መርካቶ የተከሰተው ሌላኛው የእሳት አደጋ
ሰኞ፣ ኅዳር 9 2017ዛሬ እሁድ እኩለ ቀን 6:30 ግድም የተነሳውን እሳት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ያስታወቀው የከተማ አስተዳደሩ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ቃጠሎው ሳይዛመትና የከፋ ጉዳት ሳያደርስ አንድ ሰዓት ተኩል በፈጀ ርብርብ መቆጣጠሩን አመልክቷል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ መርካቶ ጃቡላኒ ህንፃ በተለምዶ "ድንች በረንዳ" ተብሎ በሚጠራ አከባቢ በተነሳው የእሳት አደጋ ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በቅርቡ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የዛሬ አንድ ወር ግድም ሸማ ተራ ተብሎ ከሚታወቅ ነባር ህንጻ አከባቢ በተነሳው ከባድ የእሳት አደጋ ከፍተኛ የንብረት ውድመት መከሰቱ ይታወሳል፡፡ ዛሬ የእሳት አደጋው ያጋጠመበት "ድንች በረንዳ" አከባቢም ከዚህ ብዙም የማይርቅ ስፍራ ነው፡፡
አንድ ሰኣት ተኩል በፈጀ ጊዜ እሳቱን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ለዶቼ ቬለ የገለጹት የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ፤ ምንም እንኳ መንስኤው እስካሁን ባይጣራም እሳቱም የተነሳው ተቀጣጥለው ከተሰሩ ሱቆች ነው ብለዋል፡፡ “እሳቱ የተነሳው ቆርቆሮ በቆርቆሮ ሆነው ተቀጣጥለው ከተሰሩ የንግድ ሱቆች ነው” ያሉት አቶ ንጋቱ፤ እሳቱ የተነሳበት ስፍራ በብዛት ስኒከር ጫማዎች የሚሸጡበት ነው፡፡ ኃላፊው አክለውም እሳቱ እንደተነሳ አብዛኘውን እቃ በማውጣት ከቃጠሎ ማትረፍ መቻሉንም አስረድተዋል፡፡
የዛሬው አደጋ አጋላጭነቱ ከዚህ በፊት በአከባቢው ከተነሳው ከባድ የእሳት አደጋ ሊከፋ የሚችልበት እድል እንደነበርም አስረድተው፤ ነገር ግን ዛሬ እሁድ እንደመሆኑ አከባቢው ክፍት በመሆኑ እና በተደረገው ርብርብ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡ የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ወደ 18 የእሳት አደጋ ተሸከርካሪ ቦቴዎች ከ122 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር መሰማራታቸውንም አክለው ገልጸዋል፡፡
ለመቆጣጠር 1፡30 ፈጅቷል በተባለው በዚህ የእሳት አደጋ ከፍተኛ ርብርብ በመደረጉ አደጋው እንዳይስፋፋ ከማድረግም አልፎ በፍጥነት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር መቻሉም ተነግሯል፡፡ በእሳት አደጋው ስድስት ሰዎች ላይ ቀላል አደጋ ደርሶባቸው ህክምና ማግኘታቸውም ነው የተገለጸው፡፡ “ስድስት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል፡፡ ሁለቱ በዚያው በአምቡላንስ ውስጥ ስታከሙ አራቱ ድግሞ የቆርቆሮ መቁረጥ ነገር ነው” ብለዋልም፡፡
የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ንጋቱ ማሞ የመርካቶ ቤቶች አሰራር ለአደጋ እጅጉን ተጋላጭ የሚያደርጉ እንደመሆናቸው ዘመናዊነትና የእሳት አደጋ ደህንነት መስፈርትን አሟልተው መሰራት እንደሚኖርባቸው ምክር ለግሰዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ልደት አበበ