1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«እኔ ነኝ መፍትሔው» ንቅናቄ ጠንሳሽ እና አስተባባሪዎቹ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ መጋቢት 29 2015

«የማያሳብብ ፣ ትኩረቱን ራሱ ላይ ያደረገ ዜጋ መፍጠር ነው አላማችን» ይላሉ የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ተሳታፊዎች። «እኔ ነኝ መፍትሔው » በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ስድስት ከተሞች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እየሠሩ ይገኛሉ።

Anteneh Tesfaye Gründer der „I am the solution“-Bewegung
ምስል Anteneh Tesfaye

የ«እኔ ነኝ መፍትሔው» ንቅናቄ ጠንሳሽ እና አስተባባሪዎቹ

This browser does not support the audio element.

«የቆሸሹ ሀሳቦችን እየጣልን የወዳደቁ ፕላስቲኮችን እንሰብስብ » ይላል አንተነህ ተስፋዬ።  በኤፍ ኤም አዲስ የ«ጣፋጭ ሕይወት» የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ እና የ«እኔ ነኝ መፍትሔው» ንቅናቄ ሀሳብ አመንጪ እና አስተባባሪ ነው።  « ዋና ትኩረቱ ህፃናት፣ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ናቸው።  70% የምንሆን ወጣቶች በብዙ መፋዘዝ ውስጥ ነው ያለነው። ስለዚህ ነቃ ብለን ወደ ስራ ለመሄድ መሰነቅ ያለብን አንድ ስንቅ አዎንታዊ አስተሳሰብን መላበስ ነው» ይላል። 
ለዚህም «እኔ ነኝ መፍትሔው» አራት መርኃ ግብሮች ላይ አተኩሮ በተለያዩ ከተሞች እየሰራ እንደሆነ አንተነህ ገልፆልናል። ሐዋሳ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈው ሳምንት የተዘጋጀው የእኔ ነኝ መፍትሔው መርኃ ግብር ለሦስት ቀናት የዘለቀ ሲሆን «ቅን ልባዊ ድርጊት» የሚል ርዕስ ነበረው። ፕሮግራሙን ከ ሌሎች 24 የሐዋሳ ወጣቶች ጋር በመሆን ያስተባበረው ኢሳያስ አሰሌ ይባላል። ወጣቱ በሐዋሳ የበጎ ልቦች በጎ አድራጎት ማኅበር ምክትል ሰብሳቢም ነው።  ስለ ዝግጅቱ ሲያብራራ « በመጀመሪያው ቀን ከአዲስ አበባ ከመጡ እንግዶቻችን ጋር በመሆን ወደ ሶስት ትምህርት ቤቶች ነው የሄድነው። በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ መፍትሔው ሌላ ጋር ሳይሆን እዚሁ ራሳችን ጋር መፍትሔ ማግኘት እንደምንችል በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ብዙ ትምህርት የተሰጠበት ሁኔታ ነው የነበረው» ይላል። ከዚህም ሌላ ቆሻሻ እየሰበሰቡ የእግር ጉዞ ማድረግ፤ ወጣቶቹን በሚያሳስቧቸው ጉዳዮች ላይ በመወያየት፤ አረጋውያንን ምግብ በማብላት ሥራ ፣  የጥበብ ምሽት በማካሄድ ጊዜያቸውን እንዳሳለፉ ገልፆልናል።  የተወሰኑ ወራት ቀደም ብሎ የሐዋሳው አይነት መርኃ ግብር  ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ተካሂዶ ነበር። ቤተልሔም ተገኘ ዝግጅቱን ካስተባበሩት ወጣቶች አንዷ ስትሆን በባህር ዳር ዮንቨርስቲ የ 3ኛ ዓመት ተማሪ ናት።   « ታህሳስ 14 ነበር እኔ ነኝ መፍትሔው በባህር ዳር ፕሮግራም የነበረው። እኛም በየትምህርት ቤቱ እየዞርን እንዴት ታዳጊ ተማሪዎችን ማነፅ እንችላለን የሚለውን ስራ ስንሰራ ነበር። በቀጣይ ቀን ቆሻሻ ነገሮችን እየሰበስብን እና አካባቢዎችን እያፀዳን ከአዕምሮዋችን ያሉ ቆሻሻ ነገሮችን እንዴት ማውጣት እንችላለን እያለን እየተወያየን ነበር።»  

«እኔ ነኝ መፍትሔው» በባህር ዳርምስል Anteneh Tesfaye
«እኔ ነኝ መፍትሔው» በሐዋሳምስል Anteneh Tesfaye

የሐዋሳው ዝግጅታቸው ስኬታማ እንደነበር ምንም ጥርጥር የሌለው ኢሳያስ ወደፊት በጋራ ብዙ በጎ ሥራዎችን ከእኔ ነኝ መፍትሔው ጋር ለመሥራት እንዳቀዱ እና የሌሎች ተቋሞችን ትኩረት መሳብ እንደቻሉ ገልፆልናል። « ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሲዳማ ክልል ሴቶች እና ህፃናት ቢሮ ወጣቶች ዘርፍ ኃላፊ ጠርተውን ቢሮ ድረስ አናግረውናል። በቀጣይም በወጣቶች ስብዕና ግንባታ ላይ በጋራ መስራት እንዳለብን እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉልን ቃል ገብተውልናል።»
አንተነህ የጣፋጭ ሕይወት ዝግጅትን ከመጀመሩ፣ እኔ ነኝ መፍትሔው ብሎ ከመነሳቱ ወይም  በተለያዩ በጎ አድራጎ ስልጠናዎች ላይ ከመሳተፉ በፊት በብዙ ችግሮች ውስጥ ማለፉን አጫውቶናል።  ይህም ነው ሌሎች አዳጊ እና ወጣቶችን ለማነቃቃት ምክንያት የሆነው። « ሱስ በሚባል ነገር ውስጥ ወድቄ አሉታዊ የሆነ ህይወትን ሳጣጥም የነበርኩኝ ነኝ። በብዙ አስቸጋሪ የህይወት ፈተናዎች ውስጥ ያለፍኩኝ ልጅ ነኝ። ያንን ካሸነፍኩኝ በኋላ እኔ ከተቀየርኩ ሌላም ሰው መቀየር ይችላል በሚል መነሻ ነው እኔ ነኝ መፍትሔው የሚለውን ሀሳብ እንድጠነስስ ምክንያት የሆነኝ።» ይላል።
አንተነህ « እንደ እኔ በቁማር ሱስ የተጠመዱ ፣ በዚህ ምክንያት ትዳራቸው የፈረሰ፣ ቤታቸው የተናጋ ብዙ ሰዎች ነበሩ » ይላል። በማንኛውም ሱስ የተጠመዱ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከሱስ ለመላቀቅ የሌሎች ሰዎችን ድጋፍ ይሻሉ። አንተነህም ከነበረበት የቁማር ሱስ ለመላቀቅ እና እኔ ነኝ መፍትሔው ከሚለው ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ሌሎች ሰዎች ሚና ነበራቸው። « ልለወጥ የቻልኩት በጣም የምወዳቸው ሰዎችን አሳዘንኩኝ፤ አስከፋው። የእነሱ ማዘን እኔን በጣም ነው የሰበረኝ። በቃ ይኼ ነገር ከእኔ ጋር አይሄድም ብዬ ጨክኜ እንድወስን ያደረገኝ ይኼ ነው። » ከዚህም ሌላ ለመለወጡ መገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው አንተነህ ይናገራል።
የባህር ዳሯ ቤተልሔም ከእኔ ነኝ መፍትሔው ተሳትፎዋ በተጨማሪ የድንበር የለሽ በጎ አድራጎት ማህበርም አባል ናት። ሰውን መርዳት መውደዷ በበጎ አድራጎት ስራዎች እንድትሳተፍ እንዳደረጋት ትናገራለች። « ሰው ተቸግሮ ማየት አልፈልግም። አንድ ቀን እንደውም ለታክሴ የነበረችኝን 10 ብር ለአንድ መለኩሴ ሰጥቼ በእግሬ ወደ ቤት ሄጃለሁ። ሰው ሲቸገር ከማይ እኔ ብቸገር እመርጣለሁ» ትላለች።
የእኔ ነኝ መፍትሔው ንቅናቄ ከተጀመረ ሁለተኛ አመቱን ይዟል።  አንተነህ  በመደበኛ የሬዲዮ ዝግጅቱ አማካኝነት እና በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ወጣቶችን ያበረታታል፣ ያሰባስባል።  የትም ያሉ ኢትዮጵያውያን በዚህ መሳተፍ ይችላሉ ይላል አንተነህ። « ንፁህ ልብ አለኝ የሚል ሰው በሙሉ ሊቀላቀለን ይችላል። ሁላችንም ሰው መሆንን አስቀድመን እየተንቀሳቀስን ነው የምንገኘው።» 
«እኔ ነኝ መፍትሔው» ወደፊት  እንደ ማኅበር ተመዝግቦ የመሥራት እቅድ እንዳለ የሀሳቡ አመንጪ አንተነህ ተስፋዬ ገልፆልናል።

«እኔ ነኝ መፍትሔው» በአዲስ አበባምስል Anteneh Tesfaye

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW