1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኢዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ውሳኔ ላይ የባለሙያ አስተያየት

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 12 2017

“ከሚኖራቸው ገንዘብ በታች እያገኙ ታክስ መክፈል በሞራልም ሆነ በኢኮኖሚው እንደሚጎዳቸውም ግልጽ ነው” ያሉን ዶ/ር አጥላው መሆን ያለበት ቢቻል ከአነስተኛ ገቢ ምጣኔ በታች ያሉትን በመደጎም እፎይታ መስጠት ነበር የሚገባው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

Äthiopien I Addis Abeba - Märkte, während sich Christen auf das Weihnachtsfest vorbereiten
ምስል፦ Solomon Muchie/DW

አወዛጋቢው የኢዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ውሳኔ ላይ የባለሙያ አስተያየት

This browser does not support the audio element.

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሓሙሱ አስቸኳይ ስብሰባው ያፀደቀው በተለይም ከቅጥር ሠራተኞች ግብር የመክፈል አቅም አንጻር ብርቱ መነገሪያ ሆኖ የሰነበተው የፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅ ሰፊ ውዝግብና አቤቱታዎች የቀረቡበት ነበር። በኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን የመንግሥት ሠራተኞች ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል 8 ሺህ 300 ግድም እንዲሆን አቤቱታ ቢያቀርብም በማሻሻያው 2000 ብር ሆኖ ጸድቋል።
አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የምጣኔሃብት ባለሙያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ የመንግስት ግብር አሰባሰብ ለአዎንታዊ ልማትና የመንግስት አገልግሎት የማይታበል ሚና እንዳለው ጥያቄ ውስጥ ባይገባም ግብሩ ሲሰበሰብ ግን የዜጎች የመክፈል አቅም በእጅጉ ሊታሰብበት የሚገባው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ “ደመወዝ ከመኖሪያ በታች ሆኖ እሱም ግብር ይቆረጥበት ሲባል ፍትሃዊ አይሆንም” የሚሉት ባለሙያው ኑሮአቸውን ሳይደጉሙ ግብር ለመክፈል የሚገደዱ ደህንነታቸው ይፈታተናልም ሲሉ ማብራሪያቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ከሚኖራቸው ገንዘብ በታች እያገኙታክስ መክፈልበሞራልም ሆነ በኢኮኖሚው እንደሚጎዳቸውም ግልጽ ነው” ያሉን ዶ/ር አጥላው መሆን ያለበት ቢቻል ከአነስተኛ ገቢ ምጣኔ በታች ያሉትን በመደጎም እፎይታ መስጠት ነበር የሚገባው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የአንዱ የድጎማ ስልት ግብርን መቀነስ ወይም መተው ሲሆን እንደሌሎች አገራት ደግሞ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት ሁኔታን ማመቻቸትም ይጠይቃል ብለዋል፡፡ እናም በዚህ አገር ሁኔታ እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች መንግስት ግብርን መቀነስ አሊያም መተው ነበር የተሻለው አማራጭ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በሳምንቱ እጅግ መነጋገሪያ በሆነው የደመወዝ ገቢ ግብርን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን ዋና ኃላፊ ካሳሁን ፎሎ እራሱን ማኖር ከማይችል ሰው ግብር መሰብሰብ ተገቢ አይደለም የሚል መከራከሪያ ነጥብ ይገኝበታል፡፡ “መኖር ከማይችል ሰው ግብር አይሰበሰብም” ያሉት አቶ ካሳሁን በተለይ በዝቅተኛ የደመወዝ እርከን የሚተዳደሩ ሰራተኞች እጅጉን ፈታኝ ያሉት ህይወት እየመሩ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

“ከሚኖራቸው ገንዘብ በታች እያገኙ ታክስ መክፈል በሞራልም ሆነ በኢኮኖሚው እንደሚጎዳቸውም ግልጽ ነው” ዶ/ር አጥላው ዓለሙ የምጣኔ ሐብት ባለሙያምስል፦ Million Hailesilassie/DW

የኢትዮጵያ መንግስት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ.ኤም.ኤፍ) እና ከዓለም ባንክ ጋር የገባው የብድርና ድጋፍ ስምምነት የመንግስት ገቢ በተለያዩ አማራጮች ከፍ እንዲል የሚያበረታታው ነው፡፡ አንዱ እና ዋነናኛው የገቢ ማሳደግያ ስልት ደግሞ ግብር መሰብሰብ በመሆኑ መንግስት በዚያ ላይ ትኩረት አድርጎ በሚንቀሳቀስበት ባሁን ወቅት በየትኛውም ስልት የግብር ስርዓቱን የማላላት ሁኔታ አይጠበቅም የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር አጥላው ዓለሙ   “አይ ኤምኤፍ እና ዓለም ባንክ አገሪቱን የሚያስተዳድሩት እነሱ አይደሉም፤ በኋላ ለሚመጣውም ችግር ተጠያቂ ኤሆኑም” ያሉት ዶ/ር አጥላው፤ መንግስት ሁልጊዘዜም ቢሆን በዜጎች እና በባለሙያዎች የሚነገረውን ተከታትሎ መስማት ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ዓለማቀፉ አበዳሪ ተቋማቱ እንደአበዳሪነታቸው ጥቅማቸው እንዳይጎዳ ይሰራሉ ያሉት ባለሙያው እነሱ የመንግስትን ገቢ በመጨመር ያበደሩት ገንዘብ እንዲከፈል ቢሹም መንግስት ችግር ውስጥ ሚያስገባውን እርምጃ ግን ማጤን እንዳለበትም ምክረሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ባለሙያው አክለውም ከእነሱ የሚገኘውን ገንዘብ በአትራፊ ፕሮጀክቶች ላይ በማዋል ማትረፍም ሌላው ስልት ቢሆንም መንግስተ ከተቋማቱ የሚገኘውን ገንዘብ ለካፒታል ይሆን ለጊዚያዊ ወጪ የት እንደሚያውለው አይታቀም ብለዋል፡፡ ሆኖም መንግስት ገንዘቡን በአፋጣኝ ገቢ የሚያስገቡ ፕሮጀክቶች ላይ ካላዋለ ዜጎች ከአቅም በላይ ግብር ሲጠየቁ መንግስትም ሆነ ዜጎች ላይ ችግር መደቀኑ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሁለት ሳምነታት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብሪያ አገሪቱ መሰብሰብ ከሚገባት ግብር እጅግ አነስተኛውን መጠን እየሰበሰበች መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW