1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚዘጋው፣ የሚገደበው ኢንተርኔት እና ያስከተለው ኪሳራ

ሰኞ፣ ጥር 6 2016

ኢትጵጵያ ውስጥ ግጭቶች ሲከሰቱ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል ተዘግቶ ያውቃል ፣ አሁንም በአማራ ክልል አገልግሎቱ እንደተዘጋ ነው። መንግሥት ጉዳትን ለመቀነስ እና የሀገር ደህንነትን ለመጠበቅ በሚል ኢንተርኔትን ሲዘጋ ቢስተዋልም ጥናቶች "ኢንተርኔትን መዝጋት የሚነሱ አመጾችን በማስቀረት በኩል ጠቀሜታቸው እምብዛም " መሆኑ ተገልጿል።

የተቋረጠ ኢንተርኔት
በኢትዮጵያ የኢንተርኔት መቋረጥ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል ምስል Avishek Das/ZUMA Wire/picture-alliance

የኢንተርኔት መቋረጥ ያስከተለው ኪሳራ

This browser does not support the audio element.

ኢትጵጵያ ውስጥ ግጭቶች ሲከሰቱ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል ተዘግቶ ያውቃል ፣ አሁንም በአማራ ክልል አገልግሎቱ እንደተዘጋ ነው። መንግሥት በአመጽ ምክንያት የሚደርስን ጉዳት ለመቀነስ እና የሀገር ደህንነትን ለመጠበቅ በሚል ኢንተርኔትን ሲዘጋ ቢስተዋልም ጥናቶች "ኢንተርኔትን መዝጋት የሚነሱ አመጾችን በማስቀረት በኩል ጠቀሜታቸው እምብዛም ነው" የሚሉ መሆኑን የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት የተባለው ድርጅት በሳምንቱ መጨረሻ ባደረገው ውይይት ላይ ተገልጿል።

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሃ መኮንን በውይይቱ ወቅት "የኢንተርኔት መዘጋት ጉዳይ የተቋማት ልምድ የሆነበት ሁኔታ ላይ" መድረሳችን በስፋት ውይይት ተደርጎበታል ሲሉ ገልፀዋል። የሲቪክ ድርጅቶች ይህንን የሰብዓዊ መብት በተመለከተ ውትወታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው እና ምናልባትም ወደፊት ጉዳዩን በፍርድ ቤት ማየት ይቻል እንደሆንም ሰፊ ውይይት እንደተደረገበት ገልፀዋል። 

የኢንተርኔት መዘጋት አሳሳቢነት 

ከ 30 ሚሊየን በላይ ደርሷል የሚባለው እድገት ማሳየቱ የሚነገርለት የኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ሕዝብ ቁጥር ለአገልግሎቱ ያለን ፍላጎት መጨመር  ያሳያል። ይሁንና በሀገሪቱ በተደጋጋሚ ወቅት እና አካባቢ እየተቀየረ በሚከሰት ግጭቶች ሳቢያ የሚጣሉ የኢንተርኔት ገደቦች ሀሳብን በመግለጽ ነፃነት ረገድ ጉልህ ተፅዕኖ እያሳረፉ ይገኛል። የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ድርጅት ይህንኑ ችግር አስመልክቶ ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት አድርጓል።

የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪዎች ከፋኖ ታጣቂዎች በሚዋጉበት የአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧልምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

በዚሁ ውይይት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ሆን ተብሎ የሚደረግ የኢንተርኔት መዘጋት እያስከተለ ያለው ከፍተኛ ጫና እና ተጽእኖ መዳሰሱን የተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሃ መኮንን ገልፀዋል። "በእለት ተእለት ሕይወታችን መሠረታዊ የሆነ ጉዳይ እየተቆራረጠ፣ እየተዘጋ የተቋማት ልምድ የሆነበት ሁኔታ ላይ መድረሳችን በዚህም በኢኮኖሚው ዘርፍ ከ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ ያስከተለብን መሆኑን" በውይይታቸው እንዳነሱ ገልፀዋል።  

የኢንተርኔት መዘጋትን በፍርድ ቤት መከላከል ይቻል ይሆን ? 

ኢትዮጵያ ውስጥ የተጣለው የኢንተርኔት አገልግሎት ገደብ ከሥልጣኔ ውጪ ነው ሲል መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ኢትዮ- ቴሌኮም ከዚህ በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ባት መግለጹ አነጋጋሪ ገዳይ ነበር። አቶ አምሃ እንደሚሉት የኢንተርኔት መዘጋት ከሚያስከትለው የኢኮኖሚ ኪሳራ፣ የዝዜጎች የመብት መነፈግ ባሻገር የሀገርን ገጽታም በዚያው ልክ የሚጎዳ ነው። 

አለም አቀፉ የቪፒኤን ግምገማ ድረገጽ የኢትዮጵያ መንግሥት ባደረገው የኢንትፕርኔት አገልግሎት መዝጋት፣ ማቆራረጥ እና የማህበራዊ መገናኛ ዐውታሮች እገዳ ምክንያት በ2023 ብቻ ከፍተኛ የተባለ እስከ 1.59 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ኪሳራ ማድረሱን በቅርቡ ያወጣው ዘገባ ያመለክታል።

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አምሃ መኮንን በሳምንቱ መጨረሻ ባደረጉት ውይይት ተመራጭ ባይሆንም ጉዳዩን በፍርድ ቤት ማየት ይቻል እንደሆን ሀሳቦች መንሸራሸራቸውን ገልፀዋል። 

እኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ውጥረት ሲከሰት ፣ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ሲበረታ ፣ መንግሥት በመደበኛ የሕግ ሥርዓት ማስተዳደር የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር፣ የፈተና ሰሞን የብዙዎችን ሕይወት እንደሚያመሳቅል እያወቀ ኢንተርኔትን ሲዘጋ ተስተውሏል። አሁን ድረስ በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ኢንተርኔት የተዘጋ ሲሆን ከዚያ በፊት በትግራይ ክልል ጦርነት በነበረበት ጊዜ ለሁለት ዓመታት አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW