የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ስምምነት መፍረስ እና የሰራተኞች እጣ ፈንታ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 22 2014
የኢትዮ - ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት ይተዳደርበት የነበረው የሁለት ሃገራት ሕጋዊ ስምምነት ፈርሶ በድሬዳዋ አስተዳደር መግባቱን ተከትሎ ሠራተኞች ለአስተዳደሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን አንስተዋል። የድርጅቱ ሠራተኞች ሰሞኑን ጥያቄያቸውን ያነሱት የሚንስትሮች ምክር ቤት በድርጅቱ ስር ያሉ ቋሚ ሠራተኞች እና ንብረት በድሬዳዋ አስተዳደር ስር እንዲተዳደር ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ድርጅቱ ከሠራተኞቹ ጋር ባደረገው ውይይት ነው። ሠራተኞች ለዘመናት በበረሀ ንዳድ እና ቃጠሎ ሲንገላቱ የበረሃ አበል ሳይሰጣቸው መቆየታቸውንም በምሬት ተናግረዋል። እጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነም ግራ መጋባታቸውን ገልጠዋል። የድሬዳዋ አስተዳደር፦ «የፈረሰው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የሚለው ስምምነቱ ነው እንጂ ድርጅቱ አልፈረሰም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የድሬዳዋው ወኪላችን መሣይ ተክየሰሞኑን ውይይት ተከታትሎት ነበር።
እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ወርሀዊ ደሞዝ ከማገልገል ባለፈ ፤ ለአስተዳደሩም ሆነ በአስተዳደሩ ውስጥ ለሚገኙ የፌደራል ተቋማት ሰራተኞች እየተከፈለ የሚገኘው የበረሀ አበል ክፍያ እየተከፈላቸው አለመሆኑም በጥያቄ ቀርቧል።
በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አደረጃጀቶች ስር እንዲገባ እየተደረገ ህልውናው በመክሰም ጫፍ ላይ በደረሰው የምድር ባቡር ድርጅት ዙርያ በቅርብ እየወጡ ባሉ ውሳኔዎች ሀሳብ ግር መሰኘታቸውን አንስተዋል።
ውሳኔው የቀደመ እሴታችንን ዛሬም በተሻለ መልኩ እንድንጠቀም ያስቻለ ታሪካዊ ውሳኔ ነው ያሉት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር ስለውሳኔው ምላሽ ሰተዋል።
በድርጅቱ ቦርድ ሰብሳቢነት የተመደቡት የመስተዳድሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው ለብዙዎች ስጋት የሆነው የመፈናቀል ሁኔታ አይኖርም ብለዋል።
መስተዳድሩ በኃላፊነት ለተረከባቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ከመጪው ግንቦት ወር ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የ20 በመቶ የበረሀ አበል ጭማሪ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል።
መሳይ ተክሉ
እሸቴ በቀለ