የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አብዮት በኢትዮጵያ
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 15 2018
አሁን ላይ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ከ115 ሺህ በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ከትራንስፖርት እና ሎጀስቲክ ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት አሁን ያለውን የተሽከርካሪዎችን ቁጥር በግማሽ ሚሊየን ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል፡፡
ሽግግር ከነዳጅ ወደ ኤሌክትሪክ
አብዱረህማን አሊ በአዲስ አባባ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪ ነው ፡፡ ቀደም ሲል ለበርካታ ዓመታት ቪትስ ቶዮታ አውቶሞቢል ሲያሽከረክር መቆየቱን ይናገራል ፡፡ ባለፈው ዓመት የነዳጅ ተሽከርካሪውን በኤሌክትሪክ ከቀየር ወዲህ ለነዳጅ ያዋጣ የነበረውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻሉን የጠቀሰው አብዱረህማን “ በነዳጅ ተሽከርካሪ በወር ቢያንስ ከ40 እስከ 50 ሺህ ብር ለነዳጅ አወጣ ነበር ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ከለወጥኩ በኋላ ቢበዛ 5 ሺህ ብር ባወጣ ነው ፡፡ ያን ያህል ልዩነት አለው ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተሽከርካሪው ዘመናዊ እና ምቾት ያለው ነው “ ብሏል፡፡በአሁኑወቅት ከውጭ የሚገቡም ሆነ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚናገረው የሜትር ታክሲ አሽከርካሪው አብዱረህማን አሊ የኤሌክትሪክ መሙያ ጣቢያዎች ግንባታ ተደራሽ የማድረጉ ነገር ግን ሊታሰብበት ይገባል ይላል ፡፡
“ የዋጋው ነገር “
በእርግጥየኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችበዋጋ ረገድ ውድ የሚባሉ ናቸው ፡፡ በተለይ የቤት አውቶሞቢሎች እንደየደረጃቸው ከአምስት እስከ አሥራዎቹ ሚሊየን ብር ይጠራባቸዋል ፡፡ ይህ ዝቅተኛ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ላላቸው ኢትዮጵያዊያን ገዝቶ ለመጠቀም የሰማይ ያህል ሊርቃቸው ይችላል ፡፡ ግን ደግሞ እየናረ ከመጣው የነዳጅ ወጪ አንጻር የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ለበርካቶች እፎይታን አስገኝተውላቸዋል ፡፡በተለይም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መጨመር አዳዲስ የሥራ ዘርፎች እንዲከፈቱም ምክንያት እየሆነ ይገኛል ፡፡ አሁን ላይ በርካቶች በኤሌክትሪክ መሙያ ጣቢያ ወይንም በቻርጂንግ ስቴሽን ዘርፍ በመሠማራት ላይ ናቸው ፡፡ በዚህም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ ፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፍብሪካዎች መስፋፋት
ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ ከውጭ ከሚገቡት በተጨማሪ በአገር አቀፍ ደረጃ 17 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች በሥራ ላይ ይገኛሉ ፡፡ ከእነኝህም መካከል በአዲስ አበባ እና በደብረብርሃን ከተሞች የሚገኘው በላይነህ ክንዴ ሜታል ኢንጂነሪንግ አንዱ ነው ፡፡በፋብሪካዎቹ ትላልቅ እና መለስተኛ አውቶብሶች እንደሚገጣጠሙ የገለጹት የፋብሪካው ሥራአስኪያጅ አቶ በእሱፍቃድ ሸዋዬ “ ፋብሪካዎቹ በዓመት 1 ሺህ 200 ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም አላቸው ፡፡ነገር ግን በምንዛሬ እጥረትና በካፒታል እጥረት የተነሳ አሁን ላይ በዓመት 500 ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ለገበያ እያቀረበ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡
የአካባቢ ተፅእኖን ለመቋቋም ያላቸው ፋይዳ
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ወደ ሥራ የገባውን የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሠፊ የታዳሽ ሀይል አቅም አላት ፡፡ ይህ የኤሌክትሪክ የትራንስፖርት ዘርፍን ለማሳደግ ካለው ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታ ጎን ለጎን ለአየር ንብረት መጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ ፡፡የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ተቀጣጣይ ጋዝ የሆነውን ከካርበን ሞኖ ኦክሳይድ ልቀት ነጻ መሆናቸውን የተናገሩት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ምህረት ዳናቶ በዚህም ከአካባቢ አልፎ ለዓለም የአረንጓዴ አየር ንብረት አስታዋጽኦ እንድናደርግ አስችሎናል ብለዋል ፡፡የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙባቸው ባትሪዎች አካባቢ በካይ መሆናቸውን ያነሱት ዶክተር ምህረት በቀጣይ አገልግሎታቸው ሲያበቃ በምን መልኩ መወገድ አለባቸው የሚለውን ከወዲሁ ፖሊሲና መመሪያዎች በማውጣት መዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡
ሽዋን ግዛው ወጋየሁ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ፀሀይ ጫኔ