የኦሞ ወንዝ ተፈናቃዮች የዘላቂ መፍትሄ ጥያቄ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 10 2017
የኦሞ ወንዝ ሙላት ለዘመናት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱ አዲስ አለመሆኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ናኮራ ሎኩ እና አቶ ሎዶኮር ኛታል «ከ2012 ዓም ወዲህ ግን የጉዳቱ መጠን እየጨመረ ነው የመጣው። በወረዳው ከሚገኙ 40 ቀበሌያት መካከል 28ቱ በውኃ ሙላቱ ተጠቂ ሆነዋል። በአንድ በኩል የኦሞ ወንዝ ሙላት በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የቱርካና ሐይቅ ይዞታውን እያሰፋ መምጣቱ ለመፈናቀላችን ምክንያት ነው። ስለዚህ መንግሥት የተቀናጀና ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል» ብለዋል።
ተጨማሪ ጉዳት የማስቀረት ጥረት
ተፈናቃዮቹ ያሉበትን ሁኔታ ሰሞኑን ተዘዋውረው የተመለከቱት የክልሉ ባለሥልጣናት በውኃ ሙላቱ የተፈናቀሉ ከ79 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በሦስት የመጠለያ ጣቢያዎች የሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል። የኦሞ ወንዝ እና የቱርካና ሐይቅ የደቀነውን ሥጋት በዘላቂነት ለመቅረፍ ሁለት ሥራዎች ተለይተው እየተሠሩ ሥለመሆኑ ለጋዜጠኞች የተናገሩት የክልሉ ውኃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ «አንደኛው የኦሞ ወንዝን አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ ነው። ለእሱ የንድፍ ሥራ ተሠርቶ አሁን ላይ ግንባታ ተጀምሯል። ሁለተኛው እየሞላ የመጣውን የቱርካና ሐይቅን መስፋት ለመከላከል 7.5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ግድብ በመገንባት የመኖሪያ መንደሮችን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው» ብለዋል።
የኦሞራቴ ከተማ እጣ ፋንታ
አሁን ላይ የቱርካና ሐይቅ እስከ 60 ኪሎ ሜትር ይዞታውን በማስፋት በዳሰነች ወረዳ የአስተዳደር ከተማ በሆነችው ኦሞራቴ በሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ስድስት ሺህ ነዋሪዎች ያላት የኦሞራቴ ከተማ ሥጋት ውስጥ መውደቋን የጠቀሱት በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ቢሮ ሃላፊና የቡድኑ አባል ዶክተር መሪሁን ፍቅሬ «ከተማው ተስፋ ያለው አይመስልም አሁን የጎርፉን ሙላት በጊዜያዊነት እየተከላከልን እንገኛለን። በቀጣይ ግን ከፍ ወዳለ ሥፍራ አዛውሮ እንደገና መገንባት ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህ እየሠራን እንገኛለን» ብለዋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን የሚገኘው የዳሰነች ወረዳ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በደረሰ የኦሞ ወንዝና የቱርካና ሐይቅ ሙላት ትምህርት ቤቶች፣ የህክምና ተቋማት እና የመኖሪያ ቤቶች በውኃ ተውጠው ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን ከወረዳው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ