1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የእናቶችና ህጻናት ሞት

ሐሙስ፣ ሐምሌ 27 2015

" ከአዲስ አበባ አጎራባች አካባቢዎች የሚመጡ ህሙማን በጣም ከተዳከሙ ቦኋላ ስለሚመጡ፤ በጤና ተቋማቱ ከደረሱ ቦኋላም ወድያውኑ የሕክምና አገልግሎት ስለማይሰጣቸው፤ አልፎ አልፎም ሁሉንም የጤና ባለሙያ ባይወክልም የሙያ ስነምግባር ጉድለት ይታያል።"

Äthiopien | Ethiopian Ombudsman institute  Logo

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማሳሰቢያ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአዲስ አበባ ቁጥጥር ባደረገባቸው የጤና ተቋማት የእናቶች እና ሕጻናት ሞት መጨመሩን አስታወቀ። ድርጅቱ ይፋ ባደረገው የጥናት ውጤት እና ዋና ዕንባ ጠባቂው ለDW በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ለጤና አገልግሎት ተጠቃሚዎች እርካታ መጓደል በርካታ ምክንያቶችን ዘርዝረዋል።  
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመንግሥት መዋቅሮች በተሰጣቸው ሥልጣን እና ኃላፊነት መሠረት ለሕዝቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አለመስጠታቸውን መርምሮ ተጠሪ ለሆነበት የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ዘገባ ያቀርባል፤ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱም ያሳስባል። 
ዕንባ ጠባቂ ተቋም በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በአዲስ አበባ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቁጥጥር ባደረገባቸው  የመንግሥት የጤና ተቋማት የእናቶች እና ሕጻናት ሞት መጨመሩን የሚያሳዩ መረጃዎች ከራሳቸው ከተቋማቱ በተገኙ መረጃዎች ማረጋገጥ እንደተቻለ ዋና ዕንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ ነግረውናል።
"ይህ ያካሄድነው ቁጥጥር እንደሃገር የሚወክል አደለም፤ አዲስ አበባንም ሙሉ በሙሉ የሚወክል አደለም። ነገር ግን ቁጥጥር ባደረግንባቸው የጤና ተቋማት ላይ በ2015 የ9 ወራት ከአለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ሲነጻጸር የእናቶች እና ህጻናት ሞት ጭማሪ ያሳያል የሚል ሪፖርት ነው ያገኘነው።  "
የጤና ባለሙያዎች ምደባ እና ጥቅማጥቅሞች አለሟሟላት፣ አምቡላንሶች ለታለመላቸው አላማ አለማዋል፣ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር፣ የአልጋ እጥረት እና ሌሎችም ተገልጋዩ ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኝ እንዳደረጉ ተቋሙ ያወጣው ዘገባ ያመላክታል።
ጥናት ባደረጋችሁባቸው የጤና ተቀማት ለእናቶች እና ሕጻናት ሞት መጨመሩ እንደምክንያት የሚጠቅሱት ምንድነው ለሚለው ጥያቄያችን ዶክተር እንዳለ ተከታዩን ብለዋል።
" ከአዲስ አበባ አጎራባች አካባቢዎች የሚመጡ ህማን በጣም ከተዳከሙ ቦኋላ ስለሚመጡ፤ በጤና ተቋማቱ ከደረሱ ቦኋላም ወድያውኑ የሕክምና አገልግሎት ስለማይሰጣቸው፤ አልፎ አልፎም ሁሉንም የጤና ባለሙያ ባይወክልም የሙያ ስነምግባር ጉድለት በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።"
ዋና ዕምባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ኃይሌ በግብር ከፋዩ ኅብረተሰብ ደሞዝ ተከፋይ የሆኑ የመንግሥት ሠራተኖች በተለይም የጤና ሙያተኞች በኃላፊነት ስሜት መሥራት እንዳለባቸውም አሳስቧል።
ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊን በስልክ አግኝተን ለማነነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ኃላፊው ስልክ ባለማንሳታቸው ለጊዜው አልተሳካልንም።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ሽዋዬ ለገሰ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW