የኢድ አል አደኻ በዓል አከባበር በአዲስ አበባ
ረቡዕ፣ ሰኔ 21 2015
1444ኛው ዓመተ ሒጅራ የኢድ አል አደሃ - አረፋ በዓል በብሔራዊ ደረጃ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም በሰላት ስግደት በከተማዪቱ ዙሪያ ገባም ሰፊ ምእመን በተገኘበት ተከብሯል። በክብረ በዓሉ ላይ ከመንግሥትም ሆነ ከሃይማኖቱ መሪዎች ንግግር አልተደረገም ። በዓሉም በሰላት ስግደት ብቻ እንዲከበር ሆኗል ። ብሔራዊ የፀጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሃይማኖታዊዉ ክብረ በዓሉ በሰላም መጠናቀቁን አስታውቋል ።
1444ኛው ዓመተ ሒጅራ የኢድ አል አደሃ - አረፋ በዓል ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ 2: 30 በብሔራዊ ደረጃ በአዲስ አበባ ስታዲየም እና በዙሪያ ገባው ሰፊ ሕዝብ በተገኘበት ተከብሯል። የክብረ በዓሉ ታዳሚ ሙስሊሞች አቅም ያለው የሀጂ ጉዞ ሥርዓት በማድረግ ሃይማኖታዊ ግዴታውን በመወጣት ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት አረፋ በዓል በግጭት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው መድረሻ ያጡትንም የምናስብበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በቅርቡ በሸገር ከተማ መንግሥት መስጊዶችን ማፍረሱን በመቃወም ለምን ያሉ ሰዎች አዲስ አበባ ውስጥ ለሞትና ለአካል መጉደል ተዳርገዋል ። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሀሳብ ያጋሩን የበዓሉ እድምተኞች የመጅሊሱን መፍትሔ ማክበር ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም እና ዙሪያው በሰላት ስግደት የተከበረው 1444ኛው ዓመተ ሒጅራ የኢድ አል አደሃ - አረፋ በዓል በሰላም መጠናቀቁን የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ