የኢትዮ - ፈረንሳይ ትብብር 125ኛ ዓመት በድሬደዋ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 17 2015
የኢትዮ - ፈረንሳይ ትብብር 125ኛ ዓመት ክብረ በዓል አከባበር አካል የሆነ ዝግጅት በድሬደዋ ተካሄደ። ከአንድ ምዕተ አመት በላይ የዘለቀው የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት በተለያዩ መስኮች እያደገ መምጣቱም ተገልጿል። ከምስረታዋ ጀምሮ የተለያዩ ፈረንሳያውያን አሻራ ባረፈባት ድሬደዋ በተካሄደው ዝግጅት በታሪካዊው የኢትዮ - ጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ ባለውለታ የሆነችው ፈረንሳይ ይህንን ሀብት ለቱሪዝም እና ሌሎች አገልግሎቶች ለማዋል በተጀመረው ጥረት የበኩሏን ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ ቀርቧል። በዝግጅቱ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬኒ ማሪሾ የቱሪዝም ሚንስትሯ ናሲሴ ጫሊ እና የድሬደዋ አስተዳደር ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።
በድሬደዋ በተካሄደው ዝግጅት ላይ የቱሪዝም ሚንስቴር ሚንስትር ናሲሴ ጫሊ የሁለቱን ሃገራት ትብብር 125ኛ ዓመት አስመልክቶ በታሪካዊው የባቡር ድርጅት ውስጥ የተሰናዳው ኤግዚቢሽን በዓሉን ከማብሰር ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፉ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ጠቅሰው ድርጅቱን ለቱሪዝም እና ሌሎች አገልግሎቶች ለማዋል ለተጀመረው ጥረት በፈረንሳይ በኩል ድጋፍ እንደሚደረግ እምነታቸውን ገልፀዋል። የፈረንሳይ መንግሥት ድሬደዋን ከምስረታዋ ጀምሮ በማዘመን ትልቅ አስተዋፅኦ ስለማበርከታቸው የተለያዩ ማሳያዎችን የጠቀሱት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሀር ወደፊትም ይኸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬኒ ማሪሾ በበኩላቸው ሁለቱ ሃገራት በተለያዩ መስኮች በርካታ ትብብር እንዳላቸው ጠቁመዋል። ለሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ትልቅ አሻራ በሆነው የቀድሞው የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ትስስሩን ከፍ ለማድረግ ያለውን የጋራ ፍላጎት እንደሚያሳይም ነው የጠቆሙት። «ይህ ኤግዚቢሽን በራሱ ፈረንሳይ እና ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርገውን ታሪካዊ ትስስር ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ፈጠራ ልማት እንዲሁም የህዝቡን ደህንነት ለማሻሻል ያለውን ከፍተኛ የጋራ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።» የሁለቱን ሃገራት ትብብር 125ኛ ዓመት አስመልክቶ የተለያዩ ዝግጅቶች ተከናውነዋል።
መሳይ ተክሉ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ