የኤም-ፖክስ በሽታ ኢትዮጵያ ዉስጥ አንድ ሰዉ ገደለ፣ 19ኝ ሰዉ ያዘ
ዓርብ፣ ሰኔ 6 2017
ከሶስት ሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ የተረጋገጠው (ኤም-ፖክስ) እስካሁን 19 ሰዎች መያዙንናና የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ በተረጋገጠበት ሞያሌ ከተማ እስካሁን በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ ሆስፒታል የገቡት አምስት ሰዎች ናቸውተብሏል፡፡አማራ ክልል ደግሞ በበሽታው የተጠቁ ሁለት ሰዎች መገኘታቸውን ክልሉ አስታውቋል፡፡
ተዋሲው ከአጎራባች አገራት ኬንያ እና ሶማሊያ ወደ የኢትዮጵያ ደቡባቢ ጠረፍ ከተማዋ ሞያሌ የገባበትን ሁኔታ ያስረዱት የሞያሌ ከተማ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሁቃ ዶዮ፤ በአሽከርካሪነት ሙያ የተሰማሩት ግለሰብ ከሶማሌ ወደ ሞያሌ ከተማ ቤተሰቦቻቸው ጋር ስመጡ ተዋሲውን ወደ አራስ ልጅ በማስተላለፍ ነው ብለዋል፡፡ “ጨቅላ ህጻኑ ከ10 ቀናት በኋላ ነው ምልክት ያሳየው፡፡ ወደ ሞያሌ ሆስፒታል ስመጡ የሆስፒታሉ ስፔሻሊስት ሃኪም ናሙናውን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ነው የተረጋገጠው፡፡ ያንን ተከትሎ የጨቅላ ህጻኑ እናትና አባት ናሙና ሰጥተው ተዋሲው እንዳለባቸው በመረጋገጡ ወደ ህክምና ማዕከል ገቡ፡፡ ለህጻኑ የተቻለ ሁሉ የህክምና እርዳታ ብደረግለትም ህይወቱን ማትረፍ ባይቻልም እናትና አባት ከሶስት ሳምነታት በኋላ ሙሉ በሙሉ በማገገማቸው አሁን ድነው ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ወቅታዊውን የተዋሲውን ስርጭት በማስመልከት ይፋ ባደረገው መግለጫ እስካሁን በኤምፖክስ በሽታው የተያዙ ታማሚዎች ቁጥር 19 መድረሱ ሲረጋገጥ በበሽታው ከተያዙት ታማሚዎች መካከል የአንድ ወር ሕጻን ሕይወት ማለፉን ተናግሯል።
አምስት (5) ታካሚዎች ከቫይረሱ አገግመው መውጣታቸውን ያረጋገጠው ጤና ሚኒስቴር፤ ለበሽታው አጋላጭ የሆነው በበሽታው እንደተያዘ ከተጠረጠረ ሰው ጋር የሚኖርን ንክኪ ባለማድረግ መከላከል እንደሚቻልም አውስቷል፡፡
በተዋሲው የተጠቃ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘባት ሞያሌ ግን የበሽታው ተጠቂዎች እንዳይሰፉ በሚል ርብርብ መደረጉን የሚነሱት የሞያሌ ከተማው ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሁቃ ዶዮ፤ “የበሽታው መረጋገጥን ተከትሎ ይህ በሽታ ከተማችን ውስጥ ሳይስፋፋ አይቀርም በሚል ስጋት ወዲያ ያደረግነው በ28 ሺህ አባወራዎች ቤት አሰሳ ወደ ማድረግ ነው የገባነው፡፡ በዚያም ምልክቱን ያሳዩ ዘጠን ሰዎችን ለይተን ከነዚያም መካከል ሁለት ሰዎች ብቻ ላይ በሽታው መኖሩን ካረጋገጥን በኋላ ወደ ማዕከል ያስገባናቸው የተዋሲው ተጠቂዎች አምስት ደረሱ፤ ህጻኑ ህይወቱ ሲያልፍ ቤተሰቦች አገግመው ወትተዋል አሁን እኛ ጋ በህክምና ላይ የሚገኙ ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡፡ እነሱም በመልካም ጤንነት ላይ ስለሚገኙ ከሳምንት በኋላ ማህበረሰቡን ይቀላቀላሉ ብለን እንጠብቃለን” ብለውናል፡፡
ይሁንና ወደ ህክምና ማዕከላት ሳይመጡ አስቀድሞ የተያዙና ኬንያ ድንበር ተሻግረው ትምህርት ተከታትለው የሚመላለሱ አምስት ተማሪዎች ወደ ህክምና ማዕከል ሳይመጡና በተዋሲው መያዛቸው በጤና ተቋማት ከመረጋገጡ አስቀድሞ ከበሽታው ማገገማቸውም ተነግሯል፡፡ እንደ ሃላፊው ማብራሪያም አሁን ላይ ከተዋሲው መስፋፋት ጋር ያለው ስጋት አከባቢው ድንበር ላይ መሆኑና ማህበረሰቡ ተቀላቅለው የሚውሉ መሆኑ ነው፡፡ “አሳሳቢ ነገርማ አለ፡፡ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ኦሮሚያ ጤና ቢሮ እና የወረዳው ጤና ዘርፍ ሃላፊዎች ከዓለም ጤና ድርጅት ጭምር ከተመደቡ ባለሙያዎች ጋር በመሆን 24 አባላትን ያቀፈ ቡድን መስርቶ ስንሰራ በመቆየታችን ጥሩ ውጤት ተገኝቷል፡፡ ነገር ግን ህዝባችን ዓለማቀፋዊ ድንበርን ወዲህም ወዲያም እየተሻገሩ ተቀላቅለው ስለሚውሉ በኬንያ መንግስትም በኩል ተመሳሳይ እርምጃ ተወስዶ የማጣራትና ክትትል ስራ ካልተሰራ ስጋት ላይ ነው የሚጥለን” በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልልም ሁለት በተዋሲው የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን ክልሉ አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ እንዳሉት “እንደ እኛ ክልል በዚህ በሽታ ተጠርትረው ናሙና ተልኮ የተረጋገጡ ሁለት ህሙማን እስካሁን ተገኝተዋል” ብለዋል፡፡ ህሙማኑ በምዕራብ ጎንደር ሁመራ እና ባህርዳር ከተማ መገኘታቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ አሁን ላይ ሁለቱም ህሙማን ከበሽታው ስለመዳናቸውም አመልክተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ