1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሞ ወንዝ እና የቱርካና ሐይቅ የውኃ ሙላት የኦሞራቴ ከተማን አስግቷታል

ሰኞ፣ ነሐሴ 20 2016

የኦሞ ወንዝ እና በኬንያ ድንበር ላይ የሚገኘው ቱርካና ሐይቅ የውኃ ሙላት የኦሞራቴ ከተማን ሥጋት ውስጥ እንደጣሉ የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ። የውኃ ሙላቱ 10,000 ገደማ ነዋሪዎች ወዳሏት ኦሞራቴ እንዳይገባ ጥረት እየተደረገ ነው። በኦሞ ወንዝ የሞላው ቱርካና ሐይቅ ከኦሞራቴ ከተማ በ2.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

የኦሞ ወንዝ
የኦሞ ወንዝ ከአንድ አቅጣጫ፤ የቱርካና ኃይቅ ውኃ በሌላ አቅጣጫ ወደ ኦሞራቴ ከተማ እየተቃረቡ በመሆኑ ከፍተኛ ሥጋት እንደፈጠረ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ምስል Dasenech Wereda communication

የኦሞ ወንዝ እና የቱርካና ሐይቅ የውኃ ሙላት የኦሞራቴ ከተማን አስግቷታል

This browser does not support the audio element.

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ክረምት በመጣ ቁጥር የኦሞ ወንዝ ሙላትና የነዋሪዎች መፈናቀል ተለይቶት አያውቅም ፡፡ ለወትሮ የዳሰነች የጎርፍ አደጋ ምንጭ የኦሞ ወንዝ ብቻ ነበር ፡፡ ዘንድሮ የበረታ ነው በተባለለት ክረምት ግን  ከኦሞ በተጨማሪ በኬኒያ አዋሳኝ ድንበር ላይ የሚገኘው የቱርካና (ሩዶልፍ) ሀይቅ ሌላ የሥጋት ምንጭ ሆኖ ብቅ ብሏል ፡፡

አሁን የተከሰተው የውሃ ሙላት ቀደም ካሉት ዓመታት አንጻር ሲታይ ከበድ ያለ መሆኑን የዳሰነች ወረዳ አስተዳደር አስታውቋል ፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ  የውሃ  ሙላት ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ከሚገኙ 79  ሺህ  ነዋሪዎች መካከል 15 ሺህ ያህሉን ወንዙ በድጋሚ ማፈናቀሉን አስተዳደሩ ጠቅሷል  ፡፡

በውሃ የተከበበችው ኦሞራቴ

አሁን ላይ የኦሞ ወንዝና የቱርካና ሀይቅ በሁለት አቅጣጫ ይዞታቸውን በማስፋት የኦሞራቴ ከተማን መክበባቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡

የኦሞ ወንዝ  የመጨረሻ መዳረሻ በኢትዮጵያና በኬኒያ አዋሳኝ ድንበር የሚገኘው የቱርካ ሀይቅ መሆኑን የጠቀሱት የከተማው ነዋሪዎች መሳይ ፓሪት እና ናኪያ ዩሱፌ “ወንዙ ሞልቶ ወደ ኋላ በመመለስ የኦሞራቴ ከተማን እየተጠጋ ይገኛል ፡፡ በአንድ በኩል ወንዙ በሌላ ደግሞ ሀይቁ ከተማውን ከበውታል ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ የአፈር ግድብ ስንሥራ ነው ያደርነው  ፡፡ ዛሬ የውሃው ከፍታ የሚጨምር ከሆነ የከተማው ቤቶች በሙሉ ሊዋጡ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለ “ ብለዋል ፡፡

የውኃ ሙላቱ ወደ ኦሞራቴ ከተማ እንዳይገባ የአካባቢው አስተዳደር እና ነዋሪዎች ለመገደብ ጥረት ላይ ናቸው። ምስል Dasenech Wereda communication

የመከላከል ሥራው

በዳሰነች በኦሞ ወንዝ ሙላት የዳግም መፈናቀል እያስከተለ ይገኛል። ወንዙ በከፍተኛ ፍጥነት ሞልቶ መደበኛ የመፍሰሻ አቅጣጫውን ለቆ በመውጣቱ እና የቱርካና ሀይቅም መደበኛ ይዞታውን ማስፋቱን  የዳሰነች ወረዳ አስታውቋል ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎርፍ ከ3ሺህ በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ አደረገ

ውሃው እየተስፋፋ በኦሞራቴ ከተማና አካባቢው ላይ  የሚፈጥረው ስጋት እየጨመረ መምጣቱን የጠቀሱት የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ “ አሁን ላይ በከተማዋ ዙሪያ የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ፡፡ ለዚህም ከሁሉም የመንግሥት ባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ግብረሀይል ተዋቅሯል ፡፡በየአቅጣጫው ሞልቶ እየተስፋፋ ያለውን ውሃ በሰው ሀይልና በተሽከርካሪ የአፈር ካቦችን የመከተር ሥራ እየተከናወነ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡

ዘላቂ መፍትሄ

በዳሰነች ወረዳ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የውሃ ሙላት ነዋሪው ተረጋግቶ በመኖር የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን ማድረጉን የጠቀሱት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ሀቴ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የፌዴራሉ መንግሥት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲፈልጉ ሲሉ ጠይቀዋል ፡፡

የኦሞ ወንዝ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ እየሞላ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ምስል Dasenech Wereda communication

በደቡብ ከ62 ሺህ በላይ ሰዎች በወንዝ ሙላት ተፈናቀሉ 

ወንዙን በተለያዩ አቅጣጫዎች ለማፋሰስ የሚረዱ የውሃ መውረጃዎችን መገንባት ሥራዎች እንደሚከናወን ከዓመታት በፊት መገለጹን ያስታወሱት አቶ ታደለ “ በእኛ በኩል ዕቅዱ ወደ ሥራ እንዲለወጥ  ለክልሉ መንግሥት ፣ የፌዴራል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ጠይቀናል ፡፡ ይሁንአንጂ እስከአሁን ከእነኝህ አካላት ተግባራዊ ምላሽ ባለመገኘቱ ወረዳውን ከጎርፍ አደጋ ለመታደግ ሳይቻል ቀርቷል “ ብለዋል። 

ከዓመታት በፊት በውሃ ሙላት የፈናቀሉት የዳሰነች ነዋሪዎች ችግር ላይ ናቸው

ዶቼ ቬለ ለውሃ ሙላቱ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ያሥፈልጋል በሚል በቀረበው አስተያየት ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልንም ሆነ የፌዴራል መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎችን ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ የኦሞ ወንዝ በ2014 ዓ.ም በዚሁ በዳሰነች ወረዳ አድርሶት በነበረው የውሃ ሙላት ከ79 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ሲያፈናቅል በርካታ የመሠረተ ልማት አውታሮችን ማውደሙ ይታወሳል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW