1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእገታ እና የዉንበዳ ወንጀሎች መበራከት

ሥዩም ጌቱ
ማክሰኞ፣ ኅዳር 10 2017

በምዕራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ ሆለታ ከተማ የሰባት ዓመት ታዳጊን በማገት በሚሊየን ገንዘብ የጠየቁ ተፈረደባቸው፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጠቅላይ ፍርድ ቤት እያንዳንዱ የ11 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው ሶስት ወጣቶች እራሳቸውን በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በማስመሰል ወንጀሉን መፈጸማቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሸዋ ኦሮምያ ክልል
ሸዋ ኦሮምያ ክልል ምስል Seyoum Getu/DW

የእገታ እና የዉንበዳ ወንጀሎች መበራከት

This browser does not support the audio element.


በምዕራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ ሆለታ ከተማ የሰባት ዓመት ታዳጊን በማገት በሚሊየን ገንዘብ የጠየቁ ተፈረደባቸው፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጠቅላይ ፍርድ ቤት እያንዳንዱ የ11 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው ሶስት ወጣቶች እራሳቸውን በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በማስመሰል ወንጀሉን መፈጸማቸው ነው የተገለጸው፡፡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የዞኑ አቃቤ ህግ ባለስልጣን በሽምቅ መንግስትን በሚፋለሙት ታጣቂዎች ስም ሰዎችን በማገት ገንዝብ የመጠየቅ ወንጀል አሁን አሁን እየተበራከተ መጥቷል፤ ብለዋል፡፡
 
ወንጀሉ የተፈጸመው ጥቅምት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. በሆለታ ከተማ አስተዳደር ጋልገል ኩዩ ቀበሌ ልዩ ስሙ ካቢኔ ሰፈር ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ነው፡፡ አጋቾች ደግሞ በዚያው አከባቢውን በሚገባ የሚያውቁ ኤርሚያስ ሁንዴ፣ ብሩክ አብዮት እና ኢዩኤል ለማ የተባሉ ሶስት ወጣቶች ናቸው፡፡አጋቾቹሰባንቦን ጌታሁን የተባለን የ7 ዓመት ታዳጊ በቤተሰቦቹ ወደ ሱቅ እንደተላከ በባለ ሶስት እግር ተሸከርካሪ (ባጃጅ) አግተው ከከተማው በመሰወር ወጣ ባለ ስፍራ በኦና ቤት ውስጥ ዘግተው ያስቀምጣሉ፡፡ ወዲያውኑም ወደ ቤተሰቦቹ በመደወል አንድ ሚሊየን ብር እንዲከፍሉ አለበለዚያም ታዳጊ ህጻኑን በህይወት እንደማያገኙ አስረድተው የማስፈራሪያ መልእክት አስተላለፉላቸው፡፡
በምዕራብ ሸዋ ዞን የአቃቤ ህግ ልዩ ልዩ ወንጀሎች ምርመራ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ በቀለ ቤካ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየትም፤ “እለቱ እሁድ ነበር፡፡ ቀትር 8 ሰዓት ላይ፡፡ ታዳጊው ህጻን ለወላጆቹ ሱቅ ተልኮ በሚመለስበት ወቅት እነዚህ ተከሳሾች በባጃጅ እየሄዱ ጎረቤትም ስለነበሩ ልጁን ና ግባ እንሸንህ ይሉታል፡፡ ይህ የሆነው ሆለታ ከተማ ገልገል ኩዩ ቀበሌ ካቢኔ ሰፈር በሚባል አከባቢ ነው፡፡ ከዚያን ልጁን ባጃጅ ውስጥ ካስገቡ በኋላ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጄሬ ወረዳ ዳሞቱ የገጠር ቀበሌ ይወስዱና ኦና ቤት ውስጥ አስቀመጡት፡፡ ከዚያን ልጁን በተለያዩ ስለቶች በማስፈራራት እንዲፈራ አድርገው ወደ ተጎጂ ቤተሰብ ደውለው ልጁን በህይወት ለማግኘት ከፈለጋችሁ አንድ ሚሊየን ብር ላኩ በማለት አባቱን አስፈራሩ፡፡ የተደወለበት ተጎጂ አባት ለጸጥታ ሃይል በማሳወቃቸው የጸጥታ ሃይሉ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ባደረገው አሰሳ በማግስቱ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ታጋቹን ህጻን ከአጋቾች ጋር ጠዋት 1፡00 ግድም በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል” ነው ያሉት፡፡


አጋቾች “ጃል ዲዳ እባላለሁ” በማለት በትጥቅ መንግስትን የሚወጉት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እንደሆኑ በማስመሰል የተለያዩ ማስፈራሪያዎችን ስያደርሱ እንደነበርም ተነግሯል፡፡ የሆለታ ከተማ አስተዳደር የወንጀል ምርመራውን በፍጥነት በመከወን ለዞን አቃቤ ህግ በአስቸኳይ ተላልፏል፡፡ የዞን አቃቤ ህግም በ1996 በወጣው የወንጀል ህግ መሰረት ክስ ይመሰርታልም፡፡ “የዞን አቃቤ ህግ ክሱን መስርቶ ለዞን ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቀረባቸው፡፡ እነሱም ከተከላካይ ጠበቃቸው ጋር ተማክረው በሰጡት ቃል ሙሉ በሙሉ ወንጀሉን መፈጸማቸውን በማመናቸው የአቃቤ ህግ ምስክሮችን ማስማት ሳያስፈልግ በሰጡት ቃል መሰረት የጥፋተኝነት ብይን ተፈረደባቸው፡፡ በዚህም እያንዳንዳቸው የ11 ኣመት ጽኑ እስር ተበይኖባቸዋል” ነው የተባለው፡፡


መሰል የወንጅል ተግባር እምብዛም የተለመደ እንዳልነበር ያስረዱት የምዕራብ ሸዋ ዞን አቃቤ ህግ ባለስልጣኑ አሁን አሁን ግን በተለይም በትጥቅ የምንቀሳቀሱትን ታጣቂዎች በመምሰል መሰል ወንጀሎችን የሚፈጽሙ እየተበራከቱ ነው ብለዋል፡፡ “መሰል ተግባር በፊት ብዙም የተለመደ አልነበረም፡፡ ነገር ግን አሁን አሁን በትጥቅ የሚንቀሳቀሱ ሰዎችከተፈጠሩ ወዲህ ብዙ ወጣት በውንብድና እየተደራጁ እንዲህ ያለ የወንጀል ድርጊት ላይ በስፋት እየተሳተፉ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት መሰል ወንጀሎች በወረዳ ደረጃ ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ አግኝቷል፡፡ በዚህ ዓመት ደግሞ ገና ካሁኑ ሁለት መሰል መዝገቦች ውሳኔ አግኝቷል፡፡ እስካሁን በምርመራ ሂደት ላይ ያሉ ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች መኖራቸውን ለማረጋገጥ መዝገብ ማገላበት ብያስፈልግም፤ አምና ሶስት ዘንድሮ ሁለት ተመሳሳይ ወንጀል ወደ ህግ መጥቶ ውሳኔ አግኝቷል ማለት ነው”፡፡
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በታጠቁ አካላት ጭምር የሚፈጸሙ በርካታ የእገታ ዜናዎች ከዚህ በፊት በስፋት ተሰምታል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ እገታው መልኩን ቀያይሮ በተደራጁ ውንብድናም መከሰት ለመጀመሩ ይህ ጉዳይ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ በክልሉ ከተሸከርካሪዎች ጭምር በርካታ እገታዎች በተለያዩ ጊዜያት በታጠቁ አካላትም መፈጸማቸው ተደጋግሞ መዘገቡም አይዘነጋም፡፡


ስዩም ጌቱ 
አዜብ ታደሰ 
ታምራት ዲንሳ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW