የኢድ አል አድኻ (አረፋ) በዓል አከባበር ሃይማኖታዊ እና ማህበራዊ እሴት
ዓርብ፣ ግንቦት 29 2017
አረፋ የመሰባሰቢያ ፣ቤተሰብን የመጠየቂያ በዓልም ጨምር ነው በማለት አስተያየታቸውን የሰጡን ጀማል የተባሉ የሃይማኖቱ ተከታይ፤ እሳቸውም ከሚኖሩበት አዲስ አበባ ወደ ትውልድ መንደራቸው ብቅ በማለት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማሳለፍ የሚጣደፉለት በዓል አረፋ ነው፡፡ “ወደ ስልጤ ጉራጌ የመተጫጫ ጊዜም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ደግሞም ቤተሰብ የሚሰባሰብበት ነው አረፋ፡፡ ከጾም ፊቺው ከረመዳን ይልቅ በዚህ በአረፋ ሁሉም ወደ ቤተሰቡ ይሄዳል፡፡ ይህም ትርጉሙ ከሃይማኖታዊነት ይልቅ ባህላዊ ልማዱ ይጎላል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡን አብዲ የተባሉ የእምነቱ ተከታይ በፊናቸው፤ “ዛሬ እርድ ይታረዳል፡፡ እስከ ሶስት ቀናትም የሚቀጥል ነው ይሄ፡፡ ከማለዳው የሶላት መልስ የሚፈጸመው ይህ እርድ ኡድያ ይባላል፡፡ እናም ኡዲያ ፈጽመን ጎረቤት ተጠራርተን በአብሮነት እያከበርን ነው፡፡ በተለይም ደሃ የሆነ ጎረቤት ካለ ሀቁ ነውና እነሱን ማስታወስም ግድ ይላል” በማለት የአረፋን የአብሮነት እሴት አብራርተውልናል፡፡
ከጅማ አጋሮ አስተያየታቸውን የሰጡን ሱኑ የተባሉ ሌላውም አስተያየት ሰጪ ቀጠሉ፤ “ጅማ በአረፋ መዘያየር የበዓል ድግስን አብሮ መቋደስ ነው” ሲሉ የአረፋን መናፈቅና አከባበር አስረድተዋል፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ኢብራሂም ሙሉሸዋ በርካታ የእስልምና ሃይማኖትበአላት ሁለት መልኮች ማለትም ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ መልክ ቢኖራቸውም ሁሉም የቻለ የሃይማኖቱ ተከታይ እርድ በሚፈጽምበት አረፋ ብዙ እሴቶች አሉት ይላሉ፡፡ “
ነብዩ ኢብራሂም ልጃቸውን ለፈጣሪ ለመሰዋት ካደረጉት ታሪክ ጋር ተያይዞ የሚከበረው አረፋ በዓለም ሙስሊሞች ዘንድ በተመሳሳይ መልኩ ቢከበርም በሁሉም አገራት ደግሞ የየራሱ ባህል ስላለ ሁሉም በአከባቢው ባህል በአብሮነት ያከብረዋል” በማለት በኢትዮጵያ ለአብነትም በስልጤና ጉራጌ አከባቢ የበዓሉ አከባበር የመተጫጫ እንዲሁም ቤተሰብ መሰባሰቢያ ተደርጎ ስለሚወሰድ የሚፈጥረው ማህበራዊ ቁርኝትና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ አይናቅም ይላሉ፡፡
እንደ ዶ/ር ኢብራሂም አስተያየት ሰደቃ የተባለ አንዱ የአረፋበዓል እሴት ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት ነውና ሰብዓዊነትንም የሚጎላ ነው ይሉታል፡፡ “እርድ የሚርደው ሰውየ ለራሱ ለመብላት አይደለም” ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት ዶ/ር ኢብራሂም ለአቅመ ደካሞች እና ድሆች የሚካፍልበት በመሆኑ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው በማለት አረፋ የሚፈጥረውን ማህበራዊ ትስስር ተንትነዋል፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ