1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስኢትዮጵያ

የኤለክትሪክ ሞተር ሳይክል በሀገር ውስጥ መገጣጠም የጀመረው ወጣት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 21 2016

በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ወጣት ሺሃብ ሱሌማን፤ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን የሰራ ወጣት ነው።ወጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት «ታይታን» የሚል ስያሜ የስጣትን እና ራሱ ሰርቶ የገጣጠማት መኪና ለዕይታ አብቅቷል።በቅርቡ ደግሞ የኤለክትሪክ ሞተር ሳክል ገጣጥሞ በመሸጥ የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ምርት ለመቀየር መንገድ ጀምሯል።

ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ሺሃብ ሱሌይማን በቅርቡ በኤለክትሪክ የሚሰራ የሞተር ሳይክል በሀገር ውስጥ መገጣጠም ጀምሯል
ወጣቱ የፈጠራ ባለሙያ ሺሃብ ሱሌይማን በቅርቡ በኤለክትሪክ የሚሰራ የሞተር ሳይክል በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ለሽያጭ አቅርቧልምስል፦ Shehab Sulayman

ወጣቱ ከዚህ ቀደምም በርካታ የፈጠራ ስራዎችን ሰርቷል

This browser does not support the audio element.

በሃያዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ወጣት ሺሃብ ሱሌማን፤በኤሌክትሮኒክስ፣ በአውቶሞቲቭ፣ በሮቦቲክስ እና በሶፍትዌር ልማት በርካታ  ፈጠራዎች ያሉት ወጣት ነው።
ወጣቱ ከሁለት ዓመት በፊት «ታይታን» የሚል ስያሜ የስጣትን እና  ራሱ ሰርቶ የገጣጠማት  መኪና  ከስራዎቹ መካከል አንዷ ነች።«ታይታን»፤ የወጣት ሺሃብ ሱሌይማን የፈጠራ ስራ 

ታይታን፤ የሚል ስያሜ የስጣትን እና ራሱ ሰርቶ የገጣጠማት መኪና ከወጣት ሺሃብ ሱሌማን የፈጠራ ስራዎቹ መካከል አንዷ ነች።ምስል፦ Privat

ከዚህ በተጨማሪ ሺሃብ  የ«ስማርት» ስልክ ንድፍ ሰርቶ ወደ ቻይና በመላክ እንዲመረት አድርጓል።ይህንን የስልክ ንድፍ በሀገር ውስጥ እንዲገጣጠም ለባለሀብቶች አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፤ በዚህ የፈጠራ ስራ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ፈቃደኛ የሆነ ባለሀብት ሊያገኝ አልቻለም ነበር። በዚህ ሁኔታ « አይ ስታር »በሚል ስም በመሰረተው  ኩባንያ  አማካኝነት በርካታ የፈጠራ ስራዎችን ሲሰራ ቢቆይም የገንዘብ እጥረት የፈጠራ  ስራዎቹ ወደ ምርት እና አገልግሎት እንዳይገቡ  እንቅፋት ፈጥሮበት ቆይቷል። 

«አይስታር ኩባንያ ቆይቷል ከተመሰረተ ነገር ግን ያለምንም ገንዘብ ነበር የመሰረትኩት።ከዚያ በኋላ ሶፍትዌር መሸጥ ጀመርን።በ2019 ኮቪድ እንደመጣ አካባቢ በኢትዮጵያ ብዙ የሶፍትዌር «ዲማንድ» ነበር።ለድርጅቶች ዌብሳይት፣ የሞባይል አፕሊኬሽኖች እንዲሁም ለኮሌጆች ትምህርት ቤት ስለሌለ «ኦንላይን ለርኒንግ ሲስተም» እና የተለያዩ ሲስተሞች እያቀረብን በበር እና ትንሽ ከዚህ በተገኘው ገንዘብ ባለሀብትም ጨምረን ነበር ያንን መኪና የሰራነው።ያንን ከሰራን በኋላ በዚሁ በአይስታር ድርጅት ኦጅን የሚባል ሞተር ሰይክል ይዘን የቀረብነው።በዚሁ ድርጅት ስማርት ፎን ሳምፕል ሰርተን እሱም ወደ ገበያ አልቀረበም በፋይናንስ እጥረት።»በማለት በገንዘብ እጥረት ያጋጠመውን ፈተና ተናግሯል።የፈጠራ ባለሙያዎች የገንዘብ ድጋፍ ችግር

ወጣቱ «ብሉ»የሚባል የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ በመፍጠርም ከአማዞን ሰርቨር ተከራይቶ ለአገልግሎት አብቅቶ የነበረ ቢሆንም፤ ለሰርቨር የሚወጣውን ወጭ መሸፈን ባለመቻሉ እንዲቋረጥ ሆኗል።

ወጣት ሺሃብ ሱሌይማን «ብሉ» የሚባል የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ በመፍጠር ለአገልግሎት አብቅቶ የነበረ ቢሆንም፤ በገንዘብ እጥረት ተቋርጧል።

በአሁኑ ወቅት ግን አይስታር በተባለው  ኩባንያው  አማካኝነት ከውጭ እና ከሀገር ውስጥ ያገኛቸውን ቁሳቁሶች ተጠቅሞ በኤለክትሪክ የሚሰራውን ሞተር ሳይክል  ገጣጥሞ ለሽያጭ ዝግጁ በማድግ ስራዎቹን ወደ አገልግሎት የመቀየር ህልሙን ለማሳካት መንገድ ጀምሯል። የምርት ስራውን ከሞተር ሳይክል ለመጀመሩ ብዙ ምክንያቶችን ያቀርባል።  
«አወ ከሁለት ዓመት በፊት ታይተንን ሰርተን ህዝቡም በጣም ወዶት ነበር ።ወደ «ማስ ፕሮዳክሽን» ለመግባት የገንዘብ እጥረት አጋጥሞን ነበር።ወደ 8 ሰው የሚይዝ ነበር  እና እሱን ወደ «ፕሮዳክሽን» ለማስገባት ብዙ ገንዘብ ይፈልግ ነበርና ለዚያ ነው በሞቶር ሳይክል የጀመርነው። ይህ ሞተር ሳይክል ከ«ኮስት» አንፃር ትንሽ ነው።»በማለት ከመኪና ጋር ሲነፃጸር ሞተር ሳይክል ከወጪ አንፃር  አነስተኛ መሆኑን ገልጿል።

ሌላው እና ሁለተኛው  ምክንያቱ ደግሞ  በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የሞተር ሰይክል ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ ነው።
 «የሞተር ሳይክል ዲማንድ ኢትዮጵያ ላይ በጣም ሰፊ ነው።ሌላ ደግሞ ብዙ የስራ ዕድል ይፈጥራል ብለን ስላመንበት ነው።ብዙ ዲማንድ አለው ያልኩበት ምክንያት አዲስ አበባ ላይ በተለይ ብዙ ድርጅቶች አሉ «ፉድ ደሊቨሪ» ላይ የሚሰሩ።ዕቃ ማድረስ ላይ የሚሰሩ ብዙ ድርጅቶች አሉ።አሁን ላይ ብዙ «ሰርቫይቭ» ማድረግ ያልቻሉበት ምክንያት የሞተር እጥረት በመኖሩ ነው።አዲስ አበባ ላይ እነዚህ ስራዎች የሚሰሩት በሞተር ነው።በመኪና ብዙ ነዳጅ ይፈልጋል።መንገድም ይዘጋጋል።የፈለጉበት ቦታ ቶሎ መድረስ ስለማይችሉ ሞተር ሳይክል ይፈልጋሉ ።አሁን ባለው ሁኔታ የጋዝ ሞተር ሳይክልም ወደ ሀገር ውስጥ አይገባም ወጭዉም ከፍተኛ ነው።» በማለት አብራርቷል።

ወጣት ሺሃብ ሱሌይማን በኤለክትሪክ የሚሰሩ ሞተር ሰይክሎችን በሀገር ውስጥ በመገጣጠም ለሽያጭ ማቅረብ ጀምሯልምስል፦ Shehab Sulayman

በኤለክትሪክ የሚሰራ የሞተር ሳይክል በፈረንሳይ እና በአሜሪካ የፈጠራ መብት ባለቤትነት ተመዝግቦ ከ1880ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት ጥቅም ላይ መዋል የጀመረ ቀደምት ቴክኖሎጂ ነው።ነገር ግን በተለያዩ ጊዜዎች በአገልግሎቱ በቅርፁ እና በፍጥነቱ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረገለት እዚህ ዘመን ላይ ደርሷል።የሺሃብ ኩባንያ በሚገጣጥመው ኡጅን ሞተር ሳይክልም በርካታ ማሻሻያዎች እንደተደረገበት  ይገልፃል።

«የኤለክትሪክ ሞተር ሳይክል በዓለም ላይ አወ ቆይቷል።ሀገራችን ውስጥም የገቡ አሉ።እኛ ግን«ሎካላይዝ» አድርገን ነው የሰራነው።ለምሳሌ ትልቁ የሞተር ሳይክል ክፍል  ባትሪ ነው።ባትሪ ለብዙ ዓመት መቆየት አለበት።ቻርጅም ቶሎ ማድረግ አለበት።በማንኛውም ኤለክትሪክ ቻርጅ ማድረግ አለበት።የኛ ሞተር ሳይክልም የትኛውም ገጠር ላይ የሚገኝ ኤለክትሪክ ላይ ቻርጅ ማድረግ ይቻላል።ከዚያም ባሻገር ብዙ ጊዜ የተለመደው ኤለክትሪክ ሞተር ሳይክልም ይሁን መኪና የተለመደው ከሞላ በኋላ እኛ መንቀል አለብን።ካልሆነ ባትሪው እየደከመብን ነው የሚሄደው።እኛ አሁን የተጠቀምነው ቻርጄር  ራሱን ስዊች ያደርግ እና ራሱ ያጠፋል።ከዚያም ውጭ 1500 ዋት ጉልበት ያለው ነው የተጠቀምነው።» ካለ በኋላ፤ ይህ ሞተር ሳይክል እስከ 250 ኪሎ ግራም ድረስ ክብደት መሸከም የሚችል እና የስርቆት  መከላከያ የተገጠመለት መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል። 
ኡጅን በመባል የሚጠራው ይህ ሞተር ሳይክል በኤለክትሪክ የሚሰራ መሆኑ ሺሃብ እንደሚለው የአካባቢ ብክለትን በማስቀረት እና የነዳጅ ውጭን በመቆጠብ  ረገድ ጠቃሚ ነው።ከዚህ በተጨማሪ በሀገር ውስጥ በመመረቱ  ሌሎች ጥቅሞች እንዳሉት ይገልጻል።
 «ሀገር ውስጥ መመረቱ ብዙ ጥቅም አለው።ከሀገር አንፃር አንደኛ ኢትዮጵያ የዶላር ችግር አለባት እንደሚታወቀው ሀገር ውስጥ ሲመረት ብዙ «ኮስት» ይቀንሳል።ከውጭ በዶላር ተገዝቶ ሲመጣ የቀረጥ፤የትራንስፖርት ሌላ ደግሞ ዶላር አውጥተን ነው የምንገዛው።እና ያንን በ«ሎካል» ስንተካ ብዙ ነገር «ሴቭ» እናደርጋለን።ገዝቶ ለሚጠቀም ሰውም በጣም ቅናሽ ነው የሚሆነው።የሀገር ውስጥ ማቴሪያል ስንጠቀም።»በማለት ተናግሯል።

በኢትዮጵያ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ ረገድም ይህ ሞተር ሰይክል አስተዋፅኦ እንዳለው ይናገራል።
«የትራንስፖርት ችግር በጣም በሰፊው ይታያል።ለምሳሌ ሰው ወደ ስራ ለመሄድ አንድ ስዓት ሁለት ስዓት በአብዛናው ይሰለፋል።ብዙ መንገድ የለንም መኪናው ደግሞ በዝቷል።እና ሰው መንገድ ሲዘጋጋበት ይህን ሞተር ሰይክል ብዙ መንገድ ስለማይጠይቅ በተዘጋጋ መንገድም መጠቀም እንችላለን። ሌላው ደግሞ ዋጋውም ርካሽ ነው። የፈለግንበት ቦታም ቶሎ እንደርሳለን።»በማለት ጥቅሙን አብራርቷል።

በሞጆ ከተማ የመስሪያ ቦታ ተከራይቶ የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ምርት ለመቀየር እየሰራ የሚገኘው ሺሃብ፤በተለያዩ ከተሞች የሽያጭ ስራ መጀመሩን እና  ጥሩ ተቀባይነት ማግኘቱን ይናገራል።በጀመረው ስራም ለተወሰኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጥሯል።ያም ሆኖ ቀደም ሲል ከገጠመው የገንዘብ እጥረት ባሻገር የተመቸ የመስሪያ ቦታ ማጣት እንዲሁም ስራውን በተመለከተ በመንግስት በኩል ያለው ቢሮክራሲ አሁንም ችግሮቹ ናቸው። በመሆኑም በመንግስት በኩል መወሰድ አለበት የሚላቸውን ርምጃዎች ይጠቁማል።ጀማሪ ኩባንያዎች የሚያግዘው የኬንያ ማዕከል

የወጣት ሺሃብ ሱሌይማን አይስታር ኩባንያ ለተወሰኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጥሯል ምስል፦ Shehab Sulayman

«ኢትዮጵያ ውስጥ ለጀማሪዎች ወይም ለ«ኢኖቬተሮች» ያለው የ«ቢዝነስ ኢንቫሮሜንት» በጣም ከባድ ነው።ሀሳብን ወደ ቢዝነነስ ለመቀየር ስንሄድ ከህግ አንፃር እና ካምፓኒ ለመመስረት የሚጠየቁ መስፈርቶች እና ከግብር አንፃር ችግሮች አሉ።ሰፊ ወጣት ብዙ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ያለበት በመሆኑ፤እነዚህን አበረታተን ወደ ገበያ ለማስገባት የ«ሌጋል» እና የ«ታክስ» መስፈርቱን ብንቀንስ።»በማለት ከገለፀ  በኋላ፤ «የቦታ ችግርም  አለ።እንደ «ፍሪ ዞን» አይነት እዚህ አዲስ አበባ ላይ ቢዘጋጅ አሪፍ ነው።አንድ የ«ስታርትአፕ» ህንፃ ተዘጋጅቶ ያ ደግሞ ለጀማሪዎች ብቻ ከ«ታክስ»ም እፎይታ ቢኖረው።በኋላ ካደጉ በኋላ ለሀገርም ለዓለምም መትረፍ ስለሚችሉ።ከማደጋቸው በፊት ከመጀመሪው እንዳንይዛቸው እንደዚያ ቢደረግ በጣም አሪፍ ነው ብዬ አስባለሁ።»በማለት የመፍትሄ ሀሳቦችን አብራርቷል።

በአይስታር ኩባንያ የሞተር ሰይክል በመገጣጠም ስራ ላይ ያሉ ወጣቶች ምስል፦ Shehab Sulayman

በኢትዮጵያ እንደ ሺሃብ ያሉ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን የሰሩ ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎች አሉ። ይሁን እንጅ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ  ወደ ምርት እና አገልግሎት መቀየር ባለመቻላቸው፤ የፈጠራ ስራዎቻቸው  የሸልፍ ማሞቂያ ሆነው የቀሩ በርካቶች ናቸው።ሺሃብ  እነዚህ ወጣቶች ፤ ራሳቸውንና ሀገራቸውን መለወጥ እንደሚችሉ  ያምናል።በመሆኑም ተስፋ ሳይቆርጡ  ለገበያ አዋጭ በሆኑ  የፈጠራዎች ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ እና  ችግሮቻቸውን ለመፍታትም  እርስ በእርስ ቢደጋገፉ እና ቢቀናጁ መልካም መሆኑን ከተሞክሮው በመነሳት ይመክራል።

ወጣቱ የፈጠራ ሰው ሽሃብ ሱሌማን  ፈጠራን የጀመረው ገና በ11 ዓመቱ ተወልዶ ባደገባት የዶዶላ ከተማ ነው።ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሰራቸው በርካታ የፈጠራ ስራዎች  እጁ ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም በሞተር ሳይከል የጀመረውን በሰፊው የማምረት ስራ ወደሌሎቹ የፈጠራ ስራዎቹ በማሳደግ በኢትዮጵያ ብሎም በዓለም ላይ ታዋቂ ስም ያላቸው የቴክኖሎጂ ምርቶችን የማቅረብ  ዕቅድ አለው።ወጣት የፈጠራ ባለሙያዎችን መደገፍ እና ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠርም  ሌላው ህልሙ ነው።

 

ሙሉ ዝግጅቱን  የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሀይ ጫኔ 
ሂሩት መለሰ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW