የእስራኤል-ዩናይትድ ስቴትስና የኢራን ተኩስ አቁም ያሳደረዉ ተስፋ በኢትዮጵያ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 2 2018
እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስና ኢራን ባለፈዉ ማክሰኞ ለዕሮብአጥቢያተኩስ ለማቆም መስማማታቸዉ በመላዉ ዓለም እንደሆነዉ ሁሉ ለኢትዮጵያም እፎይታ ብጤ ነዉ።ሶስቱ ሐገራት ተኩስ ለማቆም መስማማታቸዉ እንደተሰማ የዓለም የነዳጅ ዘይት ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ አድርጓል።ይሁንና ከስምምነቱ በኋላ እስራኤል ሊባኖስን መድደቧን መቀጠሏና የሶስቱ ሐገራት ባለሥልጣናት መዛዛታቸዉ ብልጭ ያለዉን ተስፋ ያዳፍነዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል።“የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከውጭ በሚመጣው ጣጣ እንደሚጎዳ ግልጽ ነው፡፡ ሌሎች አገራትም ጨናው ደርስባቸዋል፡፡ ልነቱ እኩል እንቋቋማለን ወይ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የምጣነሃብት ባለሙያ ዶ/ር አብዱልመናን መሀመድ ናቸው፡፡
በዓለም ላይ እጅግ ጠቃሚ የኃይል መስመር መተላለፊያዎች አንዱ የሆነው የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በዓለም ወደ 20 በመቶ ግድም ነዳጅ ይተላለፍበታል። ኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎቷን የምትሸምትባት ኩዌትን ጨምሮ በርካታ የገልፍ አገራት በገፍ በማምረት በገፍ ለበርካታ የዓለም አገራት የሚልኩትን ነዳጅ ከዚህ ከሆርሙዝ ወሽመት ውጪ ምንም አማራጭ የላቸውም።
የጦርነቱ አለመቋጨት ለኢትዮጵያን ጎጂነቱ ከነዳጅ ስጋትም ባሻገር ነው
በዚህ ሰርጥ መዘጋት ክፉኛ ከተፈተኑ አገራት መካከልአንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ባለፉት ጢቂት ሳምንታት በአገር ውስጥ በተፈጠረ የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ኢኮኖሚው ላይ አስከፊ ሁኔታ ተደቅኖ ቆይቷል፡፡ ከቀናት በፊት በአሜሪካ እና ኢራን መካከል የተደረገው ጊዜያዊ የሁለት ሳምንታት የተኩስ አቁም ስምምነት ሆርሙዝን ክፍት የሚያደርግ በመሆኑ ወቅታዊ እፎይታ ብሰጥም እስራኤል ወዲያውኑ በሊባኖስ ላይ እጅግ ከፍተኛ ጥቃት በመውሰድ ውድመት ማድረሷ ግን ስጋቶቹን መልሶ ደቅኗል፡፡
እንደ የምጣነሃብት ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን አስተያየት፤ የሆርሙዝ ባህር ወሽመጥ መዘጋት ኢትዮጵያ ላይ ያመጠው ጣጣ በጉልህ ከታየው የነዳጅ አቅርቦት ችግርም የሚሻገር ነው፡፡ “ተጽእኖው የሚታየው ቀጥታ በነዳጅ ዋጋ እና አቅርቦቱ ላይ ነው” በማለትም ይህ የነዳጅ አቅርቦት ችግሩ በአገር ውስጥ የዋጋ ንረት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ ከፍ ሲልም የዚህ መስመር መዘጋት በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ሌላ ችግር በመደቀን ምርታማነቱ ላይ ቀጥተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳርፍ አመልክተዋል፡፡ እንደ ባለሙያው ምልከታ ጦርነቱ ካልተገታ ተጽእኖው በዚህም አያበቃም፤ በመካከለኛው ምስራቅ እና በገልፍ አገራት በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን አንድም በስራ አጥነት፤ ሁለትም በሚልኩት የውጭ ምንዛሪ መቀነስ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቀጥታ በጉዳዩ እንደሚታመም አስረድተዋልም፡፡
የጂኦፖለቲካው አዲስ ፈተና
ሌላው አስተያየት ሰጪ የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አብዱራሃማን ሰይድ ናቸው፡፡ የሆርሙዝ መዘጋት በተለይም የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ክፉኛ የሚፈትን ጉዳይ ነው፡፡ “ደሃ አገራት ይጎዳሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሲሪላንካ፣ ባንግላድሽ እና ግብጽ ጉዳቱ አሁንም ደርሷል” በማለት ገብጽ 24 ሰዓት ህይወት ባላቸው ከተሞቿ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ በጭለማ እንድትዋጥ መደረጉን በአብነት ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የነዳጅ ተጽእኖ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከቅርብ አመታት ወዲህ በርካታ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ በማተኮር ተስፋዎች መታየታቸውንም ትገልጻለች፡፡ እንደ የምጣነሃብት ባለሙያው ዶ/ር አብዱልመናን አስተያየት ግን ይህ ለአሁናዊው አንገብጋቢ ጉዳይ ግን መፍትሄ አይሆንም፡፡“ያ የረጅም ጊዜው ችግር መፍትሄ የሚታሰብበት ሆኖ አሁን የአጭር ጊዜ መፍትሄውን እንዴት እናምጣው ነው” በማለት ለአሁኑ ችግሩ ከቀጠለ ለጊዜያዊ መፍትሄ መቸገር የግድ ቢሆንም “ለወደፊቱ አርቆ ታስቦ መፍትሄ ለመውለድ መልካም አጋጣሚ” ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ የማዳበሪያ ጉዳይም ሌላው እራስ ምታት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
“ጦርነቱ ኢራንን የበለጠ ሊያጠናክራት ይችላል”
የአሜሪካ እና የኢራን ስምምነት ጊዜያዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለችግሩ መቋጨት ለጊዜው ምንም ዋስትና እንደሌሌው የቀጣናው ተንታኝ አቶ አብዱራሃማን በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡ “ባሁን ጊዜ ስምምነቱ በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ነውና እስራኤል ብዙ ያልተደሰቱበት ነገሮች ሊኖሩ ይችላል” በማለትም ኢራን በተለይም ሆርሙዝን እንደ ሉዓላዊ ግዛቷ መቁጠሯ እና ቀረጥ ለማስጀመር ማሰቧ ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም በመስጠት ድህረ ጦርነት ይበልጥ እንድትጠናከር ሊያደርጋት ይችላልም ብለዋል፡፡
ይህ የኢራን መጠናከር እውን ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮበአፍሪካ ቀንድ ላይ አዲስ የኃይል አስተላለፍ እንዲፈጠር ለማድረግ እድሉ መኖሩን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ያከሉት ዶ/ር አብዱልመናን፤ “ጦርነቱ አንድ ቀን እንኳን እረፍ ማግነት አልተቻለም፤ ተስማማን ባሉበት ቅጽበት ነገሮች ወደ ነበሩበት አለመረጋጋት ነው የተመለሱትና በዚህ ሁኔታ የቀጠለ እንደሆነ አደጋው ከፍ እያለ ነው ሚመጣ” በማለት የሌላው አገራት ኢኮኖሚ መዳከም በተለያየ መልኩ የኢትዮጵያንም ኢኮኖሚ ሊያዳክም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ