1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የእህል ዋጋ ቀነሰ

ዓርብ፣ ኅዳር 2 2015

ስንዴ በኩንታል 11 ሺህ ብር ይሸጥ ነበር አሁን 3ሺህ 200 ብር ሆኗል፣ ምስር በኩንታል 20ሺህ 800 ብር ነበር አሁን 6ሺህ 800 ብር ሆኗል፣ አተር በኩንታል 24ሺህ 400 ብር ነበር አሁን 6ሺህ 400 ብር ሆኗል፣ ጤፍ በኩንታል 14 ሺህ ብር ነበር አሁን 6ሺህ ብር ገብቷል።

Äthiopien Southern Tigray, Alamata
ምስል፦ Alemenew Mekonnen Bahardar/DW

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ የእሕል ዋጋ ቀንሷል

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልልና ክልሉን በሚያዋስኑ ዉጊያ ይደረግባቸዉ አካባቢዎች የሰላም ተስፋ በመፈንጠቁ የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ቀንሷል።በጦርነቱ የተጎዱትን የቆቦ፣ የአላማጣና የኮረም ነዋሪዎች  እንደሚሉት በየከተሞቹ እጅግ አሻቅቦ የነበረዉ ይምግብና የማጣፈጪያ ሸቀጦች ዋጋ ሰሞኑን እየቀነሰ ነዉ። ቆቦ ላይ 30ሺህ ብር የነበረው የአንድ ኩንታል ምስር ዋጋ ዛሬ 10ሺህ ብር፤ አላማጣ ላይ 25ሺህ ብር የነበረው የአንድ ኩንታል ጤፍ ዋጋ ዛሬ 6ሺህ ብር ሲሸጥ፣ ከረም ላይ 20 ብር ሲሸጥ የነበረ አንድ ሳጥን ክብሪት ዛሬ 3 ብር እየተሸጠ ነው ተብሏል፡፡የባሕርዳሩ ወኪላችን ዓለምነዉ መኮንን የየአካባቢዉን ነዋሪዎች አስተያየት ሰብስቧል።በሰሜን ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት የተከፈተው ጦርንት በትግራይና አዋሳኝ የአማራና የአፋር አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉ ይታወቃል፣ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀልና ስደት ዋነኞቹ ሲሆኑ አካባያቸውን ያለቀቁት ደግሞ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠው ቆይተዋል፡፡ የምግብ እህል ሸምቶ ለመመገብ በአካባቢዎቹ ያሉ ባንኮች አገልግሎት ተቋርጦ በመቆየቱም ሌላ የህይወት ፈተና ገጥሟቸው ኖረዋል፣ ገንዘብ ያላቸውም ቢሆን ሸምቶ ለመብላት የምርቶቹ ዋጋ የማይቀመስ በመሆኑ ችግርን ሲገፉ ቆይተዋል፡፡

አላማጣ ከተማምስል፦ DW

ሰሞኑን በኢትዮጵያ መንግስትና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ውስጥ የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ጦርነት በነበረባቸው አካባቢዎች የገበያ መረጋጋት መኖሩን ነዋሪዎቹ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

አቶ ጀማል ስጦታው የተባሉ የኮረም ከተማ ነዋሪ የአካባቢያቸውን የእህል ዋጋ ተዘዋውረው ከአጠኑ በኋላ ከሳምንታት በፊት የነበረውንና አሁን ያለውን የእህል ዋጋ በማነፃፀር ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ  በዝርዝር አስረድተዋል፡፡በቆቦና አካባቢው ውጊያ መቀጠሉ

“ ስንዴ በኩንታል 11 ሺህ ብር ይሸጥ ነበር አሁን 3ሺህ 200 ብር ሆኗል፣ ምስር በኩንታል 20ሺህ 800 ብር ነበር  አሁን 6ሺህ 800 ብር ሆኗል፣ አተር በኩንታል 24ሺህ 400 ብር ነበር  አሁን 6ሺህ 400 ብር ሆኗል፣ ጤፍ በኩንታል 14 ሺህ ብር ነበር አሁን 6ሺህ ብር ገብቷል፤ ፊኖ ዱቄት በኩንታል 12 ሺህ ብር ነበር፣ አሁን 6ሺህ ብር ገብቷል፤ ስኳር በኩንታል 20ሺህ ብር ነበር  አሁን 11ሺህ ብር ገብቷል፣ ጨው በኪሎ 300 ብር ነበር አሁን 35 ብር ሆኗል፣ ክብሪት እስከ 20 ብር ይሸጥ ነበር አሁን 3 ብር ይሸጣል፣ ፈሳሽ ኦሞ እስከ 500ብር  ይሸጥ ነበር ዛሬ 250 ብር ይሸጣል፡፡”

የአላማጣ ከተማ ነዋሪው አቶ አበራ ቻሌም ጤፍን ጨምሮ የእህል ዋጋ ከስምምነቱ እየቀነሰ መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከቆቦ መውጣቱን መንግሥት ገለጸ

“በእኛ ጤፍ በጣሳ ይባላል፣ ከአንድ ኪሎ ትንሽ ቀንሳል፣ 250 ብር ነው የነበረው አሁን ከ60 እስከ 80 ብር በጣሳ ሆኗል፣ ማሽላና በቆሎ በቆርቆሮ እስከ 120 ፣ 130 ብር ነበሩ አሁን ከ30 እስከ 35 ብር በቆርቆሮ ወርዷል፣ ገበያው አሁን እየተረጋጋ ነው ትሩ ሁኔታ ነው ያለው፣ አሁን ከወልዲያና ከቆቦ የተሸለ ገበያ አላማጣ ላይ አለ፡፡”

አላማጣ ከተማምስል፦ DW

ጦርነቱ በእጅጉ ጉዳት ካደረሰባቸው አካባቢዎች በሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘው የቆቦ ከተማ አንዷ ስትሆን ነዋሪዎቿ ከጦርነቱ ባሻገር በእህል ዋጋ መወደድ በእጅጉ ተቸግረው ቆይተዋል፣ በተፈጠረው ስምምነት ምክንያት የእህል ዋጋ አልፎ አልፎ ከፍ ዝቅ የሚል የዋጋ ሁኔታ ቢኖርም፣ ትርጉም ባለው መልኩ የእህል ዋጋ እየወረደ እንደሆነ የከተማዋ ነዋሪ አቶ አማኑኤል አሰፋ ገልጠዋል፡፡

ሙስጦፋ ከድር የራያ ወረዳ አርሶ አደር ናቸው፣ ጎለሽ 042 በሚባል ቀበሌ ይኖራሉ፣ በአካባቢው ጦርነት ከቆመ በኋላ የእህል ዋጋ የወረደ ቢሆንም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች  ሲጀመሩ እንደገና የመውጣት ሁኔታ እንደሚታይ አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነቱ በነበረባቸው አካባቢዎች አስፈላጊውን የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ 4 የሰብአዊ እርዳታን የሚያቀላትፉ ቡድኖችን ማቋቋሙን ትናንት አስታውቋል፡፡

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW