1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
እምነትኢትዮጵያ

የኢድ በዓልና ተፈናቃዮች በአማራ ክልል

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 2 2016

ከተለያዩ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለመፈናቀል ተገድደው በአማራ ክልል የሚገኙ ሙስሊሞች የዘንድሮውን የኢድ አልፈጥር በዓል በተለያዩ ስሜቶች አክብረው ውለዋል ።

Alamata Flüchtlingsunterkünfte Jara in Region Amhara
ምስል፦ Alamata City Youth League

የዒድ አል ፈጥር በዓል አከባበር በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች

This browser does not support the audio element.

ከተለያዩ የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ለመፈናቀል ተገድደው በአማራ ክልል የሚገኙ ሙስሊሞች የዘንድሮውን የኢድ አልፈጥር በዓል በተለያዩ ስሜቶች አክብረው ውለዋል ። አቅም ለሌላቸው ተፈናቃዮች ለኢድ በዓል ድጋፍ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ካሰባሰቡ ወጣቶች መካከል በአፋር ክልል ኗሪው አብዱ መሐመድ አንዱ ነው ። በርዳታ ተሰባስበው የተገዙ 3 በሬዎችን ከአፋር ወልዲያ ድረስ ተጉዞ ለተፈናቃይ ምእመኑ ማከፋፈሉን ገልጧል ። «ሃይማኖት ዘር ሳይለያቸው» ቅን ሰዎች በርዳታው መሳተፋቸውንም አክሏል ። «ኦርቶዶክስ ወንድሞችም አግዘውናል» ያለው የአፋሩ ወጣት ኅብረተሰቡ ሙስሊም ክርስቲያን ሳይል ለበዓሉ ያሳየውን ድጋፍ አድንቋል ። በሌላ ቦታዎች በዓሉን የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ያሳለፉ ተፈናቃዮች እንዳሉም ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን በስልክ በማነጋገር የባሕር ዳር ወኪላችን ዓለምነው መኮንን ቀጣዩን ዘገባ አጠናቅሯል ። 

አንዳንድ ተፈናቃዮች በዓሉን በጎ አድራጊ ግለሰቦች ባደረጉላቸው ድጋፍ በደስታ እያከበሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት ኢድ አልፋጥር በዓለን መቀበላቸውን ነግረውናል ።

በሰሜን ወሎ ዞንጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ  ተፈናቃዮች መልካም አሳቢ የሆኑ ወጣቶች ባደረጉላቸው ድጋፍ በዓሉን በጥሩ ሁኔታ ማክበራቸውን ይገልፃሉ፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ 3 ሰንጋዎች ታርዶላቸው ተከፋፍለዋል፣ እንዲሁም የስንዴ ዱቄት ተሰጥቷቸዋል፣ ከ400 እስከ 800 ብር የተሰጣቸውም እንዳሉም ገልጠውልናል፡፡ ድጋፉን ካሰባሰቡት ወጣቶች መካከል በአፋር ክልል የሚኖረውን አብዱ መሐመድን ድጋፉን እንዴት አሰባሰብክ? ብለን  በስልክ ጠይቀነው ነበር ፡፡

ወጣቱ እንደነገረን ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ተጠቅሞ እስከ 300 ሺህ ብር ማሰባሰብ መቻሉንና በዚህም 3 ሰንጋዎችን አስገዝቶ እርሱ ራሱ ከቦታው ተገኝቶ ማሳረዱን አመልክቷል። እንደዚሁም ከ400 እስከ 800 ብር የሚደርስ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጧል፣ በ100 ሺህ ብር ዱቄት ገዝቶም አከፋፍሏል፡፡ በገንዘብ መዋጮው ሁሉም ሰው በሐይማኖትና በዘር ሳይገደብ መሳተፉንን የነገረን አብዱ ለሁሉም ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በአማራ ክልል ተፈናቃዮች ከሚገኙባቸው የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች አንዱ፤ ጃራ፤ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Alamata City Youth League

በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ አካባቢ የሚገኘውና "ቱርክ” እየተባለ በሚጠራው መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አንድ ተፈናቃይ እንዳሉት ምንም እንኳ የእርድ እንስሳት ባይቀርብም በዓሉ ሞቅ ባለ ሁኔታ እየተከበረ ነው ብለዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪው የእርድ እንስሳት ዛሬ ባይቀርቡም በጾሙ ወቅት የአካባቢው ነዋሪ ሰንጋ እያቀረበ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፣ ዛሬ ደግሞ በተሰጣቸው የምግብ ዱቄት በዓሉን በደስታ እያከበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በመርሳ መጠለያ ጣቢያም እንዲሁ ከመስጊዶች በተዋጣ ገንዘብ ለተፈናቃዩ የዓመት በዓል መዋያ ዱቄትና ብር እንደተሰጣቸው አንድ ተፈናቃይ ነግረውናል፡፡ "ከመስጊዶች በተሰበሰበ ገንዘብ የዱቄት ድጋፍ ተደርጎልናል ብርም ተሰጥቶን ሥጋ ገዝተን ተመግበናል፣ በዓሉን በጥሩ ሁኔታ እያሳልፍን ነው” ብለዋል፡፡

በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሀን "ወይንሸት” በተባለ መጠለያ የሚኖሩ እንድ ተፈናቃይ ግን ምንም እንኳ የኢድ ስግደት አድርገው ቢመለሱም በምግብ እረገድ ምንም የቀረበላቸው ነገር እንደሌለ ነው ያመለከቱት፡፡ እንደ ተፈናቃዩ የኢድ ስግደትን በሰላም አከናውነዋል፣ ሆኖም ከስግደት መልስ ያለው ሁኔታ የበዓል ስሜት የለውም ነው ያሉት፣ ለቁርስ እንኳ የተዘጋጀ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች አንድ ሚሊዮን ያክል ተፈናቃዮች ወደ ክልሉ ገብተው የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹ ወደነበሩበት መመለሰቸው ይታወሳል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW