1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤርትራ ነፃነት፤ ጦርነት፤ ድሕነት እና ስደት

ሐሙስ፣ ግንቦት 16 2010

ኤርትራ፤ ተቺዎች እንደሚሉት አሁን «የአፍሪቃ ሰሜን ኮሪያ ናት።» ምርጫ የለም። ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች በቅርቡ ባወጣዉ የፕረስ ነፃነት ዝርዝር ከኤርትራ የባሰች ሐገር ብትኖር አንድ ናት። ሰሜን ኮሪያ። መንግሥትን የሚተቹ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ይታሰራሉ። የታሰሩት ያሉበት አይታወቅም።

Eritrea Bevölkerung feiert Referendum 1993
ምስል Getty Images/AFP/A. Joe

NM - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የራስዋን መንግሥት በይፋ ከመሠረተች ዛሬ 25 ዓመት ደፈነች። የኤርትራ ሕዝብ በሰጠዉ ድምፅ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ግዛት ዓለም አቀፍ እዉቅና ያለዉ ነፃ መንግሥት ከማወጅዋ ከሁለት ዓመት በፊት ለነፃነት ይዋጉ የነበሩት የቀድሞ አማፂያን ሐገሪቱን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋት ነበር። የቀድሞዎቹ አማፂያን የመሠረቱት መንግሥት ትንሺቱን ምሥራቅ አፍሪቃዊት ሐገር የመላዉ አፍሪቃ የልማት ዕድገት አብነት እንደሚያደርጓት ተስፋ ሰጥተዉ ነበር። ተስፋዉ ግን፤ የዶቸ ቬለ ዳንኤል ፔልስ እንደዘገበዉ፤ ብዙ አልቆየም። ኤርትራ ዛሬ ብዙ ተንታኞች እንደሚተቹት «የአፍሪቃ ሰሜን ኮሪያ» ናት። የፔልስን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

ስዊድን የምትኖረዉ ኤርትራዊት ሜሮን እስጢፋኖስ ዛሬ ለዋለዉ የኤርትራ የነፃነት ቀን ደንታ የላትም። «በትግሪኛ የሐገር ነፃነት ማለት የሰዎች ነፃነት ማለትም ነዉ» ትላለች፤ የ44 ዓመቷ የመብት ተሟጋች።«በዚሕም ምክንያት» ቀጠለች ሜሮን-ዳንኤል ፔልስ እንደጠቀሰዉ፤ «ብዙ ሰዎች፤ ማንም ሰዉ ነፃ ሳይወጣ፤ የነፃነት ቀን የምናከብረዉ ለምድነዉ?» እያሉ ይጠይቃሉ ትላለች።
ከሐገሯ የወጣችዉ በ12 ዓመቷ ነዉ። አሁንም ግን ከወገኖችዋ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላት። ለአደጋ የተጋለጡ ሥደተኞች ሥለምትረዳ አንዳዶች «እማማ ሜሮን» ይሏታል።
                              
«ስውአኑ የሞቱት ለኤርትራ ነፃነት ነዉ። የነሱ ልጆች ግን በመላዉ ዓለም ተበትነዋል። ሜድትራንያን ባሕር፤ ሲና በረሐ፤ ሰሐራ በረሐ ይሞታሉ። ታጋዮቻችን የተሰዉት ለዚሕ አልነበረም። ስደት እንዲቆም፤ ዴሞክራሲያዊት ኤርትራ እንድትመሠረት፤ ፍትሕ እንዲፀና ነበር።»

የዛሬ ሃያ-አምስት ዓመት የዛሬን ቀን የኤርትራ ነፃነት ሲታወጅ ርዕሠ ከተማ አስመራ-በደስታ፤ ፌስታ ፈንጠዝያ ተደበላልቃ ነበር። ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በደስታ ባሕር ይዋኝ ለነበረዉ ሕዝባቸዉ ባደረጉት ንግግር «ዛሬ የኤርትራ ዳግማዊ ልደት ነዉ። ለተፋለሙት በሙሉ ልዩ ካሳ ነዉ።» ብለዉ ነበር።
አዲሲቱ ሐገር የመላዉ አፍሪቃ የልማት ዕድገት ተስፋ እንደምትሆንም የፕሬዝደንት ኢሳያስ መንግሥት ቃል ገብቶ ነበር። ብሪታንያዊቱ የኤርትራ ጉዳይ አጥኚና ደራሲ ሚሼኤላ ሮንግ እንሚሉት ደግሞ በ1987 አስመራን የጎበኙበት ወቅት «ልዩ ጊዜ ነበር»። «ኤርትራ ከሙስና የፀዳች፤ መንግሥቷ ለሁሉም ክፍት፤ የፈለገዉ ሰዉ በፈለገ ጊዜ ሚንስትሩን ማናገር የሚችልባት ሐገር ነበረች። ብዙዎችን ያማለለች» አከሉ።
                                           
«በ1970ዎቹ ተሰደዉ የነበሩ ኤርትራዉያን በብዛት ወደ ሐገራቸዉ እየተመለሱ፤ መዋዕለ ንዋያቸዉን ሥራ ላይ እያዋሉ ነበር። ልምድ እና እዉቀታቸዉን ይዘዉ እየተመለሱ ነበር። ፋብሪካ ለመክፈት ያቀዱ ነበሩ። የማያቋራጥ የግንባታ ድምፅ ይሰማ ነበር።በየስፍራዉ የተከለለ የግንባታ ሥፍራ ነበር።»
ተስፋ፤ ቃል፤ ልዩ ጊዜዉም ብዙ አልቆየም። በነነ። ኢትዮጵያን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስነዉ ድንበር በቅጡ ባለመካለሉ በ1990 ሌላ ጦርነት ፈነዳ። ጦርነቱ፤ ፔልስ እንደፃፈዉ፤ ኤርትራን ባረባየ ሽንፈት ነዉ ያበቃዉ። በፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ የሚሰነዘረዉ ትችት ተጠናከረ። «ኢሳያስ የቀድሞ ሚንስትሮች እና ታጋዮችን ሳይቀር የሚተቿቸዉን ሁሉ ባንድ ጊዜ እስር ቤት ወረወሯቸዉ»  ደራሲ ሮንጎ እንዳሉት።

ምስል picture-alliance/dpa/S. Forrest

ኤርትራ፤ ተቺዎች እንደሚሉት አሁን «የአፍሪቃ ሰሜን ኮሪያ ናት።» ምርጫ የለም። ድንበር የለሽ ዘጋቢዎች በቅርቡ ባወጣዉ የፕረስ ነፃነት ዝርዝር ከኤርትራ የባሰች ሐገር ብትኖር አንድ ናት። ሰሜን ኮሪያ። መንግሥትን የሚተቹ ባለሥልጣናት ሳይቀሩ ይታሰራሉ። የታሰሩት ያሉበት አይታወቅም። የዉጪ ጋዜጠኞች እና የመብት ተሟጋቾች የመግቢያ ፍቃድ አይሰጣቸዉም። ዲፕሎማቶች ሳይቀሩ ከአስመራ ዉጪ መንቀሳቀስ የሚችሉት መንግሥትን አስፈቅደዉ ነዉ።
 የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የኤርትራ ጉዳይ ልዩ አጥኚ ሺይላ ኬታሩት «የሰብአዊ መብት ጥሰቱ አሳሳቢ ነዉ።» ይላሉ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የዛሬ ሁለት ዓመት የኤርትራ መንግሥትን ሰዎችን በባርነት በማሰቃየት፤ በመድፈር እና ማንገላታት ተጠያቂ አድርጎታል። 
ሰብአዊ መብት ከሚጣስባቸዉ እና ወጣቶችን ለስደት ከሚዳርጉ ምክንያቶች አንዱ ብሔራዊ አገልግሎት ነዉ። በትወራ ደረጃ 18 ዓመት የሞላዉ ኤርትራዊ ለተወሰነ ጊዜ ወታደራዊ እና ሌሎች አገልግሎቶች የሚሰጥበት ግዳጅ ነዉ። ብዙዎች ግን ለመንግሥት ገደብ የለሽ አገልግሎት የሚሰጥበት ነዉ ባዮች ናቸዉ።

ምስል Getty Images/AFP/M. Deghati

የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በ2007 ዙድ ዶቸ ሳይቱንግ ለተባለዉ የጀርመን ጋዜጣ «እዚሕ ሐገር ማንም ሰዉ እታሰራለሁ ብሎ ሳይፈራ ስለ ሐገሪቱ መንግሥት መናገር ይችላል።» ብለዉ ነበር። ኤርትራ ዉስጥ ምርጫ ላለመደረጉም ከኢትዮጵያ ጋር ያለዉ ግጭት መፍትሔ አለማግኘቱን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር እየተበራከተ ከመጣ ወዲሕ ጀርመንን ጨምሮ ጥቂት ምዕራባዉያን መንግሥታት ከአስመራ ጋር ያላቸዉን ግንኙነት ለማሻሻል አንዳድ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል። በ2007 የቀድሞዉ የጀርመን የልማት ሚንስትር ጌርድ ሙለር አስመራን ሲገበኙ ባመቱ አንድ የኤርትራ ከፍተኛ የባለሥልጣናት ቡድን በርሊንን ጎብኝቷል። የሰብአዊ መብት አጥኚ ኬይታሩት ግን ምን ተገኝቶ? ይላሉ 
                                 
«አንዳድ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተዋኞች ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለመገናኘት ጥሪት እያፈሰሱ ነዉ።ከኤርትራ ጋር ያላቸዉን ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ ባለፉት ሰወስት ዓመታት እየጣሩ ነዉ። እኔ ግን ጥያቄ አለኝ። ከዚሕ ቀደም ያነሳሁት መሠረታዊዉ የሰብአዊ መብት ይዞታ በተጨባጭ ምን መሻሻል ተገኝቷል?»
መሻሻል ወይም ለዉጥ የለም። መቼ እና እንዴት እንደሚመጣም አይታወቅም። ከቅርብ ዓመታት ወዲሕ ሥለ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ጤና ማጣት የሚናፈሰዉ አሉባልታ እየተደጋገመ ነዉ። ሰዉዬዉ አንድ ቀን አንድ ነገር ቢሆኑ ምናልባት ለዉጥ ሊመጣ ይቻላል ባዮች አሉ። ደራሲ ሮንግ ግን ሥልጣኑ ከብዙዎቹ የኢሳያስ ጄኔራሎች ካንዱ እጅ አያመልጥም ባይ ናቸዉ-ደራሲዋ።
«ለዉጥ አይቀርም የሚል እሳቤ አለ።ኤርትራ በጦር ኃይል የምትገዛ ናት።ብሔራዊ ሸንጎዉ እና የፍትሕ ሥርዓቱን የመሳሰሉ ተቋማት ትክክለኛ ሥልጣን የላቸዉም።ሐገሪቱን የሚገዛዉ ጦሩ ነዉ።ሥለዚሕ ኢሳያስ አፈወርቂ ጡረታ ቢወጡ ወይም ቢሞቱ ብዙ ጄኔራሎች አሉ።ከነሱ በታች ደግሞ የወጣቱን ስሜት የሚጋሩ ወጣት የጦር መኮንኖች አሉ።ዴሞክራሲያዊ መንግሥት  ለመመስረት የሚደረግ እንቅስቃሴ ይኖራል ብዩ ግን አላምንም።እንደ ሚመስለኝ አንዱ ጄኔራል ሥልጣኑን ከኢሳያስ የመዉረስ እድሉ ሰፊ ነዉ።»የመብት ተሟጋች ሜሮን እስጢፋኖስ በበኩሏ ኤርትራዉያን ለሐገር ነፃነት ታግለናል ትላለች።ለዜጎች ነፃነት ደግሞ ትግሉ ይቀጥላል።

ምስል Getty Images/AFP/A. Joe

ዳንኤል ፔልስ 

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW