1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮሚያውን ግጭት ማስቆሚያ መፍትሄው ምንድነው ?

ዓርብ፣ ኅዳር 6 2017

የክልሉ መንግስት መንግስትን ከሚፋለመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ጋር ለቀጣይ ሶስተኛ ዙር የሰላም ድርድር ለመቀመጥ ስለመወጠን አለመወጠኑ ያለው ነገር የለም፡፡ ዶይቼ ቬለ ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባለስልጣንት በተደጋጋሚ በመደወልና የጽሁፍ መልዕክትም በመላክ ያደረገው ጥረትም እስካሁን ምላሽ አላገኘም

Äthiopien Addis Abeba | Oromia Regionalkonferenz
ምስል Seyoum Getu/DW

የኦሮሚያውን ግጭት ማስቆሚያ መፍትሄው ምንድነው ?

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ግጭት ለመፍታት መንግስት ልዩነቶችና አለመግባባትን በሰላም ለመጨረስ ከታጣቂዎች ጋር ለሚደረግ የትኛውም ውይይት ዝግጁ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዛሬ ከሰዓት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የአቋም መግለጫ ሲል ይፋ ባደረገው አቋሙ በክልሉ በተለያዩ አከባቢዎች ህዝቡ ያሰማውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ከታጣቂዎች ጋር ልዩነቶችን ለመፍታት እሩቅ ለመሄድ ዝግጁነቱን ገልጿልም፡፡ በሌላው በኩል ግን በሶስተኛ ወገን አደራዳሪዎች እየተገፋ ያለውን በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) እና በመንግሥት መካከል ለሶስተኛ ዙር የድርድር ሂደት ተፋላሚዎችን ወደ አንድ መድረክ እንዲያመጣ የሚጠየቅ ጥያቄ በመንግስት በተደጋጋሚ ውድቅ መደረጉን በመንግስት ተፋላሚው ኦ.ነ.ሰ እየተገለጸ ነው፡፡

የኦሮምያ ግጭት፤ «ሰላማዊ ሰው ይገደላል ፤ጫናው ከፍተኛ ስለሆነ የሚናገር ሰው የለም»

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ዛሬ ከሰዓት ባወጣው መግለጫ፤ የክልሉ ህዝብ ለረጅም ጊዜ ያስቸገረው የጸጥታ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በትላልቅ ሰላማዊ ሰልፎች ደጋግሞ መጠየቁን አስረድቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ይህን ጥሪ የሚያከብርና የሚደግፈው ነው ያለው መግለጫው በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ግጭት ለመፍታት ወደርየለሽ እልባቱ በሰላማዊ መንገድ የሚደረግ ውይይት መሆኑ የመንግስት ጽኑ እምነት እንደሆነም አስረድቷል፡፡መንግስት ለሰላም ቁርጠኛ መሆኑን ስገልጽም፤ የተዘረጉ እጆች እንደማይታጠፉ ብሎም ሁሉንም አካል አሸናፊ የሚደርገው የሰላም መንገድ እውን እንዲሆን ከዚህ በፊት በታንዛንያ በሁለት ዙር የሰላም ድርድር መደረጉን በማሳያነት ጠቅሶ ለዚህም “የፖለቲካ ነጋዴ” ያሏቸው በስም ያልጠቀሳቸው፤ ነገር ግን ሰላም እንዳይመጣ ይጥራሉ በሚል የገለጻቸውን አካላት ማለፍ የግድ እንደነበርም ጠቆም አድርጓል፡፡

የክልሉ መንግስት የሰላም ቁርጠኝነቱን በገለጸበት በዚህ መግለጫ በክልሉ መንግስትን ከሚፋለመው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ጋር ለቀጣይ ሶስተኛ ዙር የሰላም ድርድር ለመቀመጥ ስለመወጠን አለመወጠኑ ያለው ነገር የለም፡፡ ዶይቼ ቬለ ለክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባለስልጣንት በተደጋጋሚ በመደወልና የጽኁፍ መልእክትም በመላክ ያደረገው ጥረትም እስካሁን ምላሽ ባለማግኘቱ ተጨማሪ ማብራሪያዎችን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም፡፡የኦሮምያው ተቃውሞ እና የሂዩመን ራይትስ ዎች ዘገባ፣ የኦነግ ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ውሎ፣ በጅማ ተከሰተ የተባለው ግጭት

በሌላ በኩል ግን በኦሮሚያ ክልል በስፋት ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ የሚገኘው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ባወጣው መግለጫ ከትናንት ጀምሮ በስፋት በኦሮሚያ ክልል በርካታ ዞኖች ውስጥ የተካሄዱት ስለሰላም የተጣሩ ሰላማዊ ሰልፎች “መንግስት ባልተገባ መንገድ ተጠቅሟል” ሲል ተችቷል፡፡ የታጣቂ ቡድኑ ዋና አዛዥ አማካሪ ጅሬኛ ጉደታ በዚህ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡና ቀጣይ የምክክር መድረክ ስለመጀመር አለመጀመሩ ተጠይቀው፤ “እውነት ለመናገር በርካታ ጥረቶች ብደረጉም ሶስተኛ ዙር የሰላም ውይይት ተጀምሯል ለማለት አልደፍርም፡፡ አሁን ቀጣይ ዙር የሰላም ውይይት ማካሄድ ያስፈልጋል ወይ

ምስል Seyoum Getu/DW

የሚለው በራሱ ሊጤን የሚገባ ነው፡፡ ይህን ለማየት ከዚህ በፊት ምን ላይ ተወያይትን ምን ላይ አልተግባባንም የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዋናነት በወቅቱ በኛ በኩል የቀረበው ሃሳብ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ እንዲወስን የሚያስችለው ለምርጫ መደላድል የሚፈጥሩ እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የፍትህ ስርዓት፣ ጸረ-ሙስና፣ ሚዲያ እና የሰብዓዊ ተሟጋች ተቋማት ነጻ የማድረግ ውጥን የያዘ የተቋማት ግንባታ ማረጋገጥ ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ተወካዮች እና የተለያዩ ማህበረሰብ አካላት ተወካዮችም በሂደቱ ተሳትፈው ድርሻ ብወስዱ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ስለሚፈጥሩ ወደ ጦርነት የማይመልሰን ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት ይዘን ነበርና ያ ብሆን አሁን ላይ የሚፋለሙ ሁለቱ ሰራዊቶች አንድ መድረክ ላይ እንመለከታቸው ነበር” ብለዋል፡፡ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ከ 50 በላይ ሰዎች ተገደሉ

አቶ ጅሬኛ በአደራዳሪ ቡድኖች የሚቀርቡ ቀጣይ የውይይት መድረክ የማመቻቸት ጥረት መንግስት ሂደቱን በመግፋቱ አልሰመረም ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ “አደራዳሪ ወገኖች እኛ ጋም በተደጋጋሚ ይመጣሉ፡፡ መንግስት ጋርም ደጋግመው ይሄዳሉ፡፡ መንግስት ግን እነሱ የጠየቁን ከልክ በላይ ስለሆነ በኃይል ችግሩን እንፈታለን የሚል ምላሽ ነው የሚሰጣቸው፡፡ እኛ ግን ጠይቀን የነበረው የፖለቲካ ምህዳሩን የሚያሰፉ ተቋማት ይገንቡ የሚል ነበር፡፡ ይህ ተቀባይ ካገኘ በኛ በኩል በቼም ዝግጁ ነን” ሲሉም ለቀታይ ምዕራፉ የሰላም ድርድር ያለውን ዝግጁነት አስረድተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አክሎ እንዳሳየው በክልሉ ስንቀሳቀሱ ከቆዩት ታጣቂዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ጦር መሳሪያ እያስቀመጡ በሰላም እየተመለሱ ነው ብሏል፡፡ በክልሉ ከሰሞኑ የተካሄዱ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፎችም ህዝቡ ለሰላም ለውን ፍላጎቱን ያሳየበት በመሆኑ፤ መንግስት የትኛውም ርቀት በመሄድ ከታጣቂዎች ጋር ለሚደረግ የትኛውም ውይይት ዝግጁ ነው ብሏል፡፡

ሥዩም ጌቱ 

ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW