1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ያለው ግጭት፤ የኢኮኖሚ ማሻሻያው አተገባበር ስጋት

ረቡዕ፣ ሐምሌ 24 2016

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ መንግስት አሁን በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰላምና ጸጥታ ችግር ቅድሚያ ሰጥቶ ካልፈታው አላማውን በማሳካት በኩል ገቢራዊነቱ አጠራጣሪ ነው ተባለ።

ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ አበባ ፎቶ ከማኅደርምስል Seyoum Getu/DW

የኢኮኖሚ ማሻሻያው አተገባበር ስጋት

This browser does not support the audio element.

 

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ መንግስት አሁን በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የሰላምና ጸጥታ ችግር ቅድሚያ ሰጥቶ ካልፈታው አላማውን በማሳካት በኩል ገቢራዊነቱ አጠራጣሪ ነው ተባለ። ለዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አገሪቱ ወደ ውጪ የምትልከውን የወጪ ንግድ ምርት ከፍ በማድረግ የከፋውን አሁናዊ የንግድ ሚዛን መዛባት ማጥበብ የኢኮኖሚ ማሻሻያው ቁልፍ ትኩረት ነው ይላሉ። እንዲያም ሆኖ ይህንን ግብ ለማሳካት የኢንቨስትመንት እና ልማት ስጋት የሆነውን በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የሚስተዋለውን ግጭት እልባት መስጠት አዳጋች እንደሚሆን አምልክተዋል።

የማሻሻያው ግብ እና የጸጥታ ስጋት

በርካታ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ከሰሞኑ የመገበያያ ገንዘቧ የብር የመግዛት አቅምን እንደ ዶላር ካሉ የዓለም አቀፍ ሸርፍ አንጻር በ30 በመቶ ገደማ ያዳከመችው ለዓመታት መንግሥት ሲደራደርበት የነበረው የውጪ ብድር ማግኛ አስገዳጅ ሁኔታ በመፍጠሩ ነው ይላሉ። በዚህ የፖሊሲ ማሻሻያ አተገባበር ሂደት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ምርትና ምርታማነትን መጨመር የወጪ ንግድን ማሳደግ ደግሞ የፖሊሲው ቁልፍ ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል። ይሁንና አሁን በአገሪቱ ዋነኞቹ ክልሎች ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ግጭት አለመረጋጋት ለዚህ ውጥን ቀዳሚው እንቅፋት ሊሆን እንደምችል ተገምቷል።

የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተንታኝ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በማሻሻው ፖሊሲ አተገባበር ሂደት ውስጥ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ለሰላምና ጸጥታው መፍትሄ መፈለግ ነው ብለዋል። «ሰላምና ጸጥታ በሌለበት ሁኔታ የትኛውም ዓይነት ፈንድ ቢፈስ ምንም ነው ሊሆን የሚችለው» የሚሉት ባለሙያው በተለይም ደግሞ የገንዘብ ድጋፉ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ እንዳለው በብድር ሲመጣ ተገቢው ውጤት ከገንዘቡ ሳይገኝ ብድር መመለሻው ደርሶ እዳ ውስጥ እንደሚያስገባም ጠቅሰዋል።

ገንዘቡ እንደ እርሾ ሆኖ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሊያነቃቃው ይችላል የሚል ግምታቸውን የገለጹት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ የኤኮኖሚ ባለሙያ ነገር ግን ስጋትም አለኝ ነው የሚሉት። ፎቶ፤ አዲስ አበባምስል Seyoum Getu/DW

የብድሩ ተስፋና ስጋት

ገንዘቡ እንደ እርሾ ሆኖ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ሊያነቃቃው ይችላል የሚል ግምታቸውን የገለጹት ባለሙያው ነገር ግን ስጋትም አለኝ ነው የሚሉት። ባለፉት ጥቂት ዓመታት በገበያው ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ስፍቶ የተስተዋለውን ክፍተት በቀላሉ መድፈን አስቸጋሪ መሆኑ ደግሞ ስጋታቸውን ካጎሉት ነጥቦች ዋነኛው ነው። «ጉዳዩ ከኢኮኖሚውም ተሻግሮ ይሄዳል። ሰላምና ጸጥታ አንዱ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ነው። ሰላም ሲኖር ምርት ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀስና ፍላጎትና አቅርቦቱ ይጣጣማል። አሁን በኢትዮጵያ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ባላቸው ሦስት ክልሎችኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ግብር እንኳ በተገቢ ሁኔታ ይሰበሰባል ወይ ብለን ብንጠይቅ ደረታችን ነፍተን በበቂ ሁኔታ እየተሰበሰበ የመንግሥት መስተጋብሩም ጤናማ ነው የምንለው አይሆንም» ብለዋል። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚውን ያለ ፖለቲካ መስተጋብር እንዳንመለከተው ያስገድደናል ብለዋል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ሳያባራ የተካሄደውና ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ግድም በፊት እልባት ያገኘው የሰሜን ኢትዮጵያው ትግራይ ጦርነት ካጠፋው ከፍተኛ የሰው ሕይወት በተጨማሪ 28 ቢሊየን ዶላር ንብረት ስለማውደሙ ተነግሯል። አሁን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ዘላቂ እልባት ያላገኙት ግጭቶችም በውል ያደረሱት ጉዳቶች ተጠንቶ ባይገለጽም ጉዳቱ ቀላል እንደማይሆን ይገመታል። የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ፤ «በጦርነት የሚገኝ ዘላቂ ድል ባለመኖሩ ለሚስተዋሉት ግጭቶች ሰላማዊ እልባት መስጠት፤ ከዚያም የተገኘውን ብድር አዋጭ በሆኑ እንደ ግብርና እና መሰረተ ልማቶች ላይ በማዋል ብቻ ውጤት ሊገኝበት ይችላል» ነው የሚሉት።

የኢኮኖሚ ተመራማሪው ባለሙያ ዶ/ር ደግዬ ጎሹም በኢኮኖሚው ሪፎርም ውስጥ በግልጽ ትከኩረት ያልተሰጠው ያሉት የጸጥታው ጉዳይ ስኬታማነቱን የሚወስን ዋናው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። «ኢነቨስትመንት ለመሳብም ሆነ ምርትን ወደ ውጪ ለመላክ ግጭትና የፖለቲካ አለመረጋጋትን መፍታት የግድ ነው» ብለዋል።

 ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW