1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያረጋግጥ ምስክር አላገኘሁም» የአውሮጳ ልዩ ልዑክ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 7 2013

"በጉብኝቴ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያረጋግጥ ምስክር ማየትም ሆነ መስማት አልቻልኩም። እንዲያውም በአንዳንድ የትግራይ ቦታዎች ማጠናከሪያ እንደተጨመረላቸው የሚገልጽ የተወሰነ መረጃም አግኝቻለሁ" ሲሉ የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ ፔካ ሐቪስቶ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት ወታደሮቹ መውጣት መጀመራቸውን ገልጻ ነበር

EU Pekka Haavisto
ምስል Olivier Hoslet/AFP

የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያረጋግጥ ምስክር አላገኘሁም-የአውሮፓ ልዩ ልዑክ

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ አቅንተው ትግራይን የጎበኙት የአውሮፓ ኅብረት ልዩ ልዑክ ፔካ ሐቪስቶ መንግሥት ያፋ ባደረገው መሠረት የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ለመውጣታቸው ማረጋገጫ እንዳላገኙ ተናገሩ።

የፊንላንዱ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ፔካ ሐቬስቶ ከመጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵዮያ ባደረጉት ጉብኝት ወደ ትግራይ የተጓዙ ሲሆን ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና ከምክትል ጠቅላይ ምኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ደመቀ መኮንን ተወያይተዋል። በጉዟቸው የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ግፊት ማድረግ ከዋንኛ ጉዳዮቻቸው አንዱ ነበር።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ለቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች መግለጫ በሰጠው ምላሽ "በህወሓት ተቆስቁሰው ድንበር የተሻገሩት የኤርትራ ወታደሮች ለቀው መውጣት ጀምረዋል" ብሎ ነበር።

በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የአውሮፓ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሐቪስቶ "በጉብኝቴ ወቅት የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያረጋግጥ ምስክር ማየትም ሆነ መስማት አልቻልኩም። በተቃራኒው በትግራይ እና በመቐለ ጉብኝቴ ያነጋገርኳቸው ኤርትራውያን በትግራይ መገኘታቸውን ነግረውኛል። እንዲያውም በአንዳንድ የትግራይ ቦታዎች ማጠናከሪያ እንደተጨመረላቸው የሚገልጽ የተወሰነ መረጃም አግኝቻለሁ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከተደጋጋሚ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ማስተባበያዎች በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ድንበር አቋርጠው ወደ ትግራይ መግባታቸውን ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያረጋገጡት መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ነው።

የኤርትራ ወታደሮች "ያለ ቅድመ-ሁኔታ በፍጥነት" ከኢትዮጵያ ሊወጡ እንደሚገባ የጠየቁት የቡድን ሰባት አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች ሒደቱ "ሊረጋገጥ የሚችል" መሆን አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኤርትራ ወታደሮች መውጣት መጀመራቸውን ሲገልጽ ስለ ቁጥራቸው ማብራሪያ አላቀረበም። ወታደሮቹ ሙሉ በሙሉ የሚወጡበት ጊዜም አልተገለጸም። በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ምኒስትር ጽህፈት ቤት በኢ-ሜይል እና በቀጥታ ስልክ በመደወል ዶይቼ ቬለ ማብራሪያ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም። 

ባለፈው መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በአስመራ ከተወያዩ በኋላ  የኤርትራ መንግሥት ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች ወታደሮቹን ለማስወጣት የደረሱበት ሥምምነት "ይተገበራል የሚል ዕምነት" መኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ "የኤርትራ ወታደሮችን በሚመለከት ክቡር ጠቅላይ ምኒስትር ዶክተር ዐቢይ አስመራ ሔደው ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው በነበረበት ወቅት የተስማሙበት ጉዳይ ነው። ይኼ ይተገበራል የሚል ዕምነት ነው ያለው" ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ ያደረግናቸው የስልክ ጥሪዎች ምላሽ አላገኙም። ባለፈው ሳምንት የኤርትራ ወታደሮች "በሒደት" እንደሚወጡ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በፍጥነት ተግባዊ እንደማይሆን መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የኤርትራ መንግሥት እስካሁን ድረስ ወታደሮቹ ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ ስለመግባታቸው በይፋ ማረጋገጫ አልሰጠም። ዶይቼ ቬለ ወደ ኤርትራ ማስታወቂያ ምኒስትር የማነ ገብረ መስቀል ቢሮ ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች አልተነሱም።

የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ የሚጠይቅ መልዕክት ይዘው ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የአውሮፓ ልዩ ልዑክ ፔካ ሐቪስቶ ሲመለሱ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንደተባለው ወጥተው ቢሆን ኖሮ እናውቅ ነበር ብለዋል።

ፔካ ሐቪስቶ "በአካባቢው ከምናነጋግራቸው ሰዎች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት፣ የሐይማኖት መሪዎች እና ሌሎች ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሚያሳውቁ መረጃ ለማግኘት እየተጠባበቅን ነው። ነገር ግን የኤርትራ ወታደሮች በከፍተኛ ቁጥር ወጥተው ቢሆን ኖሮ እኛም እናውቅ፣ በአካባቢው የሚገኙ ሰዎችም ይነግሩን ነበር።  የኤርትራ ወታደሮች ለቆ ወውጣት ለትግራይ ኹኔታ መፍትሔ ለማምጣት የመጀመሪያው እርምጃ ነው" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

በትግራይ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከ62 ሺሕ በላይ መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል። በድርጅቱ ትንበያ መሠረት እስከ 1.3 ሚሊዮን ሰዎች ዕርዳታ ጠባቂ ይሆናሉ። በክልሉ የግብረ-ሰናይ ተቋማት እንቅስቃሴ መሻሻል ማሳየቱን የተናገሩት ፔካ ሐቪስቶ በጉብኝታቸው አሁንም ፈታኝ ችግሮች መኖራቸውን እንደተረዱ አስረድተዋል።

"ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት እጅግ በጣም ጥሩ ሥራ እያከናወኑ ነው። በትግራይ ወደሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች በተሻለ መድረስ ችለዋል። ነገር ግን በአንዳንድ ቦታዎች በውጊያ ምክንያት ለመቆም መገደዳቸውን ነግረውናል። ስለዚህ አሁንም ውጊያ እየተካሔደ መሆኑን እየታዘቡ ነው" ብለዋል።

ፔካ ሐቪስቶ "ከዚህ በተጨማሪ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልን ጎብኝተን በሕሙማን መጨናነቁን ተመልክተናል። ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች እና ሕፃናት፤ እንዲሁም በጥይት የቆሰሉ ሰላማዊ ሰዎች አሁንም ወደ ሆስፒታሉ ይመጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከምዕራባዊ ትግራይ በኃይል የማፈናቀል ተግባር አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን መረጃ አግኝተናል። በየቀኑ አንድ ሺሕ አዳዲስ ተፈናቃዮች ሽሬ ከተማ ይደርሳሉ" ብለዋል።

ልዩ መልዕክተኛው “ከምዕራባዊ ትግራይ በኃይል የማፈናቀል ተግባር አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን መረጃ አግኝተናል” ብለዋል።ምስል Baz Ratner/REUTERS

ልዩ መልዕክተኛው እንደ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የቡድን ሰባት አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች ሁሉ ለትግራይ ቀውስ መፍትሔ ለማበጀት የኤርትራ ወታደሮች ለቀው ሊወጡ እንደሚገባ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ፔካ ሐቪስቶ "እንዲህ አይነት ግጭቶች ማብቂያ የሚያገኙት በድርድር ብቻ ነው። ለመንግሥት፣ ለአማራ ሚሊሺያ፣ የደፈጣ ውጊያ ለገጠሙት እና ለኤርትራ ወታደሮች የምንሰጠው ምክር መጀመሪያ የኤርትራ ወታደሮች መውጣት አለባቸው። ከዚያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያ ባለድርሻዎች ሊደራደሩ ይገባል። ግጭቱ በተራዘመ ቁጥር መደራደር አስቸጋሪ እየሆነ ይሔዳል። ምክንያቱም ወጣቶች ለደፈጣ ውጊያ እየተመለመሉ ነው። ወደ ፊትም ተጨማሪ ወጣቶች ሊቀላቀሉ ይችላሉ። ይኸ ደግሞ ጥሩ አይደለም። በመንግሥት፣ በሲቪክ ማህበራት እና በትግራይ ተወካዮች መካከል ሐቀኛ ውይይት ሊደረግ ይገባል" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ዛሬ በኢትዮጵያ የትግራይ ቀውስ ላይ እንደሚወያይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል። በውይይቱ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ እና የአስቸኳይ ዕርዳታ ጉዳዮች አስተባባሪ ማርክ ሎውኮክ ለጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ አባላት ማብራሪያ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW