የኤርዶሀን ተቃዋሚዎች
ሐሙስ፣ መጋቢት 14 2009« ነፃነቷን በተግባር የምታሳይ እያንዳንዷቱርካዊት በህዝበ ውሳኔው ማሻሻያውን አልቀበልም ስትል ድምጿን መስጠት አለባት ፤ ትላለች ወጣቷ ኑርችያን ባስ ። በምዕራብ ጀርመንዋ በኮሎኝ ከተማ ኖይማርክት በተባለው የገበያ ማዕከል ባለፈው ቅዳሜ እርስዋና ሌሎች ተቃዋሚዎች ፣ቱርኮች የህገ መንግሥት ማሻሻያ መደረጉን ተቃውመው ድምጽ እንዲሰጡ ሲቀሰቅሱ ነበር ። አስተባባሪያቸው ጉኒ ካፓንም ሆኑ ሌሎቹ ተቃዋሚዎች የፍትህ እና የልማት ፓርቲ በምህፃሩ AKP የተባለው የቱርክ ገዥ ፓርቲ አባላት አይደሉም ። በህዝበ ውሳኔው ድምፅ የሚሰጡ ቱርኮችን ለማሳሰብ የተሰባሰቡ የቱርክ ዜጎች እንጂ ። ካፓን እንደሚሉት ችግሩ አብዛኛዎቹ ቱርኮች ስለ ህዝበ ውሳኔው ምንነት በቅጡ አለመረዳታቸው ነው ።
«እኔም ሆንኩ ሌሎቹን ያሰባሰበን የቱርክ እጣ ፈንታ ነው ። የህገ መንግሥት ማሻሻያው ምክር ቤት ውስጥ ያለ አንዳች ተቃውሞ እንዲያልፍ ከባድ ትግል ነው የተደረገው ። እናም በሚያዚያ 16ቱ ህዝበ ውሳኔ የሚሳተፉት የቱርክ ዜጎች ህዝበ ውሳኔው ለምን እንደሚካሄድ አያውቁም ። ግን ማሻሻያውን ይደግፋሉ ። የህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች የሚያካሂዱ ተቋማትም ጀርመን ካሉ ቱርኮች አብዛኛዎቹ ህዝበ ውሳኔው እንደሚካሄድ ከማወቅ ባለፈ ስለ ምንነቱ ያላቸው መረጃ ውስን ነው። »
ካፓን እንደሚሉት አብዛኛዎቹ ህዝበ ውሳኔው ኤሮዶሀንን ደግፎ ወይም ተቃውሞ ድምጽ መስጠት ነው ብለው ነው የሚያስቡት ። እናም ካፓን እና ሌሎች ቱርኮች ፣የቱርክ ዜጎች ሊገኙ በሚችሉበት ስፍራ ሁሉ መረጃ ይሰጣሉ። በቱርኮች ቡና ቤቶች ሳይቀር ውይይቶችን ያካሂዳሉ ። በኮሎኙ ቅስቀሳ የተሳተፈው ሌላው በሀያዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው የኮሎኝ ነዋሪ ዶጋን የኤርዶጋን የህገ መንግስት ማሻሻያ ከሚቃወሙት አንዱ ነው ። ወጣቱ ዶጋን እንደሚለው ብዙ ጓደኞቹ የኤርዶሀን ደጋፊዎች ናቸው ። በነሱ አስተሳሰብ የህዝበ ውሳኔው ጉዳይ ለክርክር መቅረብ የለበትም ። በህዘበ ውሳኔው ላይ ትችት ሲሰነዘር የተጠቁ ያህል ነው የሚሰማቸው ።እናም ይላል ዶጋን ጀርመን የሚገኙ የአብሮ አደጎቹን ባህርይ ሊረዳ አልቻለም ። ካፓን እንደሚሉት ህዝበ ውሳኔው ዴሞክራሲ ወይስ አምባገነንነት የሚለውን ምርጫ ነው የሚያስቀምጠው ።የነርሱ ዘመቻም ይህን ማስረዳት ነው ። በርሳቸው አስተያየት ቱርክ ውስጥ ሆኖ መቃወም ከባድ ችግሮችን ያስከትላል ።
«ማሻሻያውን የሚቃወሙ የተለያዩ ወንጀሎች ይፈጸሙባቸዋል ። ተቃውሞአቸው ከአሸባሪነት ጋር እንዲያያዝ ነው የሚደረገገው ። ቱርክ ውስጥ ለህዝበ ውሳኔ በሚካሄደው ዘመቻም ተቃዋሚዎች ከደጋፊዎች ጋር የሚፎካከር አቅም የላቸውም ።የቱርክ መንግሥት ጠብ አጫሪ አቋም በቱርክ ብቻ ሳይሆን በጀርመንም እየታዘብን ነው ። ይህ ደግሞ በጀርመን ያለውን ማህበራዊ ነጻነትም እየጎዳ ነው ውዝግቡ አሁን በሁሉም አቅጣጫ ጽንፍ ይዟል ።»
በአሁኑ ጊዜ በብዙ የጀርመን ከተሞች ቱርኮች ማሻሻያውን ተቃውመው ድምጽ እንዲሰጡ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው ። የቱርክ ዝርያ ያላቸው ቱርጉት ዩክሴል በሄሰን ፌደራዊ ግዛት ፓርላማ የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ተወካይ ናቸው ።በቅርቡ ቪስባደን በተባለው ከተማ ቱርኮች ማሻሻያውን ተቃውመው ድምጽ እንዲሰጡ ዘመቻ የሚያካሂድ ቡድን መስርተዋል ። እርሳቸው እንደሚሉት ህዝበ ውሳኔ የሚሰጥበት የቱርክ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት ማሻሻያ ጀርመን የሚኖሩ ቱርኮችን በእጅጉ ከፋፍሏል ።
« ጀርመን የሚኖሩ ማሻሻያውን የሚደግፉ እና የሚቃወሙ ቱርኮች በፍፁም ርስ በርስ አይነጋገሩም ። ተቃዋሚዎቹን የአሸባሪዎች ደጋፊ ወይም የቱርክ መንግስት አሸባሪ የሚለው ፔካካ የተባለው ቡድን አባል ተብለው ስለሚፈረጁ ብዙ ሰዎች ሀሳባቸውን ከመግለፅ ይቆጠባሉ ። ሆኖም ድምጽ ለመስጠት የወሰኑም አሉ ። »
በአሁኑ ጊዜ በሄሰን በባንድቩርተምበርግ እና ሽሌሽዊሽሆልሽታይን እና በሌሎችም ፌደራዊ ግዛቶች በሚገኙ ከተሞች ቱርኮች የህገ መንግሥት ማሻሻያውን ተቃውመው ድምጽ እንዲሰጡ የሚካሄደው ዘመቻ ቀጥሏል ።
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ