በእሥራኤል ሀማስ ጦርነት የግብጽ አቋም
ቅዳሜ፣ ኅዳር 1 2016
ከተጀመረ አንድ ወር ያለፈው የእሥራኤል ሀማስ ጦርነት ግብጽን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷል። ከእስራኤል ሌላ ጋዛን የምታዋስነው ግብጽ ሰብዓዊ ርዳታ ወደ ጋዛ የሚሄድበትን መንገድ እያመቻቸች ነው ።ይሁንና ተፈናቃይ ፍልስጤማውያንን ማስገባትን ግን የማትቀበለው ቀይ መስመር ትለዋለች ። የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ እስራኤል የማትቆጣጠረው ብቸኛው ወደ ጋዛ የሚያስገባው የራፋ ድንበር ከጋዛ ለሚመጡ ፍልስጤማውያን መተላለፊያ ሊሆን አይችልም ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል። መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ቻተም ሀውስ የተባለው የጥናት ተቋም ተባባሪ መምህር እና በዴንማርክ ሮስኪልድ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ሚሼለ ፓስ እንዳሉት የግብጽ መንግሥት ድንበሩ ሲከፈት ፍልስጤማውያኑ በገፍ ወደ ግብጽ ይመጣሉ ብሎ ይሰጋል።
«የካይሮ አቋም እየጨመረ በመጣው በጋዛ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ የራፋ መሸጋገሪያን ለስደተኞች እንድትከፍት ምዕራባውያን በሚያደርጉባት ግፊት ላይ የተመረሰተ ነው። አልሲሲ በልዩነቶች መካከል በጥንቃቄ ጉዳዩን ለመያዝ በጣም ይጠነቀቃሉ። ግብጾች በእሥራኤል አጠቃላይ የጋዛ ከበባና የእሥራኤል ባለሥልጣናት ምክንያት ፍልስጤማውያን በገፍ ሊሰደዱ ይችላሉ የሚል ፍርሀት አላቸው።»አልሲሲ ከመስከረም 26 ቀን፣ 2016 ዓ. ምህረቱ የሀማስ ጥቃት በኋላ ተፈናቃይ ፍልስጤማውያን ግብጽ መግባት እንደማይፈቀድላቸው ደጋግመው አሳውቀዋል።
ይሁንና ዋሽንግተን የሚገኘው የታህሪር የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ ተቋም ምክትል ሃላፊ ቲመቲ ኢ ካልዳስ ግብጽ ሲቪሎችን የማስገባት ግዴታ አለባት ይላሉ። ጋዛ የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች ተገን የመጠየቅ መብት አላቸው ያሉት ካልዳስ መቼና እንዴት መብታቸው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ የሚወስኑት ደግሞ እነርሱው ናቸው ብለዋል። ሌላው ግብጽ ሰዎቹን ላለማስገባት የምትሰጠው ምክንያት የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊዎችን ከሰላማዊ ሰዎች መለየት አይቻልም የሚል ነው። «የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድኖች በሲናይ በረሀ የመረጃ የቁሳቁስ እና የወታደራዊ እንቅስቃሴ እገዛ ከሚያደርጉላቸው ደጋፊዎቻቸውና ተባባሪዎቻቸው ጋር ግንኙነቶችን ከመሰረቱ ግብጽ እነዚህ ቡድኖች ከግብጽ ግዛት ወደ እሥራኤል ይዞታዎች ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ ይችላሉ፤ ይህም እሥራኤልን ለአጸፋ ጥቃት በመጋበዝ ከግብጽ ጋር ያላትን ግንኙነት ያናጋል የሚል ፍርሀት አላት ግብጽ። »የተባባሰው የእስራኤል ሀማስ ጦርነትና የአውሮጳውያን አቋም
አል ሲሲ በቅርቡ ካይሮ ውስጥ በተካሄደ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት አሸባሪዎች ሲና በረሀ ገብተው እሥራኤልን ለማጥቃት የሚጠቀሙበት ከሆነ ኃላፊነቱ በግብጽ ላይ ነው የሚወድቀው ይላሉ። አልሲሲ፤ በጎርጎሮሳዊው 1979 ከእስራኤል ጋር የተፈረመው የሰላም ስምምነትም ከእጃችን ይወጣል ብለው ይሰጋሉ። የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት የሂዩመን ራይትስ ዋች የቀድሞ ኃላፊ ኬኔዝ ሮት አል ሲሲ እስራኤል በአሜሪካ፣ በአውሮጳ ኅብረት፣ በጀርመን እና በሌሎች «አሸባሪ ድርጅት» በሚል የተሰየመው ሐማስን ለመደምሰስ የምታደርገውን ሙከራ የሚደግፉት እርሳቸውም የግብጹን የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር ለማጥፋት በጎርጎሮሳዊው 2013 በራባ አደባባይ 817 ተቃዋሚዎች ላይ የደረሰውን እልቂት ጨምሮ እጅግ ዘግናኝ እርምጃ በመውሰዳቸው ምክንያት ነው ሲሉ ይገልጻሉ።
ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠረው የእሥራኤል ሀማስ ግጭት ፈላጭ ቆራጭ በሚባለው በግብጽ መንግሥትና በህዝቡ ግንኙነት ላይ ተጽእኖ አድርጓል የሚሉት ደግሞ በዩናይትድ ስቴትሱ ጆርጅ ዋሽንግተን ጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ናታን ብራውን ናቸው።ሆኖም በርሳቸው አስተያየት ልዩነቶቹ አሁን እንደ በፊቱ አይደሉም።«በአገዛዙና በህዝቡ መካከል የተፈጠረው ልዩነት ሀገሪቱ ባጋጠማት የኤኮኖሚ ችግሮች ምክንያት ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ በሰፈነው ፈላጭ ቆራጭነት በሁሉም መንገዶች ሰፊ ነው።እነዚህ ልዩነቶች ግን አሁን በመጠኑ ቀንሰዋል። ትኩረቱ የግብጽን ድንበሮች ከመጠበቅ ይልቅ በእሥራኤል ሀማስ ጦርነት ግብጽ ዋጋ እንዳትከፍል ማረጋገጥ ሆኗል።
የተባባሰው የእስራኤል ሀማስ ጦርነትና የአውሮጳውያን አቋምበጋዛ የቀጠለው ግጭት እንዲቆም የጠየቀው የብራስልስ ሰልፍይህ ደግሞ መንግሥትን ከአገዛዙ የሚለይ አልሆነም።»ይህ በቅርቡ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዳግም ይመረጣሉ በሚባሉት በአልሲሲ ተቀባይነት አግኝቷል። ግብጽ ለጋዛ በምትሰጠው ድጋፍ የምታገኘው ዓለም አቀፍ የገንዘብ እርዳታ ሀገሪቱ በኤኮኖሚው ቀውስ ምክንያት የገጠማትን ችግር ለመቀነስ እገዛ ያደርጋል። የግብጽ ገንዘብ የመግዛት አቅም ከጎርጎሮሳዊው መጋቢት 2022 ዓም ወዲህ በግማሽ ወርዷል። የግብጽ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እየተሟጠጠ ነው። የጋዛው ግጭት የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነው የቱሪዝም እንቅስቃሴም ላይ ተጽእኖ አድርጓል። ይሁንናፕሮፌሰር ናታን ብራውን ግጭቱ የግብጽ ህዝብና መንግሥት ለረዥም ጊዜ አንድ ሆነው እንዲቆዩ ማድረግ መቻሉን ይጠራጠራሉ።
«እሥራኤል ከተፈጸመባት የመስከረም 28ቱ ዘግናኝ ጥቃት በኋላ በፍልስጤም ሲቪሎች ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ድብደባ ስትፈጽም በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ መጀመሪያ ላይ ለእሥራኤል የነበረው ሀዘኔታ ወደ ንዴት ሲቀየር የግብጽ መንግሥት ለምን አሁንም የእስራኤል አጋር ሆኖ ቀጠለ የሚለው ጥያቄ እየተነሳ ነው።»
የግብጽ መንግሥት ማናቸውም ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ ነው። መንግሥት ያገደውን ፍልስጤማውያንን የሚደግፍ ሰልፍ ባለፈው ሳምንት ካካሄዱ የግብጽ ተቃዋሚዎች የግብጽ የፀጥታ ኅይሎች ካይሮ እና አሌክሳንድሪያ ውስጥ 70 ሰዎችን አስረዋል። ሂዩመን ራይትስ ዋች በቅርቡ ባወጣው ዘገባ እንዳለው ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር በመተባበርና የሽብር ጥቃት በመፈጸም ተጠርጥረው የተከሰሱ 16 ተቃዋሚዎች ታስረዋል።
ጄነፊር ሆላይስ
ኂሩት መለሰ