1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የኤች አይቪ ስርጭትና የመድኃኒት አቅርቦት ችግር

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 2016

ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ቅሬታ በተመለከተ በክልሉ ጤና ቢሮ የቲቢ፣ የስጋ ደዌና የኤች አይቪ ኤድስ፣ ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ገብሬ ንጉሴ ስለኤች አይ ቪ ያለው ስራ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ በበሽታው የሚያዙትና መድኃኒት የሚያቋርጡ በሽተኞች ቁጥር ጨምሯል ነው ያሉት፡፡

Ukraine Covid-19 Impfung
ምስል Evgeniy Maloletka/AP Photo/picture alliance

በአማራ ክልል የኤች አይቪ ስርጭትና የመድኃኒት አቅርቦት ችግር

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በመድኃኒት ስርጭትና አቅርቦት ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ ባለሙያዎችና ነዋሪዎች ተናገሩ፣ የክልሉ ጤና ቢሮ እንዳለው በየጊዜው ባለው በመንገድ መዘጋጋትና በሌሎች ምክንያቶች የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ከሚወስዱ ወገኖች መካከል 8ሺህ ያክሉ አቋርጠዋል፡፡
በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት መካከል የጤናው ዘርፉ አንዱ ነው፡፡ ባለሙያዎችና ነዋሪዎች እንደሚሉት “የመድኃኒት እጥረት የፀጥታ ችግር ባለባቸው  የክልሉ አካባቢዎች ይስተዋላል፡፡”

የነዋሪዎች አስተያየት
በምዕራብ ጎጃም ዞን የፈስ ቤት ከተማ ነዋሪ እንደሚሉት ምንም እንኳ ጤና ተቋማት ክፍት ሆነው የምርመራ አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም መድኃኒት ማግኘት ግን ፈተና ሆኗል፣ እንደ አስተያየት ሰጪው ጤና ተቋማቱ የምርመራ አገልግሎት እየሰጡ ነው፣ ግን ተቋማቱ መድኃኒት ስለሌላቸው ህሙማን ከፍተኛ ገንዘብ በመክፈል መድኃኒት ከግለሰብ መደብሮች ለመግዛት ይገደዳሉ፡፡ “የመድኃኒት ችግር የሚነገር አይደለም፣ የለም በሚል ቢወሰድ ይሻላል” ብለዋል፡፡
በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሀ ከተማ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት በተለይ የኤች አይ ቪ ኤድስ  ስርጭት እየሰፋ መጥቷል፣  ለጉዳዩ እየተሰጠ ያለው ትኩረትም መቀነሱን ነው የሚገልፁት፡፡ “”የግንዛቤ ፈጠራ ተረስቷል” ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በአደጋ ውስጥ ናቸው ሲሉ ነው ያለውን ተጋላጭነት ያመለከቱት። አካባቢው የግብርና ልማት ስራ የሚሰራበትና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የቀን ሰራተኛ ያለበት በመሆኑ አሁን ከሚታየው ቸልተኝነት ጋር ተያይዞ ሰራተኛው ለኤች ኤ ቪ ኤድስ የመጋለጥ እድሉ የሰፋ እንደሆነም አመልክተዋል፣ የኮንደም ስርጭትም ቀደም ሲል እንደነበረው አይደለም፣  ዋጋውም ቢሆን ከፍተኛ ሆኗል ነው ያሉት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጋላጭነቱ ሰፊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የጎንጂ ቆለላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ተማሪዎች ወደ ትዳር እየገቡ እንደሆነ ገልፀዋል። ጋብቻ ሲፈፅሙም የኤች አይ ቪ የደም ምርመራ እንደማያደርጉ ተናግረዋል። ምክንትያሉት ደግሞ አብዛኛዎቹ ጤና ተቋማት ደግሞ ምርመራ ማድረግ ከሚችሉበት ደረጃ ላይ አይደሉም ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል በመድሃኒት አቅርቦት ችግር ብዙዎች እየተጉዱ እንደሆነ የጤና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።ምስል Jens Kalaene/dpa/picture alliance

የጤና  ባለሙያዎች አስተያየት
በምዕራብ ጎጃም ዞን የደንበጫ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የኤች አይ ቪ ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ወርቁ ሁነኛው በበኩላቸው፣ የመድኃኒት አቅርቦትና የመንገዶች በየጊዜው መዘጋጋት የበሽተውን ስርጭት ጭምሮታል ነው ያሉት። ወቅታዊ ሁኔታው የግንዛቤ ትምህርት እንዳይሰት እንቅፋት በመሆኑ አሁን ሰዎች  ከበሽታው ይልቅ እየፈሩ ያለው እርግዝናን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
“አንደኛ የግብዓት አቅርቦት ችግር አለ፣ ሁለተኛ የትራንስፖርት ችግር አለ፣ ስለዚህ ሰዎች በፈለጉበት ቦታ ሄደው መድኃኒት መውሰድ አይችልም። በዚህ ምክንት መድኃኒት የሚወስዱ በሽተኞች መድኃኒት ያቋርጣሉ፣ አሁን የበሽተኛው ቁጥር እየጨመረ ነው፣ በዚህ ሰኣት ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በአካባቢው ስላሉ ሴተኛ አዳሪነት ተስፋፍቷል። ጥናት ቢያስፈልገውም አሁን ኤች አይ ቪ ወረርሽኝ በሚባል ደረጃ ሳደርስ አይቀርም፤ ሰው እርግዝናን ይፈራል እንጂ ኤች አይ ቪ ኤድስ ይይዘኛል ብሎ ኮንዶም መጠቀም  የለም” ብለዋል፡፡
በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረወርቅ ከተማ ጤና ጣቢያ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጤና ባለሙያ፣ መድኃኒቶችን ለመግዛት የፀጥታው ሁኔታ አላስቻለም ሲሉ ተናግረዋል፣ ለመግዛት ቢሞከርም ተፈላጊውን መድኃኒት ማግኘት አይቻልም ሲሉ አስረድተዋል። የሰራተኛ ቁጥጥሩ የላላ በመሆኑ ባለሙያው በሰዓቱ ወደ ስራ ስላማይገባ ባለጉዳዮች ይጉላላሉ ብለዋል፣ የትራንስፖርት ዋጋም ያለ ከልካይ በመጨመሩ ችግሩ ብዙ ነው ያሉት፡፡

የጤና ኃላፊዎች ምላሽ
የመድኃኒት አቅርቦትን በተመለከተ በኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ ጫኔ የመድኃኒት ችግር ባይኖርም የመንገዶች ሁኔታ ወደተፈለጉ አካባቢዎች እንዳይገባ እያደረወገው ነው ብለዋል፡፡
በአለው ፀጥታ ችግር ምክንያት ቀደም ሲል መድኃኒት ከአዲስ አበባ የሚመጣው ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በአውሮፕላን እንደነበር ጠቅሰው አሁን በየብስ ማምጣት እንደጀመሩ አመልክተዋል። ሙሉ በሙሉ በቂ ነው የሚባል ባይሆንም መድኃኒት መኖሩን ተናግረዋል፣ ችግር የሆነው መንገዶች እንደልብ ስለማያንቀሳቅሱ ወደ ሁሉም ቦታዎች መድኃኒት ማድረስ እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል ስለኤች አይቪ የሚሰጡ ትምህርቶች የሉም ማለት እንደሚቻል ባለሙያዎች ይገልጻሉ።ምስል Abdelhak Senna/AFP/Getty Images


ከኤች አይ ቪ ጋር በተያያዘ የተነሳውን ቅሬታ በተመለከተ በክልሉ ጤና ቢሮ የቲቢ፣ የስጋ ደዌና የኤች አይቪ ኤድስ፣ ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ገብሬ ንጉሴ ስለኤች አይ ቪ ያለው ስራ እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ በበሽታው የሚያዙትና መድኃኒት የሚያቋርጡ በሽተኞች ቁጥር ጨምሯል ነው ያሉት፡፡  በአማራ ክልል ቀደም ሲል 145 ሺህ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች እንደነበሩ ገልፀዋል። በክልሉ መድኃኒት እየወሰዱና በደማቸው ኤች አይ ቪ አድስ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር 145 ሺህ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ዓመት ደግሞ 5ሺህ 600 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ተገኝቶባቸዋል ብለዋል፡፡ በተለያየ ምክንያት መድኃኒት በአካባቢያቸው የማይወስዱ ሰዎች ቀደም ሲል ይወስዱበት ከነበረ ጤና ተቋም ለመውስድ ወቅታዊ ሁኔታው አመቺ ስላልሆነ 8ሺህ 700 ሚሆኑት መድኃኒት መውሰድ ማቆማቸውን አስረድተዋል፣ ሌሎች እንደዚሁ መድኃኒት አቋርጠው የነበሩ 11ሺህ ሰዎችን ደግሞ በተደረገ ከፍተኛ ጥረት እንደገና ማስጀመር ተችሏል ብለዋል፡፡
የኮንደም ስርጭት ለምን ተቀዛቀዘ ለሚለው ጥያቄም፣ “ከውጪ ይገኝ የነበረ ሀብት መቀነስና በአገር ውስጥም ሀብት ማንቀሳቀስ አለመቻል ነው፡፡” ሲሉ ምላሽ ሰትተዋል፡፡
በአማራ ክልል ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከ270 ባይ የጤና ተቋማት ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውና በመንገዶች ተደጋጋሚ መዘጋጋት  የህክምና ቀጠሮ የነበራቸው 10ሺህ ያክል ህመምተኞች ወደ ጤና ተቋማት መድረስ እንዳልቻሉ የክልሉ ጤና ቢሮ ቀደም ሲል መግለፁ ይታወሳል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ 


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW