በሰሜን ወሎ ዞን የኤሌክትሪክ እጦትና የነዳጅ እጥረት
ረቡዕ፣ ሐምሌ 20 2014በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ አንዳንድ ወረዳ ነዋሪዎች በመብራትና በነዳጅ እጥረት ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል፣ የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች አንድ ኪሎሜትር ለማይሞላ የከተማ ትራንስፖረት እስከ 10 ብር እከፈሉ ነው፣ የራያ ቆቦ ወረዳና አካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ በዓመት 3 ጊዜ በመስኖ በመታገዝ ያመርቱ እንደነበር አስታውሰው በነዳጅ እጥረት ምክንያት ጀኔረተር ተጠቅሞ ውሀ ከወንዝ መሳብ ባለመቻላቸው የመስኖ ስራቸው ቆሟል፡፡
የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በተፈጠረው የኃይል እጥረት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለከፋ ችግር እየተዳረጉ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡
አቶ ግርማይ አበበ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ የመብራትና የነዳጅ እጥረት በከተማዋ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡ ነዳጅ ባለመኖሩ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ ለአንድ ፌርማታ 10 ብር ይከፍላል፣ በፀጉር ስራና በአነስተኛና ጥቃቅን ሥራ የተሰማሩ ወጣቶች ደግሞ በመብራት እጦት ምክንያት ስራ አቁመዋል ብለዋል፡፡
ከተማው የቱሪስት መስህብ የነበረ ቢሆንም፣በመብራትና በውኃ አለመኖር ሰበብ ሆቴሎች አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡
አቶ አማኑኤል አስፋው የተባሉ የቆቦ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው የተፈጠረው የኃይል እጥረት በከተማው ነዋሪና በአርሶ አደሩ ሥራ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ብለዋል፡፡ በራያ ቆቦ ወረዳ በመስኖ የሚለማ ሰፊ መሬት ቢኖርም ውሀ ከወንዝ በጀነሬተር መሳብ ባለመቻሉ በዓመት 3 ጊዜ ያመርት የነበረው አርሶ አደር አሁን ምንም ማምረት አልቻለም ነው ያሉት፤ በርካታ ወጣቶችም ያለስራ መቀመጣቸውን አክለዋል፡፡
በአማራ ክልል የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ ተስፋ ሀፍቱ በላሊበላ ከተማ ከ400 በላይ ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎች (ባጃጆች) እንዳሉ ጠቁመው ለነዳጅ እጥረቱ ዋናው ምክንያት በከተማው አንድ ብቻ የነዳጅ ማደያ በመኖሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የመብራት እጥረቱን በጀነሬተር ለመፍታት ቢሞከርም ከተማ አስተዳደሩ ወጪውን አልቻለውም ነው ያሉት፡፡ ክልሉ አንድ ሚሊዮን 200 ሺህ ብር መድቦ መብራት ለከተማው በጀነሬተር መስጠት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም ይህ ነዳጅ አገልግሎት የሰጠው ለሶስት ሳምንታት ብቻ እንደሆነ ገልጠዋል፡፡
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብተማሪያም አሰፋ ስለተፈጠረው ችግር እንዳሉት የመብራት ማከፋፈያ ጣቢያው አሁን በህወሓት ስር በሚገኘው አላማጣ ከተማ በመሆኑ አገልግሎቱ ተቋርጧል፤ ሆኖም ተለዋጭ የመብራት ማሰራጫ ጣቢያ “ዶሮ ግብር” ከሚባል ቦታ ላይ እየተገነባ በመሆኑ ይህ ሲጠናቀቅ ችግሩ በከፊልም ቢሆን ይቀረፋል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታ ፈጠነ በላሊበላና አካባቢው የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት የተከሰተው በቂ የሆነ የነዳጅ ማደያ ባለመኖሩና ያለውም የተሟላ አገልግሎት ስለማይሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል፣ መፍትሔውም የነዳጅ ማደያዎችን ቁጥር ማበራከት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ነዋሪዎች ቆቦ ከተማ ውስጥ የነዳጅ ማደያ የለም ቢሉም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ግን በቂ የነዳጅ ማደያ እንዳለ ጠቁመው፣ ምናልባት ማደያዎቹ ስራ አቋርጠው ከሆነም የጦርነት ቀጠና በመሆኑ ከስጋት ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ያም ሆኖ ስለ ችግሩ መፈጠር ወደ ቢሯቸው የመጣ ቅሬታ እንደሌለ ነው የገለጡት፡፡
በየአካባቢዎቹ ስለተፈጠረው የኃይል እጦት የወልዲያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠይቆ ጉዳዩ የሚመለከተው የደሴ አሌክትሪክ ኃይል መስሪያ ቤት ነው ብሏል፡፡ ዶቼቬለ የሚመለከታቸውን የደሴ የአሌክትሪክ ኃይል አካላት በስልክ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ