የኢጣሊያ ርምጃና አዉሮጳ ፍርድ ቤት ብይን
ዓርብ፣ የካቲት 16 2004የኢጣሊያ መንግሥት ወደ ሐገሩ ለመግባት የሞከሩ የሶማሊያና የኤርትራ ስደተኞችን አስገድዶ ወደ ሊቢያ በመመለሱ ካሳ እንዲከፍል የአዉሮጳ የሰብአዊ ጉዳይ ፍርድ ቤት በየነበት።የኢጣሊያ ጠረፍ ጠባቂ ወታደሮች እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2009 በመርከብ ወደ ኢጣሊያ ለመግባት የሞከሩ አፍሪቃዉያን ስደተኞችን አስገድደዉ ወደ ሊቢያ መልሰዋቸዉ ነበር።ወደ ሊቢያ ከተመለሱት ስደተኞች አስራ-ሰወስት የኤርትራና አስራ-አንድ የሶማሊ ዜጎች በአንድ የስደተኞች መብት ተሟጋች ድርጅት አማካይነት የኢጣሊያን መንግሥት ከሰዉ ሲከራከሩ ነበር።ትናንት ሽትራስቡርግ-ፈረንሳይ ያስቻለዉ ፍርድ ቤት ኢጣሊያ ለያንዳዱ ስደተኛ አስራ-አምስት ሺሕ ዩሮ ካሳ እንድትሰጥና የከሳሾችን ወጪ በሙሉ እንድትሸፍን በይኗል።የሮማ ወኪላችን ተኽለ እግዚ ገብረ እየሱስ ዝር ዝር ዘገባ ልኮልናል።
ተኽለ እግዚ ገብረ እየሱስ
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ኢጣልያ የሰብዓዊ መብት ጥሳለች ሲል ውሳኔ አሳለፈ ። ፍርድ ቤቱ ያሬ ባሳለፈው ውሳኔ ኢጣልያ ከ 2 ዓመት በፊት በሜዴትራኒያን ባህር አቋርጠው ወደ ኢጣልያ በማቅናት ላይ የነበሩ አፍሪቃውያን ስደተኞች ወደ ሊቢያ በማባረር ሰብዓዊ መብታቸው ጥሳለች ሲል አስታውቋል ። በወቅቱ 24 የሶማሊያ የኤርትራ ስደተኞች ወደ ኢጣልያዋ የወደብ ከተማ ላምፔዱዛ በመጠጋት ላይ ሳሉ ነበር ኢጣልያ እ.ጎ.አ በ 2008 ዓም ከሟቹ የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ከሞአመር ጋዳፊ ጋር በደረሰችው ስምምነት መሠረት እንዲባረሩ ያደረገችው ። ፍርድ ቤቱ እንዳለው ኢጣልያ ስደተኞቹን በመባረር እ.ጎ.አ በ 1951 የፀደቀውን የጄኔቫው ስምምነት በተለይም የስደተኞችን አያያዝ የሚመለከተውን አንቀፅ 3 ን ጥሳለች ። በተጨማሪም ስደተኞቹን ወደ ሶማሊያ እና ኤርትራ ለመወሰድ አደጋ አጋልጣቸውም ነበር ሲል ፍርድ ቤቱ በሙሉ ድምፅ ተስማምቷል ። ኢጣልያ ከ 2 ዓመት በፊት ወደ ኢጣልያ የባህር ክልል ለመሻገር የሚሞክሩ ስደተኞችን ወደ ተነሱበት ቦታ እንድትመልስ ከጋዳፊ ጋር የፈረመችው ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያን ተወግዟል ።