የኤርትራው ፕሬዝደንት የግብጽ ጉብኝት አንድምታ
ዓርብ፣ ጥቅምት 21 2018
የኤርትራው ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ አፍወርቂ በግብጽ የአምስት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ካይሮ ይገኛሉ። የኤርትራው ፕሬዝደንት ወደ ካይሮ ያቀኑት የግብጹ ፕሬዝደንት አብደልፋታሕ አልሲሲ ባደረጉላቸው ግብዣ ነው ተብሏል። የፕሬዝደንቱ የካይሮ ጉብኝት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያበቀይ ባሕር ያላትን የተጠቃሚነት ፅኑ አቋም ለምክርቤት በተናገሩ ማግስት መሆኑ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
ሁለቱም መሪዎች የሁለቱን ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግኑኝነት ይበልጥ ለማጠናከርና ለሁለቱም ሃገራት በሚጠቅሙ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንደሚወያዩ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው አስፍሯል።
«በጣም አደገኛ አካሄድ በመሆኑ»
የፕሬዝደንቱ ጉብኝት በኤርትራናበግብጽእንደሚደገፍ የሚነገረው የሱዳን ጦር በዳራፉር ያጋጠመው ሽንፈትና የፈጥኖ ደራሽ ሐይሎች የኤፋሽር ከተማን መቆጣጠራቸውን፤ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዚህ ሳምንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በሰጡት ማብራሪያ «የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልከዓ ምድራዊና ኤኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው» ማለታቸውን ተከትሎ በመሆኑ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
የጉብኝቱን አንድምታ በማስመልከት ካነጋገርናቸው፤ ኤርትራዊው የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አብዱራሕማን ሰይድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሰጡት ማብራሪያ የኤርትራ ታሪካዊ የቅኝ ግዛት ውሎችና የኤርትራ ሉዓላዊነትን ያላገናዘበ እንደሆነ ነው የገለጹት። ጉብኝቱን በሚመለከት ደግሞ እንዲህ ብለዋል።
«ግብጽና ኤርትራ ጥብቅ ግኑኝነት አላቸው። እና የኤርትራ ባለስልጣናትና የብጽ ባለስልጣናት ጉብኝት ይፈጽማሉ በእያንዳንዳቸው አገሮች፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ሁለት ታላላቅ ነገሮች አሉ እዛ አካባቢ። አንደኛው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ አካሄድ ሲሆን እሱ ደግሞ በጣም አደገኛ አካሄድ በመሆኑ፤ ሁለተኛው ደግሞ ኤልፋሽር በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ እጅ በመውደቋ ለግብጽ ብዙ ስጋት ይፈጥራል። እንዲሁም ለኤርትራም ሊፈጥር ይችላል።»
«ተያያዥነት አላቸው ብሎ ለመደምደም በጣም ያስቸግራል»
ሌላው ያነጋገርናቸው የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ዩሱፍ ያሲን ናቸው። እሳቸው እንዳሉት ሃገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር በአቋም የሚመሳሰለቸውን ሐገር ከጎናቸው ማሰለፍ የተለመደ ቢሆንም የአቶ ኢሳያስ አፍወርቂ የካይሮ ጉብኝት ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ጋር የሚገናኝ አይመስለኝም ባይ ናቸው።
«የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር የፓርላማው ንግግርና የአቶ ኢሳያስ የካይሮ ጉዞ ቀታ ተያያዥነት አላቸው ብሎ ለመደምደም በጣም ያስቸግራል።
በሌላ በኩል ግን አሉ አቶ ዩሱፍ ያሲን፤ በሌላ በኩል ግን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች በየጊዜው ስለቀይባሕር የሚሰጡ መግለጫዎች የዲፕሎማሲ ሂደቱን እንደሚያበላሽ ይናገራሉ።
አቶ ዓብዱራህማን ሰይድ በበኩላቸው የኤርትራው ፕሬዝደንትአንዱ የጉብኝታቸው አካል በግብጽ በነገው ዕለት በሚካሄድ የአንድ ታላቅ ሙዚየም ምረቃ ሥርዓት ለመሳተፍ ነው ቢባልም፤ በዋናነት ግን በኢትዮጵያ በኩል ይታያል ያሉትን በኃይልም ጭምር ቀይባሕርን የመቆጣጠር አዝማሚያና የሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ መነጋገሪያ አጀንዳዎቻቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገምታሉ።
አቶ ዩሱፍ ያሲን በበኩላቸው በኢትዮጵያ በኩል በቀይባሕር ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር የምትችለው በመጀመሪያ በአባይ ተፋሰስ ሃገራት እንደተሠራው ዲፕሎማሲ በቀይባሕር ተጎራባች አገሮች ላይም ተመሳሳይ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በመቅደም ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሰ