የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያ ድንበርን አቋርጦ መዝለቁን ተነገረ
ረቡዕ፣ መስከረም 27 2019
በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ከዕዳጋ ሓሙስ ወደ አፅቢ በሚወስደው መንገድ ይጓዙ የነበሩ የኤርትራ ወታደሮች ዕዳጋ ዓርቢ በተባለ ቦታ ሲደርሱ የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የትግራይ የሰላም ኃይል አንድ ወታደራዊ አዛዥ ገለጹ። የኤርትራ ወታደሮች በዛሬው ዕለትከዛላምበሳ አቅጣጫ የዓዲ ግራት ከተማን ጥሰው ዕዳጋ ሐሙስ ከተማ መግባታቸውን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የትግራይ የሰላም ኃይል አዛዥ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በምዕራባዊ የትግራይ ክፍልም በሸራሮና ሽረ እንዳስላሰ ከተሞች መሐል በሚገኙ ዓዲ ነብሪ ኢድና ዛግር ወደ ተባሉ አካባቢዎች መግባታቸውንም ገልጸዋል።
አንድ የዓዲ ግራት ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው የኤርትራ ወታደሮች የዓዲግራት ከተማን ጥሰው በማለፍ ወደ ዕዳጋ ሓሙስ መግባታቸውን እንደተመለከቱ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ለማነጋገር ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ፣ ለመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይና ለኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር በእጅ ስልኮቻቸው ብንደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የገለጹት የትግራይ የሰላም አዛዥ እንደሚሉት ዕዳጋ ሓሙስ ከገቡትየኤርትራ ወታደሮች ወደ አፅቢ ወንበርታ አቅጣጫ በ2 የጭነት መኪኖች ተጭነው በሚጓዙበት ወቅት በድሮን ተመተዋል። ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ የሚዋጋው ታጣቂ ቡድን አመራር ተፈጽሟል ያሉትን የድሮን ጥቃት ዶይቼ ቬለ በገለልተኝነት አላረጋገጠም።
በዚህ ዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን ከሰባሰበው ከባልደረባችን ታምራት ዲንሳ አጭር ቆይታ አድርገናል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
እሸቴ በቀለ