1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

የእስራኤል፣ አረብ አፍሪቃ ወዳጅነት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 5 2013

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን፤ ባሕሬንና እስራኤል «የሰላም» የተባለዉን ዉል ያፈራረሙት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደት ዶናልድ ትራምፕ ግን ስምምነቱ «ደም መፋሰሱን ያቆማል» ይላሉ።የማንን ደም? አናዉቅም።የምናዉቀዉ የትልቂቱ ሐገር ትልቅ መሪ ያሉትን ማለታቸዉን ነዉ።

Bildcombo I Benjamin Netanyahu ,Donald Trump, König Mohammed VI

የእስራኤልና የአረብ ሰላም

This browser does not support the audio element.


ታሕሳስ 1969 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ራባት-ሞሮኮ የተሰየመዉ የዓረብ ሊግ ጉባኤ እስራኤል በኃይል የያዘችዉን የአረብ ግዛት ለማስለቀቅ አረቦች በጋራ መታገል እንዳለባቸዉ ወሰነ።ሕዳር 1984 የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የሰሐራዊ አረብ ሪፐብሊክን አብዛኛ ግዛት ከሞሮኮ አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት የሚታገለዉን ፖሊሳሪዮን አባሉ ማድረጉን በመቃወም ሞሮኮ አዲስ አበባ ላይ ከተሰየመዉ ጉባኤም፣ከድርጅቱ አባልነትም ወጣች።ጊዜዉ ይሮጣል።የራባቱ ጉባኤ 51ኛ፣ የአዲስ አበባዉ 36ኛ ዐመታቸዉን ደፈኑ።ዛሬም ግን እስራኤል የአረቦችን፣ ሞሮኮ የሰሐራዊ ግዛቶችን እንደተቆጣጠሩ ነዉ።ፖለቲካዉም እንደ ጊዜዉ ተለዉጧል።ሞሮኮ ዳግም የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሆናለች።ባለፈዉ ሳምንት ደግሞ ከእስራኤል ጋር ተወዳጀች። አሜሪካም የፍልስጤሞችን ግዛት በተለይም አሮጌዉ እየሩሳሌንም ለእስራኤል፣የሰሐራዊዎቹን ለሞሮኮ መረቀች።የመለወጥ-አለመለወጡ ተቃርኖ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ ።
                                   

ያኔ ለአረብ ክብር፣ ለግዛት አንድነቱ ልዕልና እንዋጋለን ከሚሉት ትላልቅ የአረብ ሐገራት መካከል ኢራቅ ፈርሳለች።ሶሪያ ወድማለች።የመን ደቃለች።ሊቢያ ተከፋፍላለች።ሱዳን ደም ካፋሰሰ ለዉጧ በቅጡ አላገገመችም።ዛሬ ከኢራቅ እስከ የመን፣ ከሶማሊያ እስከ ሶሪያ፣ ከሱዳን  እስከ ሊቢያ፣ ከኢራን እስከ እስራኤል-ፍልስጤም ያለዉን የመካከለኛዉ ምሥራቅና የአፍሪቃን ፖለቲካዊ፣ መልከዓ ምድራዊ፣ ባሕል ኃይማኖታዊ ዕዉነታን ለመታረማስ ቢሊዮነ-ቢሊዮናት ዶላር የሚረጩት እኒያ ሐብታም፣ ትናንሽ የአረብ ደሴቶች ያኔ እንደ ሐገር ቀርቶ እንደ ወጥ ግዛት እንኳ አይታወቁም ነበር።
እኒያ ለዲፕሎማሲ-ፖለቲካዉ ጡቃንጡቅ ደንታ የሌላቸዉ፣ ቅብጥብቅ፣ ወጣት ኮሎኔል ያን በመሠለ ትልቅ ጉባኤ ላይ ሲገኙ የመጀመሪያቸዉ ነበር።ራባት።ታሕሳስ 1969።የጉባኤዉ አስተናጋጅ የሞሮኮዉ ንጉስ ሐሰን ዳግማዊ ጉባኤዉን እንዲከፍቱ የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ካንገታቸዉ ሰበር፣ ከወገባቸዉ ጎንበስ፣ ዝቅ  ብለዉ የንጉን ዕጅ ስመዉ ጋበዙ።
«የፈጣሪ ያለሕ» ጮኹ፣ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ፣ «ያየሁትን አይታችኋል።» ቀጠሉ ዓይናቸዉን ናስር ላይ እንደተከሉ።«በዚሕ ፊዉዳልና በባርነት ቀንበር ተዉጠን----ከዚሕ ሳንወጣ፣ ፍልስጤምን እንዴት ነፃ ልናወጣ እንችላለን?» ጠየቁ።አዳራሹ በቃዛፊ ጩኸት፣ በነገስታቱ ቁጣ፣ በሌሎቹ ሁካታ ሲተረማመስ፣ ናስር ቃዛፊን ያፅናኑ ገቡ- ጋዜጠኛ መሐመድ ሐይከል እንደፃፈዉ።
በ51 ዓመቱ የዘመን ሒደት ብዙዎቹ የዚያ ጉባኤ ተሳታፊዎች የሚሰሩትን ሠርተዉ አልፈዋል።ብዙዎቹ በክብር ተቀብረዋል።ቃዛፊ ግን እንደአዉሬ ታድነዉ፣ ቴሌቪዥን ካሜሪ ፊት ጭንቅላታቸዉ በጥይት ተፈርክሶ በረሐ ላይ ተጥለዋል።የራባት ላይ ጩኸታቸዉ ግን ትንቢት መስሎ እነሆ ዛሬም ይጠቀሳል።ፍልስጤምም ነፃ አልወጣችም።
የአረብ ግዛትን ለማስመለስ «ከባድ ሚዛን» የነበሩት የኢራቅ፣ የሶሪያ፣ የየመን፣ የሊቢያ፣ የሱዳን መንግስታት ፈርሰዋል፣ተበታትነዋል ወይም ደክመዋል።ያኔ የረቦች መሪና አስተባባሪ ትባል የነበረችዉ የናስሯ ግብፅ ሁሉንም እርግፍ አድርጋ ትታ በ1979 ከእስራኤል ጋር ተስማምታለች።በመስማማቷ ከዩናይትድ ስቴትስ በየዓመቱ ለሚቆረጥላት 2 ቢሊዮን ዶላር የናስር ምትክ መሪዋን የሳዳትን ሕይወት ሳይቀር ቤዛ መክፈል ግን ግድ ነበረባት።
የሐሺማይቶቹ ተገዢ፣ የአል-አቅሳ የበላይ ጠባቂ ዮርዳኖስን በ1994 የግብፅን ፈለግ ተከትላ፣ እንደ ግብፅ ተጠቅማ ከእስራኤል ጋር ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነት መስርታለች።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችና ባሕሬን ከእስራኤል ጋር ወዳጅነት ለመመስረት፣ «የሰላም ዉል» ፈረሙ የሚለዉ ዜና ባለፈዉ መስከረም ከወደ ዋሽግተን ሲሰማ፣ ለብዙዉ የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ተንታኝ ግራ አጋቢ፣አስቂኝ፣ ማፌዣም ብጤ ነዉ የሆነዉ።አረቦች ከእስራኤል ጋር ሲዋጉ እነዚሕ ትናንንሽ ሐገራት እንደ መንግስት ሊቆሙ ቀርቶ እንደ ግዛት ቅኝ ለማደር እንኳ የለንደን ቅኝ ገዢዎችን ደጅ ይጠኑ ነበር። 
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶችን፤ ባሕሬንና እስራኤል «የሰላም» የተባለዉን ዉል ያፈራረሙት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደት ዶናልድ ትራምፕ ግን ስምምነቱ «ደም መፋሰሱን ያቆማል» ይላሉ።የማንን ደም? አናዉቅም።የምናዉቀዉ የትልቂቱ ሐገር ትልቅ መሪ ያሉትን ማለታቸዉን ነዉ።
                                    
«ይሕ በመካከለኛዉ ምሥራቅ የአሸዋ ላይ ደም ሳይፈስ የተደረገ ሰላም ነዉ።እስካሁን ድረስ ለብዙ አስርተ-ዓመታት በየአሸዋዉ ላይ ደም ይፈሳል።የሚያደርጉት ነገር መገዳደል ብቻ ነዉ።ማንም ምንም አያገኝም።»
ለ1969ኙ የራባት ጉባኤና ለጠንካራ ዉሳኔ መሠረቱ በ1967 ካርቱም-ሱዳን ላይ የተደረገዉ የአረብ ሊግ ጉባኤና ዝነኛ ዉሳኔዎቹ ነበሩ።የካርቱሙ ጉባኤ «ሶስቱ አይሆንሞች» የተባለዉ ዉሳኔ የፀደቀበት ነበር።ከእስራኤል ጋር ሰለም ማዉረድ፣ ለእስራኤል እዉቅና መስጠት፣ ከእስራኤል ጋር መደራደርን የከለከለከለ ዉሳኔ።
በጦርነቱም፣ በጉባኤ ዉሳኔዉም ያልተካፈሉና ያልነበሩት፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችና ባሕሬን ከእስራኤል ጋር ለወዳጅነት መስማማታቸዉ በተነገረ በወራት ዉስጥ ሱዳን ከእስራኤል ጋር ሠላም ለማዉረድ ተስማምታለች።ስምምነቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ይጨምር-አይጨምር በዉል አይታወቅም።
የ1967ቱ የአረብ ጉባኤና ዉሳኔ አስተናጋኝ ሱዳን ከእስራኤል ጋር በተስማማች በወሩ የ1969ኙ ጉባኤና ዉሳኔ አዘጋጅ ተከተለች።ሞሮኮ።አርብ።የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቢንያሚን ኔታንያሁ «ታሪካዊ» ያሉት  ቀን እንደሚመጣ ያምኑ ነበር።
                             
«ይሕ ታሪካዊ ቀን እንደሚመጣ አምን ነበር።ለዚሕ ቀን መምጣት ሁሌም እጥር ነበር።መጀመሪያ ለእስራኤል ሕዝብና ለመካከለኛዉ ምስራቅ ሕዝብ ሠላም ለማስፈን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉትን ፕሬዝደንት ትራምፕን ማመስገን እወዳለሁ።የሞሮኮዉን ንጉስም፣ ንጉስ መሐመድ 6ኛም ይሕ ታሪካዊዉ ሠላም በሁለቱ ሐገሮቻችን መሓል እንዲወርድ በመወሰናቸዉ ማመስገን እወዳለሁ።»
ፍልስጤሞች እንደገና ጀርባችንን በጩቤ ተወጋን ይላሉ።የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን፣ ባሕሬንና ሱዳን ያደረጉትን ስምምነት እንደተቃወሙ ሁሉ የሞሮኮንም ዉሳኔ ባደባባይ ሰልፍ ተቃዉመዉታል።ኔታንያሁ ብልሕ፣አዋቂ፣ «ለሠላም የጣሩ» እያሉ ያደነቋቸዉ የሞሮኮዉ ንጉስ መሐመድ 6ኛ የአል አቅሳ ጠባቂና የእየሩሳሌም «አስመላሽ» የተባለዉ የአረቦች ኮሚቴ የወቅቱ ሊቀመንበር  ናቸዉ።የፍልስጤሙ የቀድሞ የምክር ቤት እንደራሴ መሐመድ አል ጉኡል የሞሮኮን ዉሳኔ «ወንጀል» ይሉታል፣ የሚጣረስም።«ሞሮኮ በፍልስጤም ሕዝብ ላይ እንደፈፀመችዉ ወንጀል ነዉ የምንቆጥረዉ።ሞሮኮ ከያዘችዉ የአል-አቅሳ መስጊድ ተከላካይ ኃላፊነት፣ የአል ቁድስ (የእየሩሳሌም) አስመላሽ ኮሚቴ ሊቀመንበርነት  ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጋጭ ነዉ።»
ሞሮኮ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ አረብ-የሁዲ ዜጎች አሏት።የሞሮኮ-የሁዲዎቹ ስምነቱን ከልብ ደግፈዉታል።የራባቱ ነዋሪ ድሪስ ኢልቶሚ ግን አዲስ ነገር የለም ባይ ናቸዉ።«በይፋ ይሁን አይሁን፣ ከእስራኤል ጋር ሁሌም ግንኙነት ነበር።በተለያዩ መስኮች በተለይም በንግዱ ድሮም ግንኙነት ነበር።እና አዲሱ ነገር ምድን ነዉ?»
ስምምነቱን የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት በሁለቱ ታላላቅ ወዳጆቻችን መካከል የተደረገ በማለት አወድሰዉታል።የሞሮኮዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ናስር ቡሪታም እንደ ኔታንያሁ ሁሉ ንጉሳቸዉ ማድነቅ፣ ማወደስ ትራምፕን ማመስገናቸዉ አልቀረም።የአድናቆት፣ ዉዳሴ ምስጋናቸዉ ቀዳሚ ያደረጉት ምክንያት ግን የሞሮኮን ሕዝብ ከሚያስቆጣዉ ከእስራኤል ሞሮኮ ወዳጅነት ይልቅ፣ የሚያስደስተዉን በመጥቀስ ነዉ።
«ግርማዊነታቸዉ በመልዕክተኞች፣ በቀጥታ ግንኙነትና በቀጥታ ተሳትፎ ላለፉት 3 ዓመታት ላደረጉት ጥረት ምስጋና ይግባዉና ጥረታቸዉ ዛሬ ለፍሬ በቅቷል።ዩናይትድ ስቴትስ፣ ታላቂቱ ኃያል ሐገር፣ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አባል፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍተኛ ተፅዕኖ የምታሳርፈዉ ሐገር ሰሕራ ግዛት የሞሮኮ ግማደ ግዛት አካል መሆኑን ዕዉቅና ሰጥታለች።ሞሮኮ የደቡባዊ ግዛትዋን ጨምሮ ሉዓላዊት ሐገር መሆንዋ (አሜሪካ) ተቀብላለች።»
ጥንት የስጳኝ ሳሕራ፣ ኋላ የሠሐራዊ አረብ የሚባለዉ በረሐማ ግን ስልታዊ ግዛት እስከ1975 ድረስ የስጳኝ ቅኝ ግዛት ነበር።ስጳኝ ግዛቱን ስትለቅ ከግዛቱ 80 በመቶዉን ሞሮኮ ስትቆጣጠር የቀረዉን 20 በመቶ መንበሩን አልጀሪያ ያደረገዉ የነፃነት ተፋላሚ ድርጅት ፖሊሳርዮ ተቆጣጠረ።የሞሮኮና የፖሊሳሪዮ ዉጊያ ዉዝግብ ቀጠለ።
ዉዝግቡ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ለአፍሪቃ ሕብረት፣ ለአልጀሪያም ተርፏል።ተደጋጋሚ ድርድሮች፣ ዉይይቶች፣ ሽምግልናዉም ሠላም ማምጣት አልቻሉም።የሕዝበ ዉሳኔ ሐሳቦች እየተነሱ ወቅቀዋል፣ ሠላም አስከባሪ ሠራዊት ሠፍሯል።ሠላም ግን የለም።
የአልጄሪያና የሞሮኮ ጥንታዊ የነፃነት አርበኞች ሐገሮቻቸዉን ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት በጋራ ተፋልመዋል።ከ1975 ጀምሮ ግን ሁለቱ ተጎራባች፣ አፍሪቃዊ፣ አረብ ሐገራት  በሰሐራዊ ግዛት ሰበብ ጠላቶች ናቸዉ።የሁለቱ ሐገራት ድንበሮች ዛሬም ዝግ ናቸዉ።የራባት ገዢዎች ድንበር፣ ዘር፣ቋንቋ፣ ታሪክ ምጣኔ ሐብት ከሚጋሯቸዉ አልጀሪያዎች ጋር እየተቆራቆሱ ከእስራኤል አሜሪካኖች ጋር አወረድን ያሉት ሰላም ለሐገር ሕዝባቸዉ ይበጅ ይሆን? 
 «የሐገራችንን አንዱን የፖለቲካ ችግር ጥሎ፣ መርሐችንንና ሞራላችንን አፍርሶ ለሌላዉ ችግር መፍትሔ መፈለግ ተቀባይነት የለዉም። አልቀበለዉም።»ይላሉ ፋይዚ ግሊሊ።የራባት ነዋሪ ናቸዉ።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የአብዛኛ ሕዝባቸዉን ድጋፍ አጥተዉ በምርጫ ተሸንፈዉ ሥልጣናቸዉን ለማስረከብ የ4 ዓመት ዶሴያቸዉን እየሸከፉ ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ በሙስና ተከሰዉ፣ የፍርድ ቤቱ ዉጣ ዉረድ አልበቃ ያላቸዉ ይመስል ሕዝባቸዉ በአደባባይ ሰልፍ-በቁን በቃንዎት ማለት ከጀመረ 25ኛ ሳምንቱ።ሁለቱ መሪዎች ግን ከአቡዳቢ፣ ከማናማ፣ ካርቱም ራባት ገዢዎች ጋር ሆነዉ  ለአረብ እስራኤል ሰላም እየባተልን ነዉ ባይ ናቸዉ።ሠላም ቦርማ ይሆን ፈንዝማ?

ምስል Louiza Ammi/abaca/picture alliance
ምስል picture-alliance/AA/J. Morchidi

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW