1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ኤርትራ ጠብና የደቡብ ሱዳን የሽምግልና ሐሳብ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 15 2005

አስገራሚዉ ግን ጥሩዉ ሐሳብ የተሰማዉ የሁለቱ ሐገራት ዉዝግብ ጦርነትም-ሠላምም የለም ከሚለዉ ይልቅ፥ ጦርነት የለም። ሠላምም የለም። ግጭት ግን አለ ወደሚለዉ በናበረበት ወቅት መሆኑ ነዉ...የሁለቱን ሐገራት ባለሥልጣናት ማረጋገጪያ ለማግኘት ሞክረን ነበር።አልተሳካልንም።

ምስል AP Graphics/DW

5 10 12


ደቡብ ሱዳን ረጅም ዓመታት ያስቆጠረዉን የኢትጵያና የኤርትራን ጠብ ለማስወገድ ሽምግልና መግባት እንደምትፈልግ ማስታወቋ ለአካባቢዉ ሠላም ጥሩ እርምጃ መሆኑን አንድ የፖለቲካ ተንታኝ አስታወቁ።ቻተም ሐዉስ የተሰኘዉ የብሪታንያ የጥናት ተቋም የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳይ አጥኚ አሕመድ ሱሌይማን እንደሚሉት የደቡብ ሱዳን ሐሳብ አስገራሚ፥ ግን የሚደገፍ እና ጥሩ ነዉ።አዲሲቱ፥ እራስዋ ገና ከድርድር ያልወጣችዉ፥ ደካማ ሐገር ሥር የሰደዉን የሁለቱን ሐገራት ጠብ ቁርቁስ ለማስወገድ የማደራደር አቅም ማግኘቷን ተንታኙ ይጠራጠራሉ።ነጋሽ መሐመድ የፖለቲካ አጥኚ አሕመድ ሱሌይማንን አነጋግሮ የሚከተለዉን ዘገባ አጠናቅሯል።

የደቡብ ሱዳን የካቢኔ ጉዳዮች ሚንስትር ዴንግ አሎር ትናንት ያሉት እየጋመ፥ ሲቀዘቅዝ፥ እየቀዘቀዘ ሲግም-የታዳጊ ወጣት እድሜ ያስቆጠረዉን ጦርነት፥ ግጭት፥ ዉዝግብን ለሚከታተለዉ ታዛቢ ሁሉ ዱብ ዕዳ አይነት ነዉ የሆነዉ።ድንገተኛ እዉነት።

የማደራደር ሐሳቡ ከአዲሲቱ ነፃ ሐገር መምጣቱ ደግሞ ድንገተኛዉን እዉነት፥ የአፍሪቃ ቀንድ የፖለቲካ አጥኚ አሕመድ ሱሌይማን እንደሚሉት አስገራሚ አድርጎታል።

«በጣም አስገራሚ እመርታ ነዉ።ያዉ እንደሚታወቀዉ መጀመሪያ ማለት የሚቻለዉ፥ ረጅም ጊዜ ካስቆጠሩት የአፍሪቃ ቀንድ ግጭቶች አንዱ መፍትሔ ያሻዋል መባሉ ነዉ።እና ወደ መፍትሔ የሚያመራ ተነሳሽነት መታየቱ ጥሩ ነዉ።ደቡብ ሱዳን ይሕን ይሕን ማድረግ መቻል-አለመቻሏ ግን ወደፊት የሚታይ ነዉ።»

አስገራሚዉ ግን ጥሩዉ ሐሳብ የተሰማዉ የሁለቱ ሐገራት ዉዝግብ ጦርነትም-ሠላምም የለም ከሚለዉ ይልቅ፥ ጦርነት የለም። ሠላምም የለም። ግጭት ግን አለ ወደሚለዉ በናበረበት ወቅት መሆኑ ነዉ።

«እንደሚመስለኝ ማለቴ፥ ጥሩ ምልክት ነዉ።በቅርብ ወራት ግን መጥፎ ምልክቶችን አይተናል።ኢትዮጵያ ኤርትራ ድንበርን ጥሳ መግባቷ፥ በድንበር አካባቢ በዉጪ ሐገር ጎብኚዎች ላይ የተፈፀመዉ ጥቃትና ኢትዮጵያ ለጥቃቱ ኤርትራን ተጠያቂ ማድረጓ።እና በሁለቱ ሐገራት መካካል የነገሮች መባባስን ነዉ ያየነዉ።»

የደቡብ ሱዳኑ ሚንስትር አሎር ግን ሮይተር ዜና አገልግሎት እንደጠቀሰዉ የጁባ መሪዎች መጥፎዉን ለመለወጥ፥ ከልብ አስበዉበታል ባይ ናቸዉ።የሁለቱን ባላንጦች ይሁንታም አግኝተዋል። «አረንጓዴ መብራት» ብለዉታል አሎር። ጁባዎች፥ ለአዲስ አበቦችም፥ ለአስመሮችም ወዳጅ መሆናቸዉ ለሐሳብ፥ ጥረት ሙከራቸዉ ስኬት ጥሩ ምርኩዝ ሊሆን ችላል።ግን በምን አቅም።

«ደቡብ ሱዳን እራሷ ገና እየተደራደረች ነዉ።ለጊዜዉም ቢሆን የምጣኔ ሐብት ችግር አለባት፥ በዚሕ ላይ ገና በጣም አዲስ ሐገር ነች።ደቡብ ሱዳን ከሰሜን ጋር የምትደራደረዉ ባብዛኛዉ አዲስ አበባ ዉስጥ መሆኑም ሊጤን ይገባዋል።»

ዓለም አቀፉ የድንበር አካላይ ኮሚሽ የጠቡ ዋና መነሻ የተባለችዉን ባድመ የኤርትራ ግዛት አካል መሆንዋን ከወሰነ-አስር ዓመት አለፈዉ።ባድመ ዛሬም በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ነች።የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በየጊዜዉ እንደሚሉት ልዩነቱ ድርድር መፍታት አለበት።ኤርትራ ደግሞ ዉሳኔዉ ሳይከበር ድርድር የለም ባይናት።

የኢትዮጵያ መሪ መለወጥ፥ የተደራደሩ ጥያቄዉ ከሁለቱ ሐገራት ወዳጅ ሐገር መመጭት፥ የአስመራን አቋም ያስለወጥ ይሆን? የፖለቲካ አዋቂዉ መልስ-ማረጋገጪያ እስኪገኝ አይ አዎ አይነት ነዉ።

«የምናዉቀዉ ኤርትራ እንደመገለል ብላለች።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የማዕቀብ ኢላማም ሆናለች።ይሕን መሠሉን ዓለም አቀፍ ገፅታዋን ለማሻሻል ባለፉት ዓመታት እየጣረች ነዉ።በሁለት ሺሕ አስራ አንድ የአፍሪቃ ሕብረት ኤምባሲዋን ዳግም ከፍታለች።የማዕድኗ መስክ ማደግና የገቢዉ መጠናከር መገለሏን እየሸፈነዉ ነዉ።ይሕ ኤርትራን በትንሹም ቢሆን ወደ ድርድር እንድታዘነብል ያደርጋት ይሆናል።ያም ሆኖ እንዳልኩት ማረጋገጪያ ሳይገኝ መተንበይ ከባድ ነዉ።»

የሁለቱን ሐገራት ባለሥልጣናት ማረጋገጪያ ለማግኘት ሞክረን ነበር።አልተሳካልንም።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ

ምስል AP
ምስል CC-BY-SA- World Economic Forum
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW