የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ገቡ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 19 2010ማስታወቂያ
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌሕ የተመራ የኤርትራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ እና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኦስማን ሳሌሕ ጉንጉን አበባ ከአንገታቸው አጥልቀው ተቀብለዋቸዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነሕ ገበየሁ፣ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ዶክተር አርከበ እቁባይ እና የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ብርሀኑ ጁላ ገለልቻ በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት ለሁለት አስርት አመታት ገደማ በሁለቱ አገራት መካከል ሰፍኖ የቆየው ውጥረት ማብቂያ እንደሆነ የጠቅላይ ምኒስትር ፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ፍጹም አረጋ በትዊተር ገፃቸው ጽፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የኤርትራ ልዑካን ቡድን ጉብኝት ለተሻለ መፃኢ ጊዜ መሠረት እንደሚጥል ተስፋ እንዳላቸው አቶ ፍጹም አረጋ ገልጸዋል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ