ኤምሬቶች የጦር ሰፈር በበርበራ ወደብ ላይ ሊገነቡ ነው
ማክሰኞ፣ የካቲት 7 2009በጦርነት ስትታመስ ከነበረችው ሶማሊያ ራሷን አግላላ የራሷን መንግስት የመሰረተችው ሶማሌላንድ በምክር ቤቷ አማካኝነት ባለፈው እሁድ ያሳለፈችው ውሳኔም የባህረ ሰላጤዋ ሀገር ብርቱ ፍላጎት ውጤት ነው፡፡ የሶማሌላንድ ምክር ቤት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በበርበራ ወደብ የጦር ሰፈር እንድትገነባ ይሁንታውን ሰጥቷል፡፡ በጥቂት ተቃውሞ የጸደቀው የሁለቱ ሀገራት ስምምነት ለ25 ዓመታት እንደሚቆይ ተዘግቧል፡፡
ስምምነቱ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በምትገነባው ወደብ አማካኝነት ማንኛውንም ወታደራዊ ቁሳቁስ ያለቀረጥ እንድታስገባ ያስችላታል፡፡ ጦሯም የበርበራ አለም አቀፍ አየርማረፊያን እንደልብ እንዲጠቀም የሚፈቅድ ነው፡፡ ከተቃዋሚዎች ከፍተኛ ትችትን እያስተናገደ ያለውን ይህን ስምምነት ሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት አህመድ ሲላንዮ ገና ዓለም አቀፍ እውቅና እንኳ ያላገኘችው ሀገራቸው በምትኩ የምትጠቀመውን በማንሳት ተካለክለውታል፡፡
አወዛጋቢ የተባለለት የሁለቱ ሀገራት ስምምነት ለኢትዮጵያ እና ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ያለው ፖለቲካዊ እና መልካምድራዊ አንደምታ እያወያየ ይገኛል፡፡ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላትን መስፋፋት አስመልክቶ ሰፋ ያለ ጽሁፍ ያሳተሙት የጸጥታ ጉዳዩች ተንታኙ አሌክስ ሜሎን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ጠበቅ ያለ ትብብር ቆየት ቢልም ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ ይበልጥ ጠንክሯል ይላሉ፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት የጸደቀው ስምምነት ለኢትዮጵያ ያለውን አንደምታም ያብራራሉ፡፡
“ባለፈው ግንቦት ወር የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የወደብ አንቀሳቃሽ የሆነው DP World የበርበራ ወደብን ለማስተዳደር ኮንትራት አሸንፏል፡፡ በጦር ሰፈሩ ላይ የነበረው ድርድር የቀጠለው ከዚያ በኋላ ነበር፡፡ ይህ በሶማሌላንድ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንደዚሁም በቀሩት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ግንኙነት ላይ በእርግጥም አንደምታ ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በተለይ ይህ ጠቃሚ ነው፡፡ የስምምነቱ አካል የሆነውን የበርበራ መተላለፊያን የመገንባት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ታከናውናለች፡፡ ይህ አውራ ጎዳና ወደብ አልባ ከሆነችው ኢትዮጵያ ተነስቶ ሶማሌላንድን አቋርጦ የሚያልፍ እና የወጪ ገቢ መተላለፊያ የሚሆን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ የሚመጣ ማንኛውም ነገር በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው የሚያልፈው፡፡ ይህ በበርበራ እየተገነባ ያለው አዲስ ወደብ እና ይህ አውራ ጎዳና ለኢትዮጵያ በእርግጠኝነት ትልቅ ልዩነት ያመጣል” ይላሉ፡፡
በጸደቀው ስምምነት መሰረት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከበርበራ ከተማ ዋጃሌ የተሰኘች የወደብ ከተማ ድረስ አውራ ጎዳና ትገነባለች፡፡ የበርበራ አለም አቀፍ አየርማረፊያንም እንድታድስ እና እንደታዘምን ይጠበቃል፡፡ የኤምሬቶቹ ግንባታ ኢትዮጵያን ይበልጥ ወደ በርበራ ወደብ የሚስብና ጅቡቲ በብቸኝነት ተቆጣጥራ የነበረውን የሀገሪቱን የወጪ ገቢ የወደብ አገልግሎት ሌላም የሚያካፍል እንደሆነ አሌክስ ያስረዳሉ፡፡
ኤምሬቶቹ በሶማሌላንድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በኤርትራም ያላቸውን ይዞታ እያጠናከሩ መጥተዋል፡፡ በዚያ የነበራቸውን ጊዜያዊ የጦር መቆያ ወደ ጦር ሰፈር ቀይረዋል፡፡ የተዋጊ አውሮፕላኖች ማረፊያ እና ወደብ በአሰብ ላይ ገንብተዋል፡፡ አሰብን ለጦር ሰፈርነት ለፈቀደው የኤርትራ መንግስትም በምትኩ ጠቀም ያለ እርዳታ እንደሰጡ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
ኤምሬቶች በሶማሊያ ምርጫ ዋና ተዋናይ መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ ከፑንትላንድ ጋርም ጥሩ የሚባል ትብብር አላቸው፡፡ ከግብጽ እና ሱዳን ጋርም ጥብቅ ግንኙነት አላቸው፡፡ “እነዚህ የተባበሩት ኤምሬቶች አካሄዶች ለኢትዮጵያ ስጋት ሊደቅኑ ይችላሉን?”፡፡ በዓለም አቀፉ የደህንነት ተቋም ስትራትፎር ከፍተኛ ተንታኝ ሲም ታክ ጉዳዩን ከሁለት አቅጣጫ ይመለከቱታል፡፡
“በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ስጋት ሊገባት ይገባል ብዬ አላስበም፡፡ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከግብጽ እና ሱዳን ጋር እንዳላቸው ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታም ከኢትዮጵያም ጋር አላቸው፡፡ በየሀገራቱ የሚያፈስሱትን መዋዕለ ንዋይ እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ሀገራት ጋር ግንኙነር ለመመስረት ይጠቀሙበታል፡፡ እንደ ጫና ማሳደሪያነትም ያገለግላቸዋል፡፡ በዚህ መልኩ ካየነው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እያደረገች ካለችው ኢትዮጵያን ነጥሎ ኢላማ የሚያደርግ ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ነገሩን በኢትዮጵያ ምልከታ ካየነው አሁን እየሆነ ያለው ኤርትራን የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ ኤርትራ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ባላት ግንኙነት የምትቀበለው መዋዕለ ንዋይ እና እያደገ የሚመጣው ወታደራዊ አቅሟ በእርግጥም በሆነ ደረጃ ለአዲስ አበባ ተጨባጭ ስጋት ይደቅናል” ይላሉ፡፡
ሁለቱም ተንታኞች የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በአፍሪካ ቀንድ የምትከናውናቸው ይህን መሰል እንቅስቃሴዎች መበራከት ቀጠናው ለባህር ትራንስፖርት እንቅስቃሴ ካለው ቁልፍ ቦታነት የመነጨ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚያ ላይ ከጎርጎሮሳዊው 2015 ጀምሮ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በመጣመር በየመን የሁቲ አማጽያን ላይ የከፈቱት ዘመቻ አለ፡፡ በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉትን የሁቲ አማጽያን መደምሰስ ለሁለቱም ሀገራት ተቀናቃኝ የሆነችው ኢራን አካባቢውን ለመቆጣጠር የምታደርገውን እንቅስቃሴ መግታት በመሆኑ ዘመቻቸውን አጠናክረው ገፍተውበታል፡፡
ተስፋለም ወልደየስ
አርያም ተክሌ