉ።

አማራ ክልል ዉስጥ በፋኖና በመንግስት ኃይላት መካከል የሚያካሔደዉ ዉጊያም ብዙ ሕይወት፣ሐብት ንብረት እያጠፋ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ፣ ሥራና እንቅስቃሴም እያወከ ነዉ።በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ወይም ክልሎች ቀጥታ ግጭትና ወጊያ ባይደረግም ሰዎች ይታገቱ፣ ሐብት ንብረታቸዉ ይዘረፍባቸዋል።

የየሥራ አጡ ቁጥር ብዛት፣ ኑሮዉ ዉድነት፣ ሙስና፣ አጭበርባሪነት ለደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ገላጭ አማርኛ ቃላት ካላቸዉ ቢነግሩን ጥሩ ነዉ።የዞንና የወረዳ መስተዳድሮች ለመንግስት ሠራተኞቻዉ ደሞዝ መክፈል ተስኗቸዋል።በዚሕ መሐል የሌላ ጦርነት ሥጋት በርግጥ የጤና ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

ሒሩት መለስ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW