1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤሚ አዋርድስ አሸናፊዎቹ ሀድራ እና ንጉሱ

ዓርብ፣ ጥቅምት 11 2015

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ፣ ለፊልም ባለሙያዎች የሚሰጠውን ፣በአጭሩ «ኤሜ » በመባል የሚታወቀውን ሽልማት ያገኙ ሁለት ወጣት ኢትዮጵያውያንን እንግዳው አድርጓል። የፊልም ፕሮዲውሰር እና ጋዜጠኛ ሀድራ አህመድ እና የካሜራ ባለሙያ ንጉሱ ሰለሞን ፣የኤሚ 2021 ተሸላሚ ናቸው።

Emmy Award 2021 Winners
ምስል Mekbib Tadesse

This browser does not support the audio element.

« ኤሚ አዋርድስ» በዩናይትድ ስቴትስ እና ዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ ለፊልም ባለሙያዎች የሚሰጥ ትልቅ ሽልማት ወይም እውቅና ነው።  ኢትዮጵያዊቷ ሀድራ አህመድ ይህንን በጎርጎሮሲያኑ 2021 ያሸነፈችውን ሽልማት በቅርቡ ተቀብላለች።  ጤናይስጥልኝ የተከበራችሁ የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተከታታዮች፤  የ 33 ዓመቷ ሀድራ የኑቢያ ሚዲያ ኤንድ ኮሙኒኬሽንስ  (Nubia Media and Communications)  ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም ጋዜጠኛ እና የዘገባ ፊልሞች አዘጋጅ ናት። ለ« ኤሚ አዋርድስ»  ሽልማት ያበቃት ከሶስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከሰከሰው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከባልደረጋዋ ጋር የሰራችው ዘጋቢ ፊልም ነው። « ያሸነፍንበት ዋንኛው ምክንያት የምርምራ ጋዜጠኝነትን እና በሰዎች ላይ አንድ ነገር ሲከሰት በሰዎች ላይ ስለሚያመጣው ጫና፣ ጉዳት እና የመሳሰሉትን የተጎዱ ቤተሰቦችን ታሪክ በደንብ ሽፋን ስለሚሰጥ ነው።  » ትላለች።  ዘጋቢ ፊልሙን የሰሩት ሌላ ኢንዶኜዢያ ውስጥ የተከሰከሰ ተመሳሳይ አይሮፕላን ስለነበር ከዚያ በተውጣጣ ቡድን እና ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከሚገኙ የተጎጂ ቤተሰቦች ጋር በመሆን ነው።  
አሸናፊ በሆነው በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ ከሀድራ ጎን ሆኖ ከኢትዮጵያ የተሳተፈው የካሜራ ወይም የቪዲዮግራፊ ባለሙያ ንጉሱ ሰለሞን ይባላል። የ32 ዓመቱ ወጣት እጎአ በ2017 ዓም ከሀድራ ጋር የመሰረቱት የኑቢያ ሜዲያ ኤንድ ኮሙኒኬሽንስ ምክትል ሥራ አስኪያጅም ነው።  

የ« ኤሚ አዋርድስ» ተሸላሚ ፕሮዲውሰር ሀድራ አህመድምስል Mekbib Tadesse

የኤሚ አዋርድስ ተሸላሚ የሆኑት በቡድን ወይስ በተናጥል ነው?

«የኤሚ አዋርድስ በመሰረቱ በተናጥል የሚበረከት ሽልማት ነው። ለፕሮዲውሰሮቹ የኤሚ ዋንጫ ሽልማት ሲሰጥ ለሌሎቹ የፕሮዳክሽን አባላት ደግሞ የእውቅና ፕላክ እና ሰርተፊኬት ይሰጣል። በዋናነት ግን የኤሚ አሸናፊ ሊስት ውስጥ የሚገቡት ፕሮዲውሰሮች ናቸው።» ይላል ንጉሱ።
ሀድራ ስለ ስኬቷ ወይም ደግሞ ይህንን ለስራዋ ትልቅ እውቅና የሚሰጥ ሽልማት ማግኘቷን በማህበራዊ መገናኛ ገጾቿ ላይ ለሌሎች ስታጋራ ወላጆቿን ማኩራት ትልቅ ህልሟ እንደነበርም ገልፃለች። ይህ ምኞቷም ተሳክቶላታል።  «ወላጆቼ ከእኔ በላይ ነው የተደሰቱት ምክንያቱም ብዙ ለፍተው ነው ያሳደጉን። » ትላለች ሀድራ ። ወጣቷ ጋዜጠኛ ብዙ ፈተናዎችን አልፋ ከዚህ እንደረሰች ምሳሌ በመስጠት ሌሎች ወጣቶች ተስፋ እንዳይቆርጡ እና እንዲበረታቱ ትመክራለች። 

የካሜራ ወይም የቪዲዮግራፊ ባለሙያ ንጉሱ ሰለሞንምስል Mekbib Tadesse

«የካሜራ ስራ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም እውቅና የማይሰጠው ስራ ነው» የሚለው ንጉሱ ሳያስበው ወደዚህ ስራ መግባቱን አጫውቶናል። ንጉሱ ከዮኒቨርስቲ  በኮምፒውተር ሳይንስ በዲግሪ ተመርቋል። ይሁንና የካሜራ ቴክኒክ ይበልጥ ስቦት ሙያውን ሊያዳብር ችሏል ከሀድራ እና ከተለያዩ አለም አቀፍ የሚዲያ ድርጅቶች ጋር ይሰራ የነበረው ንጉሱ ኤሚን ያሸነፉበት ቀረፃ «በጣም ፈታኙ ነበር» ይላል።« ቦታው  ላይ ሆኖ መቅረፅ እጅግ በጣም ፈታኝ ነበር። መቅረፅ ማቆም የማይታሰብ ነበር። እያለቀስንም ነበር ቀረፃውን የምናደርግ የነበረው።» ብዙውን ስራ የሰራችው ሀድራ ናት የሚለው ንጉሱ « ቃለ መጠይቅ ስታደርግ ጥንቃቄ በማድረግ እንዴት የተጎጂ ቤተሰቦችን ማናገር እንደሚቻል ፣ እንዴት መስመር ሳናልፍ  ሰዎች ታሪካቸውን እንዲነግሩን ማናገር እንደሚቻል።  የተማርኩበትም ነበር» ይላል።
ሀድራ እና ንጉሱ የለፉበትን ይህ ዘጋቢ ፊልም የአሜሪካ ታንክስ ጊቪንግ ምሽት በ ABC News ቴሌቪዥን ጣቢያ በ 2020 እንደታየ እና አሁንም  በዚህ ቴሌቪዥኝ ጣቢያ ወይም ዲስኒ ላይ በተናጥልም ዩ ቲውብ ላይ እንደሚገኝ ገልፆልናል።
ወደ ሀድራ ስንመለስ ፣ ጋዜጠኝነትን በፎርቹን ጋዜጣ እንደጀመረች እና ቀስ በቀስ ሙያዋን እያዳበረች ከአለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋር መስራት እንደቻለች ነግራናለች።  ሀድራ ለዘጋቢ ፊልሟ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሽልማት ስታገኝ ኤሚ አዋርድስ የመጀመሪያዋ አይደለም። ከዚህ ቀደም ህዳሴ ግድብን በሚመለከት የሰራችው ዘጋቢ ፊልም፣ለአውሮጳ ወይም ዩሮቪዥን ለተባለው ሽልማት አብቅቷታል። ሌሎች ለሽልማት የታጩ ዘገባ ፊልሞችም ነበሯት።  እነዚህ እውቅናዎች በተለይ ደግሞ የኤሚ ሽልማት ለወደፊት ስራዎቿ ብርታት ሆኗታል። « ከአሁን በኋላ ጥራታቸውን የጠበቁ ፕሮዳክሽኖች ብቻ መስራት እንዳለብን የተረዳሁበት ነው። በአለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የሆነ ዘገባ መስራት እንደምንችል ያሳየን ሽልማትም ነው» በማለት በአሁኑ ሰዓት ሁለት ዘገባዎች ላይ እየሰሩ እንደሆነ ገልፃልናለች።

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW