1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወሰን ማካለሉ በ147 ቀበሌዎች ይካሄዳል

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 12 2009

በአካባቢ ይገባኛል ጥያቄ እና በድንበር ጉዳይ ግጭት ላይ የከረሙት የሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ትላንት ተፈራርመዋል፡፡ በስምምነቱ መሰረት በሚቀጥሉት ሶስት ወራት በሁለቱ ክልሎች የአስተዳደራዊ ወሰን ማካለል ይከናወናል ተብሏል፡፡ 

Somalia Äthiopien Viehzucht-Nomaden
ምስል DW/J. Jeffrey

Oromia & Somali region to resolve border dispute - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.

የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች በወሰን ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ በዚህ ዓመት የተከሰተው የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ቀደም ሲል ተመሳሳይ ችግሮች ተከስተው ጉዳዩን ለመፍታት ህዝበ-ውሳኔ እሰከማካሄድ ሁሉ ደርሰው ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ በሁለቱ ክልሎች ወሰን የሚገኙ 422 ቀበሌዎችን ተካትተዋል፡፡ ከዓመታት በኋላ በድጋሚ ባገረሸው የአካባቢ ይገባኛል ጥያቄ ከወራት በፊት የበርካቶችን ህይወት የቀጠፈ ግጭት መከሰቱ ይታወሳል፡፡ 

ሁለቱ ክልሎች በፕሬዝዳንቶቻቸው አማካኝነት ትላንት የፈረሙት ስምምነት ህዝበ ውሳኔው ላይ የተንተራሰ እንደሆነ የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ ለዶይቸ ቨለ ተናግረዋል፡፡ 

“በትናትናው ዕለት የነበረው ዋና አጀንዳ ህዝቡ የመረጠውና በህዝበ ውሳኔው ያረጋገጠውን የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ወደ ተግባር የመቀየር የፊርማ ስምምነት ነው” ይላሉ ምክትል ኃላፊው፡፡

በስምምነቱ መሰረት በቀጣይ ሶስት ወራት የወሰን ማካለል ይካሄዳል ተብሏል፡፡ ለዚህም የሚረዳ የሁለቱን ክልል ፕሬዝዳንቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ባለሙያዎችን የያዘ የቴክኒክ ኮሚቴ መቋቋሙን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡ የቴክኒክ ኮሚቴው “ህዝቡ የመረጠውን በደንብ አጥንቶ እና ሁለቱን ክልሎች ሊያግባባ የሚችል ውሳኔ ይወስዳል” ይላሉ አቶ አለማየሁ፡፡ የወሰን ማካለሉ የሚካሄድባቸው በሰባት ዞኖች የሚገኙ 147 ቀበሌዎች ናቸው፡፡

“ሰባቱ ዞኖች ኦሮሚያ እና ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚያዋስኑ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምስራቅ ሐረርጌ፣ ባሌ፣ ጉጂ እና ቦረና እነኚህን የሚያካትተው፡፡ ከእነዚህ ጋር የሚያዋስኑ ዞኖች አሉ፡፡ ጥያቄ ሲነሳባቸው የነበሩ ሁለቱ ክልሎች ወረዳዎች አሉ፡፡ ያንን ጥያቄ ከበላይ ወይም ከተወሰነ የመንግስት አካል ሳይሆን ህዝቡ ነው ያንን ወደዚህ ይሻለኛል ብሎ የሚወስነው፡፡ የሁለቱ የጋራ ስምምነት ያን የተወሰነውን በተግባር ለመቀየር፣ ለአስተዳደር አመቺ በሚሆን፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ያንን ውሳኔ እና ምርጫ በማያፋልስ፣ ያንን መሰረት አድርጎ ለቀጣይ ስኬታማ ይሆናል ተብሎ የታመነበት ነው” ብለዋል አቶ አለማየሁ፡፡  

ስምምነቱን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ “ድል” ሲሉ የጠሩት ሲሆን “ካሁን በኋላ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ” ሲባል የተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የአስተዳደር እና ጸጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ስምምነቱ በመዘግየቱ ለበርካቶች ሞት ምክንያት መሆኑን ያስተጋባሉ፡፡ በሁለቱ ክልሎች መካከል በነበረው ግጭት በሁለቱም ወገኖች በርካቶች መሞታቸውን ቢናገሩም በቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ 

“አንደኛ መዘግየቱ ራሱ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ይሄ ለዚህ ሁሉ ጥፋት በተለይ ለሰው ህይወት መዘግየቱ ዋና መንስኤ ነው የሚል በደንብ ታይቷል፡፡ እንደገና ደግሞ ለጠፋው ህይወት የሚጠየቁ አካላት በዝርዝር ከሁለቱም አካላት እንደ ግለሰብም እንደ ቡድንም የሚጠየቁበት አካሄድ አለ” ይላሉ ምክትል ኃላፊው፡፡   

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም ትላንት በጽህፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሁለቱ ክልሎች መካከል ለነበረው ግጭት ተጠያቂዎች የሆኑ አካላት በህግ እንደሚጠየቁ ተናግረዋል፡፡ 

“ለዚህ ችግር መንስኤ የሆኑ አካላት ሁሉም ወንጀል የሰራ ሁሉ በወንጀል መጠየቅ አለበት፡፡ ወንጀል ሰርቶ ምንም ምክንያት ማቅረብ አይቻልም፡፡ የሰው ህይወት ተኩሰህ ገድለህ ስታበቃ በዚህ ምክንያት ነው ተኩሼ የገደልኩት ብለህ ምክንያት ማቅረብ አትችልም፡፡ ማንም ሰው የሰውን ህይወት ያጠፋ ሰው መጠየቅ አለበት፡፡ ስለዚህ የሰው ህይወት ደመ ከልብ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ አኳያ መረጃዎቹ ህግ ፊት ቀርበው ተጠያቂ የሚያደርጉ መረጃዎች ያሉ በመሆኑ በዚህ ላይ የተሳተፈ አካል በሙሉ ተጠያቂ የሚሆንበት ስርዓት ይቀጥላል ማለት ነው፡፡”

 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW