የኤሎን ማስክ ግሮክፒዲያ ምን የተለዬ ነገር ይዞ መጣ?
ረቡዕ፣ ጥቅምት 26 2018
በጠፈር ጉዞዎች፣ በኤሌክትሪክ መኪናዎች እና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ባለቤትነቱ የሚታወቀው ቱጃሩ ኤሎን ማስክ፤ በቅርቡ ማለትም በጎርጎሪያኑ ጥቅምት 27 ቀን 2025 ዓ/ም ግሮኪፔዲያ ተብሎ የሚጠራ አዲስ የበይነመረብ ኢንሳይክሎፔዲያ ይፋ አድርጓል።ስሙ እንደሚያመለክተው ግሮክ የቀድሞው ቲዩተር የአሁኑ X ማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ላይ ጎልቶ የሚታየውን የሰውሰራሽ አስተውሎት ወይም AI ቻትቦትን ነው። ግሮክ እንደ ኩባንያው ገለጻ በአዲሱ ግሮኪፔዲያ ላይ እውነታ የማረጋገጥ ስራን ይሰራል።ግሮክፔዲያ፣ በሰዎች ከሚደረግ አርታኢነት ይልቅ በሰውሰራሽ አስተውሎት የሚሰራ የበይነመረብ ኢንሳይክሎፒዲያ ነው። ኤለን ማስክ ይህንን ዲጅታል መድረክ ይፋ ያደረገው፤ የዊኪፔዲያን ወደ ግራ ያዘነበለ አድልዎን ለመቃወም ነው ይላል።ነገር ግን ሰውሰራሽ አስተውሎት /AI/ በእርግጥ ያልተዛባ እና አድልኦ የሌለው መረጃ ማቅረብ ይችላልን?ሲውዘርላን የሚገኙት የሶፍትዌር መሀንዲሱ አቶ ዳዊት ዓለሙ አይቻልም ባይ ናቸው።ምክንያቱም ይላሉ ማሽን የሚያንፀባርቀው መረጃ በተሰጠው ውሂብ ወይም ዳታ ላይ ተመስርቶ ነው።
የመረጃ ማጣሪያው ግሮክ ራሱ እንደሌሎቹ የሰውሰራሽ አስተውሎት ሞዴሎች ብዙ ጊዜ የተሳሳተ መረጃ ማጋራቱን መረጃዎች ያሳያሉ።ለምሳሌ የመረጃ ይህ ዲጅታል መድረክ የፀረ ሴማዊነት መረጃን በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ አጋርቷል።ግሮክፔዲያ ስሪት (Version 0.1) በሚል ይፋ የተደገ ሲሆን፤በአሁኑ ጊዜ 900,000 መጣጥፎችን ይዟል። በጎርጎሪያኑ 2001 ዓ/ም የተመሰረተው እና በሕዝብ እርማት የሚደረግበት እና ለትርፍ ያልተቋቋመው የበይነመረብ ኢንሳይክሎፔዲያ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ገበያውን ተቆጣጥሮ እና በዓለም ላይ በብዛት ከሚጎበኙ ድረ ገጾች አንዱ ሆኖ ቆይቷል።
ኤሎን ማስክ ግሮክፔዲያን ለምን ጀመረ?
ኤለን መስክ ምንም እንኳን ቀደም ሲል ዊኪፔዲያን ሲያወድስ የቆየ ቢሆንም፤በኋላ ግን አቋሙን ቀይሮ ባለፈው መስከረም መገባደጃ ላይ ዊኪፒዲያን "ዎክፔዲያ" የሚል ስያሜ በመስጠት ድረ-ገፁ ለዘብተኛ ጉዳዮች እና በዚያ መንገድ መረጃ በሚያቀርቡ ሰዎችን ይደግፋል ሲል ነቅፏል።
አቶ ዳዊት ግን ዊኪፒዲያ ሰው የሚሰተፍበት በመሆኑ ስህተት እንኳ ሲኖር በቀላሉ መለየት ይቻላል።ለማስተካከልም ቀላል ነው።ይላሉ። ነገር ግን ግሮክፒዲያ የሚሰራው በሰው ሰራሽ አስተውሎት በመሆኑ ፤ማሽን የሚሰራው ስህተት ደግሞ ውስብስብ እና አሳማኝ በሆነ መንገድ የሚቀርብ በመሆኑ ለማረም እንኳ አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ኤለን ማስክ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዩኤስ አሜሩካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወዳጅ የነበረ እና ብዙ ወግ አጥባቂ ፖሊሲዎቻቸውን በይፋ ይደግፍ የነበረ በመሆኑ ፤ግሮፒክፒዲያም ከወገንተኝነት ሊፀዳ አይችልም የሚሉም አሉ።ከዚህ አንፃር ግሮኪፔዲያ ለንግድ የተሰራ ቢመስልም፣ ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር ፊሊፖ ትሬቪሳን ለDW እንደገለጹት የድረገጹ መነሻ የበለጠ ርዕዮተ ዓለም ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።የማስክ አዲሱ ዲጅታል መድረክ ገንዘብ ማግኘት ቀጥተኛ አላማ አይደለም፣ የሚሉት ባለሙያው ፤ይህ ድረገፅ ይፋ የተደረገው በአሜሪካ ወግ አጥባቂ እና ቀኝ ዘመሞች በዊኪፒዲያ ያቀርቡት ለበረ ትችት ምላሽ ለመስጠት ነው።ስለሆነምበሰውሰራሽ አስተውሎት የሚሰራው የዚህ ዲጅታል መድረክ ዓላማ ከዊኪፔዲያ እና ከነባሩ የመረጃ ምንጭ ሌላ አማራጭን መሞከር እና ማቅረብ ነው ሲሉ ይገልፃሉ።ይህ ደግሞ አቶ ዳዊት እንደሚሉት ግሮክፒዲያ የማስክን አመለካከት ሊያንፀባርቅ የሚችልበት ዕድል ሊኖር ይችላል።
ግሮክፔዲያ ከዊኪፔዲያ በምን ይለያል?
ሁለቱ ዲጅታልመድረኮች ልዩነቻው በመጀመሪያ እይታ ለተጠቃሚው ብዙ ግልፅ አይደሉም።እንዲያውም ግሮኪፔዲያ፤ በዊኪፔዲያ መረጃ ላይ የተመሰረተ ይመስላል። በአንዳንድ ልጥፎች ግርጌ ላይ እንደተገለጸውም አንዳንድ መረጃዎች የአቻው የዊኪፔዲያ ትክክለኛ ቅጂ ናቸው። እና የፅሁፉ ውበትም ተመሳሳይ ነው። ማስክ ይህንን አሰራር ከ2026 በፊት ለማስቆም እንደሚፈልግ ተናግሯል።
በሁለቱ መካከል ያለው ዋናው ልዩነት የሚታየው መረጃ የሚጣራበት ሂደት ላይ ነው። ዊኪፔዲያ በትብብር ማህበረሰብ አርትዖት ላይ የተመሰረተ እና ማንኛውንም ስህተቶች ወይም የክርክር ነጥቦችን ለመጠቆም ሂደቶች አሉት። በዩናይትድ ኪንግደም በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና የህዝብ ፖሊሲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሮክሳና ራዱ ለDW እንደተናገሩት ግሮኪፔዲያ ምንም አይነትየሰው አርትኦት እና ተሳትፎ የሌለው እና ቁጥጥር የጎደለው ይመስላል።ፕሮፌሰሯ አያይዘውም ግሮኪፔዲያ ይዘቱን ለተጠቃሚ ከማቅረቡ በፊት በሚደረጉ ውሳኔዎች ላይ ግልጽነት ሳይኖረው ፤ግልጽ ባልሆነ የመረጃ አሰባሰብ እና የመረጃ ምንጭ የመረጃ ቋት እና ሞዴል ይሰራልም ሲሉ ገልፀዋል።አቶ ዳዊት በበኩላቸው የመረጃ ምንጫቸው በግልጽ አለመታወቁም ሌላው ችግር መሆኑን ያስረዳሉ።
ግሮክፒዲያ ምን ያህል ትክክለኛ ሀሳቦችን ያቀርባል?
ማስክ አዲሱን ድረ-ገጽ በመረጃ ስፋት፣ ጥልቀት እና ትክክለኝነት ከዊኪፔዲያ ይበልጣል ብሏል ነገር ግን በግሮክ እና ሌሎች የሰውሰራሽ አስተውሎት /AI /ሞዴሎች የተሰሩ ከፍተኛ ስህተቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በካቶች ጥርጣሬ አላቸው።«ግሮክፔዲያ ሆን ብሎ ሁልጊዜ ያልተረጋገጡ ምንጮችን ይጎትት እና 'በግሮክ የተረጋገጠ እውነታ' በሚለው መለያ ሊመጣ ይችላል ፣ ይህም አከራካሪ ነው» ብለዋል ራዱ።ራዱ ስለ ግሮኪፔዲያ ያላቸው የመጀመሪያ ግንዛቤ ሲገልፁም «አንዳንድ ጊዜ መረጃዎችን እንደ ውክፔዲያ በተለየ ርዕስ ላይ አጠቃላይ እይታ ለመስጠት፤ ሁል ጊዜ ያልተደራጁ የተለያዩ ሀሳቦች ፣ ክስተቶች እና ፅንሰ-ሀሳቦችን ስብስቦ ያቀርባል» ብለዋል።ፕሮፌሰሯ አክለውም «ግሮኪፔዲያ አንባቢዎቹን ከተለመደው ኢንሳይክሎፔዲያ የሚጠብቁትን ሰፊ እና አጠቃላይ ስዕል ሊያሳጣ ይችላል።»ብለዋል።እናም ከነባሩ መገናኛ ዘዴ የበለጠ እንደ «ሪኤዲት» ልጥፎች እና የብሎግ መጣጥፎች ላሉ ክብደትን ይሰጣል።
የግሮኪፔዲያን ትክክለኛነት በሰፊው ለመገምገም ጊዜው በጣም ገና ቢሆንም፣ የተወሰኑ ፅሁፎች ግን ጠቃሚ መረጃዎች ይሰጣሉ።ለምሳሌ፣ስለራሱ ስለኤለን ማስክ በግሮክፒኪያ የሰፈረው መጣጥፍ በዚህ ዓመት ጥር ወር በተደረገው የአሜሪካው ፕሬዚዳንድ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ያሳየውን ብዙዎች እንደ ናዚ ሰላምታ አድርገው ይመለከቱት የነበረውን የማስክን የእጅ ምልክት አልጠቀሰም። በዊኪፔዲያ አቻው ግን መረጃው በሰፈው ሰፍሯል።ያም ሆኖ እንዲህ ያለ አድልኦ እና ስህተት ሲያጋጥም ማሽኑ እዚህ ድምዳሜ ላይ እንዴት እንደደረሰ የማወቂያ መንገድ የለም።
ግሮክፔዲያ አድሏዊ ነው?
ነባሩ የመገናኛ ዘዴ እና ይፋዊ የመረጃ ምንጮች የማይታመኑ ናቸው የሚለውን የማስክ እምነት በአሜሪካ ፖለቲካ በወግ አጥባቂው ወገን ብዙዎች የሚጋሩት ነው።እንደ ትሬቪሳን አባባል የመድረኩ ስኬት የሚወሰነው ሰውሰራሽ አስተውሎት ከሰዎች በተሻለ የማያዳላ ነው የሚለውን ሀሳብ በመግዛት ላይ ነው።ትሬቪሳን እንደሚሉት «ማስክ ለማድረግ እየሞከረ ያለው AIን ለአድሏዊነት ችግር መፍትሄ አድርጎ ማቅረብ ነው።» በዚህም ማስክ «አንዳንዶች ሊሰማቸው የሚችለውን ግንዛቤ ለመጠቀም እየሞከረ ነው።የሰውን ተሳትፎ ማስቀረቱም ይህን የበለጠ ተጨባጭ ያደርገዋል።» ብለዋል።
የሂደቱ ግልፅነት የጎደለው መሆኑኑም ለትሬቪሳንም ሌላው ችግር ነው። «በዚያ ጥቁር ሣጥን ውስጥ በትክክል ምን እንደተፈጠረ አናውቅም የሚሉት ባለሙያው፤ ስለዚህ እኛ የመረጃ ሸማቾች ለምን አንድ መረጃ በአንድ ኢንሳይክሎፔዲያ ማጠቃለያ ውስጥ ሊደርስ እንደቻለ የምናረጋግጥበት እድል አልተፈጠረም።በማለት ገልፀዋል።አቶ ዳዊት ይህንኑ ሃሳብ በምሳሌ ያጠናክራሉ።
ዊኪፔዲያ ራሱ ብዙ ጊዜ ከአድልዎ ጋር የተያያዘ ክስ አጋጥሞታል። ክሱ ከማስክ እና ከአሜሪካ ቀኝ ዘመሞች ብቻ አይደለም።የሃቫርድ ዩኒቨርሲቲ እና የወግ አጥባቂው የማንሃታን ተቋም ጥናት፤ ድረ-ገጹ ወደ ግራ ክንፍ የሚያደሉ አንዳንድ ማስረጃዎችን እንዳሳየ ደርሰውበታል።«የዊኪፔዲያ መጣጥፎች ከግራ ፖለቲካ አቻዎቻቸው ይልቅ ወደ ቀኝ ያዘነበለ የፖለቲካ አቅጣጫን ከሚወክሉ ቃላት ጋር አሉታዊ ስሜትን የማያያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።» ሲል የማንሃተን ኢንስቲትዩት ባለሙያው የዴቪድ ሮዛዶ ዘገባ አጠቃሏል።
የሰዎች ቁጥጥር አስፈላጊነት
ባለሙያዎች በመረጃ አቅርቦት ላይ አንዳንድ አድልዎየማይቀር እንደሆነ ይስማማሉ፣ ነገር ግን ግልጽነት እና ስህተቶችን መቀበል ለቁጥጥር እና ለእርምት በር ይከፍታል።ነገር ግን በግሮክፔዲያ ይህ ጉዳይ እስካሁን አልታየም።ስለሆነም የባለሙያዎቹ ትክክለኛ እና ሚዛናዊ መረጃ ለተጠቃሚው ለማቅረብ ስህተትንም ለማረም የሚሻለው ሂደቱን የማንረዳው ማሽን ሳይሆን፤ ስሜት እና ተጠየቅን የሚረዳው የሰው ልጅ ነው። በመሆኑም ከማሽን በተጨሪ የሰዎች አርትኦት ሁልጊዜ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎቹ አስምረውበታል።
ያምሆኖ እንደባለሙያዎቹ በትክክለኛ መንገድ ጥቅም ላይ ከዋለ ከዋለ እና የሰዎች ቁጥጥር ከታከለበት የሰውሰራሽ አስተውሎት ጊዜን፣ገንዘብን በመቆጠብ፣ የስራ ቅልጥፍናን በመጨመር እና የተሻለ ውጤት በማግነት ረገድ ለሰውልጆች ያለው ጠቀሜታ የሚካድ አይለም።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሐይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ