የኢትዮ- ጀርመን የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫል
ቅዳሜ፣ ግንቦት 11 2010የዘንድሮውን የፍራንክፈርቱ የኢትዮ- ጀርመን የስፖርት እና የባህል ፌስቲቫል ልዩ የሚያደርገው ስፖርታዊ እንቅስቃሴውን የፍራንክፈርቱ ኢትዮ-አዲስ የስፖርት ክለብ ምግብ እና መስተንግዶውን ለኢትዮጵያውያን ማሕበራዊ እንቅስቃሴ ልዩ ልዩ ድጋፍ የሚያበረክተው አዳብና የኢትዮጵያ የባሕል ሬስቶራንት እንዲሁም የመዝናኛውን ጉዳይ ለረጅም ዓመታት ከሃገር ቤት የሙዚቃ ባለሙያዎችን እዚሁ ጀርመን እያስመጡ የመድረክ ዝግጅቶችን በማቅረብ የሚታወቁት አቶ አልያስ የማነ በጋራ ያዘጋጁት መሆኑ ነው።
ፌስቲቫሉ ከተዘጋጀበት ፍራንክፈርት ሬብሽቶክ ከሚገኘው የስፖርት እና የመዝናኛ ማዕከል ለመታደም በግልም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ከጀርመን የተለያዩ ከተሞች ከአጎራባች የአውሮፓ ሃገራት ጭምር የመጡ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ለማየት ችለናል። በተለይ በልዩ ልዩ የብሔር ብሔረሰቦች እንዲሁም በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተጠለፉ የባህል አልባሳትን የለበሱ ኢትዮጵውያን እና የስፖርት ክለባቱ ደጋፊዎች ጭፈራም በስፍራው የሃገር ቤትን ድባብ ከመፍጠር ሌላ ለዝግጅቱም ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል ጭፈራ እና ሆታውም ልዩ ነበር።የዝግጅቱ ዓላማ እና አጠቃላይ መርሃ-ግብር በፍራንክፈርቱ የኢትዮ አዲስ ስፖርት ክለብ አመራሮች ከተገለጸ በኋላ ከከለን የኢትዮጵያን ባሕል እና ውዝዋዜ በሙዚቃ ለማድመቅ በስታዲየሙ የታደሙ የሕጻናት የእግር ኳስ ውድድር ከስዊትዘርላንድ ዙሪክ በተጋባዥነት የመጣ የስፖርት ክለብን ጨምሮ በጥቅሉ ከመላው ጀርመን ደጋፊዎቻቸውን ይዘው ውድድሩን የሚካፈሉ 15 የእግርኳስ ቡድኖች የማጣሪያ ውድድር በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በስታድየሙ ዙሪያ በተጣሉ ትናንሽ የድንኳን ዳሶች ውስጥ የሃገር ባሕል ምግቦችን እና መጠጦችን እንዲሁም ልዩ ልዩ ምርቶችን የሚሸጡ እና የሚያስተዋውቁ ኢትዮጵያውያን እና ለሕጻናት የሚሆኑ ልዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች መኖራቸውንም አስተውለናል። ከበዓሉ ታዳሚዎች ያነጋገርናቸው ነበሩ።
ይህ ዓይነቱ ዝግጅት በውጭው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን አስወግደው ሃገራዊ አንድነታቸን ብሎም አብሮ ተረዳድቶ የመኖር በጎ ልማዳቸውን እንዲያጠናክሩ ዘመን ተሻጋሪ ባሕል ቅርስ እና ወጋቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም የሚኖሩበትን ሃገር ሕግ እና ሥርዓት አክብረው እንዲኖሩ ከማድረጉም ሌላ ከደባል ሱሶች ርቀው በስፖርታዊ ጨዋነት እንዲታነጹም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተወስቷል። ለረጅም ዘመን በስራ እና በቦታ እርቀት የተለያዩ ወዳጆችን በማቀራረብ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውንም ኢትዮጵያውያን በማበረታታትና የደከም አዕምሮንም በማነቃቃት በኩልም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ይታመናል።በተለይም በውጭው ዓለም ለሚወለዱ ሕጻናት ታሪክ እና ማንነታቸውን እንዲረዱ በማድረግ ረገድም ቢሆን የማይናቅ አስተዋጽዖም እንደሚኖረው አስተያየት የሰጡን የፌስቲቫሉ ታዳሚዎች ያስረዳሉ። ዝግጅቱ ገና ከአጀማመሩ የተዋጣለት ነበር። ብዙ ሃላፊነትን የሚጠይቀውን እንዲህ ዓይነቱን እንቅስቃሴ በጋራ ተከፋፍሎ እና ተግባብቶ መስራቱ የስኬቱ መሰረት ነው ይላሉ አዘጋጆቹ።
ፍራንክፈርት ሬብሽቶክ በሚገኘው የሥፖርት ማዕከል ስታዲየም ዛሬ የተጀመረው የኢትዮ-ጀርመን የስፖርት እና የባሕል ፌስቲቫል በነገው ዕለት ይጠናቀቃል:: በመዝጊያው ሥነ-ሥርዓትም ላይ የዋንጫ እና የደረጃ ጨዋታዎች የኢትዮጵያን ባሕል የሚያስተዋውቁ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ጨምሮ ተጋባዥ ድምጻዊ ምዕራፍ አሰፋ በሙዚቃ ባንድ እና ታዋቂ ዲጄዎች ታጅቦ የሙዚቃ ሥራዎቹን ለበአሉ ታዳሚዎች የሚያቀርብበት መሰናዶ እንደሚኖር የፌስቲቫሉ አዘጋጆች ገልጸውልናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአውሮፓ ደረጃ 16ተኛው የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባሕል ፌስቲቫል በጀርመኗ የሽቱትጋርት ከተማ ከኦገስት 1 እስከ ኦገስት 4 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ከአውሮፓ የስፖርት ፌዴሬሽን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
እንዳልካቸው ፈቃደ
ተስፋለም ወልደየስ