1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የኤኮኖሚ ማሻሻያው» የብር አቅም መዳከም ለብዙኀኑ ሕዝብ ምን ማለት ይሆን?

እሑድ፣ ነሐሴ 5 2016

ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ መነጋገሪያ ሆኖ የከረመውን የኤኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ካደረገች ሳምንት አለፈ። የውጭ ገንዘብ ግብይቱ በነጻ ገበያው እንዲወሰን መደረጉ የሀገሪቱን መገበያያ ገንዘብ አቅም አሁን ከታየው የባሰ እጅግ እንደሚያዳክመው ነው የኤኮኖሚ ባለሙያዎች የሚናገሩት።

የኢትዮጵያ ገንዘብ
አቅም ያጣው የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ፤ ብር ፎቶ ከማኅደር፤ ገበያ ምስል Eshete Bekele/DW

«የኤኮኖሚ ማሻሻያው» የብር አቅም መዳከም ለብዙኀኑ ሕዝብ ምን ማለት ይሆን?

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግሥት የኤኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉን በቅርቡ ይፋ አድርጓል። ይህን ተከትሎም የውጭ ገንዘብ ምንዛሪ በዓለም ገበያ እንዲወሰን ነጻ ማድረጉ የሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ ብር አቅም በጣም መዳከሙ እየተገነገረ ነው። የብር የመግዛት አቅም በተለይም የሸቀጦች ዋጋ መናርን ማስከተሉም እየታየ ነው። ይህን ለመቆጣጠርም መንግሥት የንግድ ቤቶችን እስከማሸግ ደርሷል። መንግሥት እርምጃውን የወሰድኩት የተከማቸውን የሀገሪቱን የዕዳ ጫና ለመቀነስ ነው ይላል። ከዚህም ሌላ የውጭ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለማምጣት እንዳለመም ነው የሚገለጸው። ቀደም ሲል የኤኮኖሚ ማሻሻያ እንዲደረግ ያሳስቡ የነበሩ የዘርፉ ባለሙያዎች እርግጥ መንግሥት ይህን ማድረጉ የሚጠበቅ እንደሆነ በማመልከት የምንዛሪውን ስልት ቀስ በቀስ መለወጥ ይሻል ነበር ባይ ናቸው። የውጭ መዋዕለ ንዋይን ፍሰትን ለመሳብም አስቀድሞ በሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ተገቢውን የቤት ሥራ መፈጸም እንደሚኖርበትም ይገልጻሉ። ለመሆኑ በኑሮ ውድነት ግራ ለተጋባው ብዙሃኑ ኢትዮጵያ በእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት ይፋ የተደረገው የኤኮኖሚ ማሻሻያ ምን ማለት ይሆን? ሲል ዶቼ ቬለ ሦስት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ባለሙያዎችን ማለትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅ የነበሩ እንዲሁም ለማዕከላዊ ባንክ በአማካሪነት ያገለገሉ፤ በዓለም ባንክ ለ30 ዓመታት በተለያዩ ደረጃዎች የሠሩትና አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት ታዋቂቱ የኤኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር አክሎግ ቢራራ፤ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሀዋሳ እና በዲላ ዩኒቨርሲቲዎች በኤኮኖሚክስ መምህርነትና ተመራማሪነት ያገለገሉ፣  በኢትዮጵያ የንግድ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የሠሩ፤ አሁንም በዩኒቨርሲቲ በማስተማርን በምርምር የቀጠሉት ዶክተር ደገላ ኤርገኖ፤ እንዲሁም፤ ዶክተር ያብባል ሙሉዓለም፤ በጀርመን ሀገር ቦን ከተማ የሚገኘው የጀርመን ልማትና ዘላቂነት  የሚባለው የምርምር ተቋም በኤኮኖሚ ከፍተኛ ተመራማሪ ሆነው በማገልገል ላይ ያሉ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በጀርመኑ ጎቲንገን ዩኒቨርሲቲዎችም በዘርፉ በማስተማር ያገለገሉ፤ ከሦስቱ የኤኮኖሚ ባለሙያዎች በተጨማሪ ደግሞ የመንግሥትን የኤኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃው እርምት ይደረግበት ወቅቱም አይደልm ሲል አጥብቆ የተቃወመው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ ኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖትን ጋብዞ ውይይት አካሂዷል።

በዚህ አጋጣሚ በውይይቱ በመሳተፍ የመንግሥትን አቋም እንዲያብራሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕረስ ሴክረታሪያት እንዲሁም ለመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣናት በኢሜይል ብንጠይቅም ምላሽ እንዳላገኘን መግለጽ እንወዳለን።

ሙሉ ውይይቱን የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW