1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የኦሮሚያ ክልል ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ መጋቢት 19 2017

በምዕራብ ኦሮሚያ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የፀጥታ ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ ነዉ። ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ታጥቀዉ በስፋት በሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) እና በመንግሥት ጸጥታ ሃይሎች መካከል በሚፈፀሙ ግጭቶች ለፀጥታው መደፍረስ ዋነኛ ተጠያቂዎች መሆናቸዉ ባለፉት ስደስት ዓመታት በጉልህ ታይቷል።

ፎቶ ማህደር ፤ ኦሮምያ ክልል
ፎቶ ማህደር ፤ ኦሮምያ ክልል ምስል፦ G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ምዕራብ ኦሮሚያ ወቅታዊ ሁኔታ

This browser does not support the audio element.

የኦሮሚያ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ

በምዕራብ ኦሮሚያ የምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ነዋሪ ስለአከባቢያው የፀጥታ ሁኔታው ያላቸው አስተያየትና ስሜት የተደበላለቀ ነው። ወትሮም ላለፉት ጥቂት ዓመታት ስያስጨንቃቸው ከከረመው የጸጥታው መደፍረስ መጠነኛ እፎይታ መገኘቱን ያልሸሸጉት ነዋሪ አሁንም ድረስ ግን ለዓመታት ሰላማዊውን የአከባቢ ህዝብ ያሰለቸው ግጭት አሁንም እስከወዲያኛው ተወግዷል የሚያስብል ደረጃ ላይ አለመድረሱን አስረድተዋል። “እንቅስቃሴው አሁን ጥሩ ነው። ነገር ግን ፍራቻ አለ። ታጣቂዎች ይንቀሳቀሳሉ። በኦሮሚያ በኩል ያሉ ታጣቂዎች አልፎ አልፎ ለዝርፊያ ከሚንቀሳቀሱት ውጪ ብዙም አይስተዋሉም ለመንግስትም ስጋት በሚሆኑበት ደረጃ አይመስልም ብለዋል። በአማራ ስም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ግን አሁንም ድረስ አልፎ አልፎ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር የሚታኮሱበት፤ በተለይም ከጊዳ አያና ወደ ጉቲን ነቀምቴ በሚወስድ መንገድ ዲቾ በሚባል ተራራማ ስፍራ አከባቢ የመንገደኞች ተሸከርካሪ ላይ ጥቃት በመፈጸም አልፎ አልፎ ጉዳትም ስለሚያደርሱ አከባቢው ከስጋት የጸዳ ነው ለማለት ያስቸግራል” ሲሉ አሁናዊ ስለሆነዉ ስለአከባቢው የፀጥታ ሁኔታ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል። 

አሁን ላይ በተሻሻለው የፀጥታው ይዞታ በደጋማ የወረዳዋ አከባቢዎች አርሶ አደሮ በበርካታ ቦታዎች ወደ መደበኛ የእርሻ ህይወታቸው መመለሳቸውንም የገለጹት ነዋሪው፤ በወረዳው ቆላማ አከባቢዎች ላይ ግን ታጣቂዎች በስፋት ስለሚንቀሳቀሱ በርካታ አርሶአደሮች ከቤት ንብረታቸዉ መፈናቀላቸዉ ለመከራ ህይወት መጋፈጣቸዉ  ቀጥሏል ብለዋል።

“ህዝቡ በደጋማ አከባቢዎች ላይ ወደ ቀዬው ተመልሶ ወደ ምርት ቢገባም ወደ ቆላማ አከባቢዎች ላይ ግን ሲመለስ በታጣቂዎች ስለሚመታ አልተመለሰም። በደጋማ አከባቢዎችም ቢሆን ሙሉ በሙሉ ሳይሆን ሰው በከፊል ነው ወደ መረጋጋት ሕይወት የተመለሰው” ያሉት አስተያየት ሰጪው በተለይም በከተሞች አከባቢ የኮሪደር ልማት በሚል የሚከወን የቤቶች ፈረሳ በርካቶች ላይ ጉዳት ቢያደርስም የፀጥታ መረጋጋቱ በተሸለ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።የኦሮምያ ግጭት፤ «ሰላማዊ ሰው ይገደላል ፤ጫናው ከፍተኛ ስለሆነ የሚናገር ሰው የለም»

በቅርቡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስተዳደራዊ ወሰኖች በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጣሰ መሆኑ አሳስቦኛል በሚል ባወጣው መግለጫ ከአማራ ክልሉ የሚመጡ ባሏቸው ታጣቂዎች በወሰን አከባቢ ባሉ ማህበረሰቦች ላይ በሚፈጸም ጥቃት ስጋት ካንዣበበባው አከባቢዎች የኪረሙ እና አሙሩ ወረዳዎች ቆላማ ስፍራዎች ተጠቃሽ እንደነበሩ ማስታወቁ አይዘነጋም።

በማዕከላዊ ኦሮሚያ የምዕራብ ሸዋ

ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ታጥቆ በስፋት በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) እና በመንግስት ጸጥታ ሃይሎች መካከል በሚፈፀም ግጭት የፀጥታው መደፍረስ ዋነኛው ተጠቂ የክልሉ ነዋሪ መሆኑን ባለፉት ስደስት ዓመታት በጉልህ ታይቷል። መንግስት ታጣቂዎቹ ላይ እየወሰድኩ ነው ባለው ወታደራዊ እርምጃ በቅርቡም ድል እንደቀናው ደጋግሞ አስታውቋል። ለአብነትም በምዕራብ ሸዋ ዞን ጅባት ወረዳ በአከባቢው ሸማቂዎች ላይ እርምጃ በወሰደው በአገር መከላከያ ሰራዊት በታጣቂ ቡድኑ ላይ ከፍተኛ የሰውና የመሳሪያ ኮሳራ መድረሱን ባሳለፍነው ሳምንት ላይ መንግስታዊ የመረጃ ምንጮች በስፋት ዘግበውት ነበር። ከዚሁ አከባቢ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኖኖ ወረዳ ነዋሪ ስለጉዳዩ ማረጋገጫ በመስጠት በዚሁ ወረዳቸው እና በዙሪያቸው በሚገኙ እንደ ዳኖ፣ ጅባት እና አመያ ባሉ ወረዳዎች በወቅቱ ስለሚስተዋለው የፀጥታው ይዞታ አስተያየታቸውን አጋርተውናል።

“የፀጥታ ይዞታው አሁን ላይ አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ምንም አይልም ሰላም ነው። ትልሽ የከፋ የፀጥታ ችግሩ ያለው በዚህ በደቡብ በኩል እንደ አማያ ባሉ ወረዳዎች አዋሳኝ ላይ ነው። በዙሪያችን ባሉ ዳኖ እና ጅባት ወረዳዎችም የመከላከያ ሰራዊቱ በቋምነት እየተንቀሳቀሰ የሃይል እርምጃ ስወስድ እየተመለከትን ነው። በቅርቡ ጅባት ላይ የተወሰደው አንዱ ምሳሌ ይመስለኛል። በዚህ በአከባቢያችን አመያ፣ ጅባት እና የደቡብ ክልል አዋሳኝ አከባቢዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር ምንም አይልም መልካም ነው አሁን” ሲሉ መረጋጋቶች መስተዋላቸውን ገልጸዋል።ለምዕራብ ኦሮምያው ግጭት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪ

ፎቶ ማህደር ፤ ኦሮምያ ክልል ምስል፦ G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

እገታ ባልተቋረጠበት ሰሜን ሸዋ ዞን

በቅርቡ ከአንድ ሳምንት በፊት አንድ ሙሉ አውቶብስ መንገደኞች ከዋናው መንገድ ላይ ታፍነው የተወሰዱበት አይታወቅም በሚባልለት የሰሜን ሸዋ ሰላሌ ዞን አከባቢም ተስፋም ጭንቀትም አብሮ መታየታቸውን ነው ነዋሪዎች የሚገልጹት። በዞኑ የደብረጽጌ ከተማ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ፤ “አሁን ፀጥ ያለ ነገር ነው የሚስተዋለው” ያሉ ሲሆን፤ ማህበረሰቡ አሁን ላይ በቀንም ሆነ በሌሊት እንቅስቃሴ ቢያደርግም ነገር ግን በስጋት ድባብ ውስጥ በመሆን ነው ብለዋል። አክለውም “ሰው በተወለደበት አገር በሰላም ቢኖር ነበር ጥሩ” ብለው “የተሻለውን ከፈጣሪ እንደሚጠብቁ” በተስፋ ድምጽ አስጠያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ሰሜን ሸዋ ዞን ከፍተኛ የፀጥታው ችግር ከሚስተዋልባቸው እንደ ሂደቡ አቦቴ ባሉ ወረዳዎች ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱንና በርካቶችም እጃቸውን በሰላም ስለመስጠታቸውን የአገር መከላከያ ሰራዊት መረጃዎች አሳይተዋል። በታጣቂ ቡድኑ በኩል ግን በዚህ ላይ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልተሰማም።

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW