የኤምፖክስ (Mpox) ተሀዋሲ ስጋት
ማክሰኞ፣ ግንቦት 19 2017
ታሪካዊ ዳራ
ፈንጣጣ ከመላው ዓለም መጥፋቱ በዓለም የጤና ድርጅት በይፋ ከተነገረ ዘንድሮ 45 ዓመት ደፈነ። የመጨረሻው የፈንጣጣ ታማሚ የተገኘው በጎርጎሪዮሳዊው 1977 ዓ,ም ሶማሊያ ውስጥ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። በአንጻሩ በመጀመሪያ በእንስሳት ላይ የተከሰተውና ወደ ሰዎች የተዛመተው Mpox ተሀዋሲ ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንዳዲስ በተለያዩ ሃገራት መታየት ጀምሯል።
Mpox ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በእንስሳት ላይ መሆን ተከትሎ አጠራሩ ያንን ማገናኘቱ እንዲቀር የዓለም የጤና ድርጅት በይፋ ከደነገገ ሰነባብቷል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ወንድወሰንም ይህንኑ አጽንኦት በመስጠት በሽታው Mpox ተብሎ መጠራት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት።
መላውን ዓለም ኮቪድ 19 ግራ አጋብቶት ከከረመ በኋላ ስጋቱ ሳያባራ Mpox በሰዎች ላይ መገኘቱን በመጥቀስ የዓለም የጤና ድርጅት ተህዋሲውን በወረርሽኝነት ይፋ አድርጓል። በዚህ ወቅት በምዕራብ አፍሪቃ በተለይም ናይጀሪያ ውስጥ የተከሰተው Mpox ወደተለያዩ የምዕራብ ሃገራት ተዛምቷል። ካለፈው ነሐሴ ወር አንስቶም ዴሞክራቲክ ኮንጎ ምሥራቃዊ ግዛት ውስጥ ዳግም የተከሰተው Mpox ተሀዋሲ ድንበር ተሻግሮ ወደአገራባች ሃገራትም መዳረሱ እየተነገረ ነው።
የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ተቋም ጋር በመሆን ባሳለፍነው የሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ከኬንያ ድንበር አካባቢ ተሐዋሲው ሁለት ሰዎች ላይ መገኘቱን ከመግለጹ ጎን ለጎን ከታማሚዎቹ ጋር በቅርብ ግንኙነት ያላቸውን ሰዎችም እየተከታተለ እንደሆነ ነው የገለጹልን።
ተሀዋሲው በአሁኑ ጊዜ ድንበር እያለፈ ወደተለያዩ ሃገራት መዛመቱ እየታየ እንደመሆኑ ለሕይወት አስጊነቱ እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። ዶክተር ወንድወሰን እንደሚሉት ባለፉት ወራት በMpox ከተያዙት ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡት ጥቂት ናቸው። ከፈንጣጣ ጋር ሲነጻጸርም ምንም እንኳን ተሀዋሲው ተመሳሳይ ዝርያ ቢኖረውም ለሞት የማድረስ አቅሙ የቀነሰ እንደሆነም አመልክተዋል።
መተላለፊ መንገዶች
Mpox ተሀዋሲ በእንስሳም ሆነ በሰዎች አማካኝነት የሚተላለፍ መሆኑ ነው የሚገለጸው። በተለይም የግብረ ሥጋ ግንኙነት እና ጥብቅ ንክኪ ዋነኛ የመተላለፊያ መንገዶች መሆናቸውን ዶክተር ወንድወሰን አስረድተዋል።
Mpox ከሦስት ዓመታት በፊት ሲከሰት መነሻውን ምዕራብ አፍሪቃ አድርጎ ወደ አውሮጳና ሌሎች አህጉራት አዋቂ ወንዶች ላይ ነበር። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፑብሊክ ጀምሮ በምሥራቅ አፍሪቃ ሃገራት የታየውና ከቀናት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ የተረጋገጠው ደግሞ በብዛት ሕጻናትን መያዙንም አስረድተዋል። በሕጻናት ላይ ለመከሰቱም ምናልባት አዋቂዎች በአንድም በሌላ አጋጣሚ የፈንጣጣንም ሆነ ሌሎች ክትባቶችን ማግኘታቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ነው የተናገሩት።
በተሀዋሲው ከተያዙ ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ
በሽታው መኖሩ በምርመራ ከተረጋገጠ ታማሚውን በጥንቃቄ ለመርዳት ለብቻ ማቆየት ወሳኝ መሆኑን ነው የዓለም የጤና ድርጅትም የሚያሳስበው። በሽታ የመቋቋም አቅሙን ለማጠናከር የሚያግዙ ድጋፍ ሰጪ ፈሳሽና ቫይታሚኖችን መስጠትም አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር ወንድወሰን መክረዋል። እንዲህ ያለው ክብካቤም ታማሚው ሌላ የጤና ችግር ከሌለው በስተቀር ለመዳን ያለው ተስፋ እጅግ ሰፊ ይሆናል ነው ያሉት። ከዚህ ባለፈ ግን Mpox ሊከላከሉት የሚቻል በሽታ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
የMpox ተሀዋሲ የተያዘ ሰው በሚታዩበት ምልክቶች ሽፍታ፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ የራስ ምታት፣ የዕጢ እብጠት፣ የቆዳ ቁስለትና ድካም፣ እንዲሁም የጡንቻና የጀርባ ህመም ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ ምልክቶች ሲያጋጥሙ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ ተገቢውን ምርመራና የህክምና አገልግሎት ማግኘት ይኖርባቸዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ እና ተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ወንድወሰን አሞኘ እንደሞከሩት አሁን በውስን ስፍራ የተከሰተው ተሀዋሲ እንዳይሰራጭ ሰዎች በየግል ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም መክረዋል። አለሰጡን ለሙያዊ ማብራሪያ ዶክተር ወንድወሰንን እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ