የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት እርዳታ መቋረጥ በአማራ ክልል የሚፈጥረው ጫና
ሐሙስ፣ ጥር 29 2017
አሜሪካ በተራድኦ ድርጅቷ (USAID) በኩል ትሰጥ የነበረውን እርዳታ ማቋረጧ በበርካቶች ዘንድ የመወያያ ርዕስ ሆኗል። እርዳታው መቋረጡ በተለይ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ በጦርነት ለተፈናቅሉ፣ በድርቅ ለተጎዱና እርዳታውን የሚሹ ወገኖችን ከባድ የኑሮ ፈተና ውስጥ እንደሚከታቸው የሚናገሩ በርካቶች ናቸው።
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከል ተጠሪ ጽ/ቤት ባለሙያ እንድሪስ መሐመድ የዩኤስ ኤድ መቋረጥ ሊያስከትል የሚችለውን ሰብአዊ ቀውስ ይናገራሉ።
ድጋፉን ሲጠብቁ ለነበሩ ወገኖች ጉዳት ያስከትላል
«... የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶ ች(UN Agencies)” WFP, OCHA, FAO, UNHCR, CRS የመሳሰሉ ድርጅቶች ድጋፋቸው ሲቀር ድጋፉን የሚጠብቁ ወገኖች ይጎዳሉ፣ በተለይ ተፈናቃዮች፣ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች፣ ህክምናው ይስተጓጎላል፣ ሕጻናት ይጎዳሉ፣ ነፍሰጡሮች ይጎዳሉ ሌሎችም እንዲሁ ይጎዳሉ»።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሰርክአዲስ አታሌ የእርዳታው መቋረጥ በርካታ ተረጂ ላለበት የአማራ ክልል ከፍተኛ ቀውስ ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ እርዳታ ፈላጊዎች፣ በበርካታ የአማራ ክልል ድርቅ ተከስቶ የነበረበት ዓመት እንደነበርና አሁን ያለው የአማራ ክልል ተጨባጭ ሁኔታ ታክሎበት የእርዳታ መቋረጥ ከፍተኛ ችግር እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።
የእርዳታው መቋረጥ ለአማራ ክልል «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» ነው
በተለይ በድርቅ ለተጎዱ የሰሜን ወሎ ዞን ቡግና ወረዳ እርዳታ ፈላጊዎች ድርጅቱ ከፍተኛ እገዛ ሲያደርግ እንደነበር የሚናገሩት ወ/ሮ ሰርክአዲስ አሁን የተፈጠረው የዩኤስ ኤድ ድጋፍ መቋረጥ «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» ነው ብለውታል።
የዩኤስ ኤድ ድጋፍ መቋረጥ ሰብአዊ ሁኔታውን ብቻ ሳይሆን የሚጎዳው፣ በድርጅቱ የገንዘብ ድጋፍ እየታገዙ የሚሠሩ ልማቶችንም እንደሚያደናቅፍ አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ።
የእርዳታው መቋረጥ የመስኖ ፕሮጀክቶች፣ በተለያዩ መንገዶች አርሶአደሩን በገንዘብ ለመደገፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዛቸው እንደማይቀር ነው አስተያየት ሰጪዎች የሚገልፁት።
«የእርዳታ መቋረጡ ትክክል ነው፣ ከልመና መውጣት አልብን» አስተያየት ሰጪ
አቶ አዳነ እውነቱ የተባሉ የወገል ጤና ከተማ ነዋር ግን የተለየ አስተያየት አላቸው።እርሳቸው እንደሚሉት እርዳታ መቋረጡ ምናልባት በድርጅቱ ስር ያሉ ሠራተኞችን ይጎዳ ካልሆነ በስተቀር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚያመጣው ተፅዕኖ አይኖረውም። መቋረጡም ትክክል ነው።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ሰርክአዲስ አታሌ ግን ችግሩን ለመቋቋም ጠንካራ የዲፐሎማሲ ሥራዎችን መሥራት፣ ምርታማነትን ማሳደግና የአመራር ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል 2 ሚሊዮን 500 ሺህ የዕለት ምግብ እርዳታ ፈላጊ ሲኖር ከዚህ ውስጥ 664,840ዎቹ ተፈናቃዮች እንደሆኑ ከአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ