1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራና የትግራይ ኃይላት ፍጥጫ

ሐሙስ፣ ሰኔ 2 2014

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተስፋዬ ሰላሙን በማምጣቱ ረገድ ላይ ግንጽነትንም ጭምር በማስፈን የኢትዮጵያ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ መጣወት ብችል ባይ ናቸው፡፡

Grenzgebiet zwischen Eritrea und Äthiopien
ምስል AP

ዉጥረቱ ለቀጠናው ሌላ ስጋት ያጠላል-ፖለቲከኞች

This browser does not support the audio element.

በሰሜን ኢትዮጵያ በኤርትራ ድንበር አዋሳኝ አከባቢ በትግራይ ሃይሎች እና በኤርትራ መንግስት ሰራዊት መካከል የሚስተዋለው ውጥረት ለቀጠናው ሌላ አስከፊ ስጋት እንዳይደቅን  ፖለቲከኞች ገለጹ፡፡አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የገለጹት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች እንደሚሉት የኢትዮጵን የውስጥ ጉዳይ በሰላማዊ ሁኔታ መፍታት ግጭቶችን ድንበር ከመሻገር መቆጣጠርም ይቻላል፡፡የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘውን ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት)ን በኤርትራ ላይ ተደጋጋሚ የግጭት ሙከራ በማድረግ ጥረት በተደጋጋሚ ሲከስ ይስተዋላል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ መንግስትን የሚፋለመውና በኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታትን ወደ ጦርነት ለማስገባት ፍላጎት እንዳለውም የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ ባለፈው ሳምንት ለዶይቼ ቬለ አብራርተው ነበር፡፡
የህወሓት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ባለፈው ሳምንት የትግራይ ኃይሎች የኤርትራ መንግስት ሰራዊትን ጥቃት መመከቱንም ማሳወቃቸው አይዘነጋም፡፡ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተስፋዬ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት እንዳብራሩት ይህ በትግራ ኃይሎች እና በኤርትራ መካከል እንዳያገረሽ የሚያሰጋው ግጭት አስከፊ ገጽታ ሊኖረው እንደሚችል በማመልከት የግጭቱን መነሻ ከወዲሁ መግታት ቢቻል ይላሉ፡፡ 
እንደ ፖለቲከኛ መስፍን ገለጻ ከ2010ሩ የኢትዮጵያ መንግስታዊ ለውጥ በኋላ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የመጣው የሰላም አየር ወደ ታች በተለይም ወደ ትግራይ ክልል ወርዶ ያልተስተዋለ መሆኑ እና ከአንድ ዓመት በፊት በትግራይ በተካሄደው ጦርነት የኤርትራ ሰራዊት በሰብዓዊ መብት ጥሰት መከሰሱ የሁለቱን ወገኖች ቁርሾ ያባብሳል፡፡ ሌላኛው ፖለቲከኛ አቶ ሙላቱ ገመቹ ስለአሁናዊ የሰሜን ኢትዮጵያው ሌላው ስጋት ሀሳባቸውን ካጋሩን ናቸው፡፡ አቶ ሙላቱ ገመቹ ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እልባቱ ሰላማዊ የሆነ መፍትሄ መፈለግ ብቻ ነውም ብሏል፡፡ 
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ተስፋዬ ሃሳቡን በመጋራት ሰላሙን በማምጣቱ ረገድ ላይ ግን ግልጽነትንም ጭምር በማስፈን የኢትዮጵያ መንግስት የአንበሳውን ድርሻ መጫወት ቢችል ባይ ናቸው፡፡
ስዩም ጌቱ
ኂሩት መለሰ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW