1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያ ክልል ግጭትና የመንግሥት ማስተባበያ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 16 2015

በክልሉ የተለያዩ ቀውሶችን በመፍጠር በመንግሥት የሚከሰሰው መንግስት «‘ሸነ» ያለውና እራሱን «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» ብሎ የሚጠራው ሸማቂ ቡድን ከጥቅምት 10 ወዲህ ብቻ ስድስት ጊዜ የድሮን ጥቃት በኦሮሚያ መፈጸሙን አመልክቷል፡፡

Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

በኦሮሚያ ክልል የተሰነዘረ የድሮን ጥቃት የለም-ክልሉ

This browser does not support the audio element.

 

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብና ምሥራቅ ሸዋ እንዲሁም ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የመንግስት ፀጥታ አስከባሪዎች በሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) በሰነዘሩት ጥቃት ሰላማዊ ሰዎችን ጭምር ገድለዋል የሚለዉን ዘገባ የክልሉ መንግሥት አስተባበለ፡፡የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ከፍያለዉ ተፈራ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት እስካሁን ድረስ በኦሮሚያ አንድም ቦታ የተወሰደ የድሮን ጥቃት የለም፡፡

ባለፈው እሁድ ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ በኬ ኦፉ ቀበሌ ደርሷል በተባለው በድሮን የታገዘ የአየር ጥቃት ከ60 በላይ ሰላማዊ ዜጎችን መገደላቸዉና  ከ100 በላይ መቁሰላቸዉን ነዋሪዎች ገለጸው ነበር፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በፊናቸው “መንግስትና በመንግስት በሚደገፉ ኃይሎች” በኦሮሚያ ክልል የሚፈጽሙትን የንፁሃን ዜጎች ግድያ እንዲያቆሙ በጠየቁበት መግለጫ፤ በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች ንጹሃንን ሰለባ ያደረገ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን አመልክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ፀጥታ እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ኮሚሽነር ከፍያለው ተፈራ ግን ክሶቹን በማስተባበል “በኦሮሚያ ውስጥ የተወሰደ አንድም የአየር ጥቃት የለም” ብለዋል።

“በኦሮሚያ ባሁን ወቅት ሸነ የተባሉትን ከህወሓት ጋር የሚሰሩ ታጣቂዎችን እየተፋለሙ የሚገኙት ፖለቲስና የምሊሻ ታጣቂዎች ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ደግሞ ምን እንደታጠቁ ይታወቃል፡፡ የድሮን ጥቃት በኦሮሚያ ተፈጽሟል መባሉ ፍጹም ሀሰት ነው፡፡ በርግጥ ይህ ኃይል ከዚህ የፖሊስ እና ምሊሻ አቅም በላይ መሆኑ ሲረጋገጥ መንግስት አስፈላጊ የሆነውን የትኛውንም የጦር አማራች መጠቀም ግዴታውና መብቱ ነው፡፡ ለጊዜው ግን ቡድኑ ከዚህ አቅም በላይ ባለመሆኑ የወሰድነው የአየር ጥቃት የለም ማለት ነው” ሲሉ ተፈጽሟል የተባለውን የድሮን ጥቃት አስተባብለዋል፡፡

ኮሚሽነር ከፍያለሁ ተፈራ በኦሮሚያ በትጥቅ የሚንቀሳቀሰውን መንግስት “ሸነ” ሲል የሚጠራውና እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” በማለት የሚጠራውን የሽምቅ ተዋጊ ቡድንን በሰሜን ኢትዮጵያ መንግስትን ከሚወጋው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር በመስራትም ከሰውታል፡፡ ኃላፊው ሰሞነኛውን የኦሮሚያውን የድሮን ጥቃት ክሱንም “በታጣቂዎች የተቀነባበረ የመንግስትን ስም የማጥፋት ዘመቻ” ሲሉ ነው ያጣጣሉት፡፡

“የድሮን ቴክሎጂ የኢላማ ትክክለኛነት ያለው ነው፡፡ ድሮን በኦሮሚያ ጥቅም ላይ ብውል የተባለው የንጹሃን ጥቃት የመፈጠር እድልም አይኖረውም ነበር፡፡ ደግሜ እላለሁ የፕሮፓጋንዳው አካል ካልሆነ በስተቀር ድሮን ለመጠቀም የምንገደድበት ሁኔታ ላይ አይደለንም” ብለዋልም፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በህወሓት አገራዊ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ያሉትን ሙከሪያ መንግስታቸው መቀልበሱን የሚያነሱት የኦሮሚያው የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊው፤ የዚሁ ኦፕሬሽን ተቀጽላ የሆነ ያሉት የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ በኦሮሚያ ተጠናክሮ እየተወሰደ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው ኮሚሽነር ከፍያለሁ ተፈራ ይህን ይበሉ እንጂ፤ በክልሉ የተለያዩ ቀውሶችን በመፍጠር በመንግስት የሚከሰሰው መንግስት ‘ሸነ’ ያለውና እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ብሎ የሚጠራው ሸማቂ ቡድን ከጥቅምት 10 ወዲህ ብቻ ስድስት ጊዜ የድሮን ጥቃት በኦሮሚያ መፈጸሙን አመልክቷል፡፡ ቃል አቀባዩ ኦዳ ተርቢ በትዊተር እንደጻፉት “ሰዎች በሚበዙባቸው ከተሞችንም ጭምር ኢላማ ያደርጋል” ያሉት ጥቃቱ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችን ቀጥፏል፡፡” በምዕራብ ሸዋ ጮቢ እና ሜታ ወልቂጤ ወረዳዎች እንኳ 150 ሰዎች በዚሁ ጥቃት መሞታቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስም በሰሞነኛው መግለጫው እንዳመለከተው በኦሮሚያ 120 ንጹሃን በያዝነው ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት ብቻ በመንግስት የፀጥታ ሃይላት እና ተባባሪዎቹ ባሏቸው መገደላቸውን አመልክቷል፡፡ ኦፌኮ በመግለጫው በምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች ንጹሃን ያጠቃ የድሮን ጥቃት መፈጸሙንም በመግለጫው ጠቅሶ ነበር፡፡

ዶይቼ ቬለ ስለውዝግቡ ከገለልተኛ አካል ማጣራት አልቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በጉዳዩ ላይ ተጠይቆ ገና በምርመራ ሂደት ላይ መሆኑን ነግሮናል፡፡

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW